በሃይማኖት ተቋማት መካከል ውይይት በማደረግ ግጭቶችን መፍታት እንደ ሚቻል ተገለጸ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተለያዩ አርስቶች ላይ ተንተርሰው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በኅዳር 03/2012 ዓ.ም ከእዚህ ቀደም በሐዋርያት ሥራ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ካደረጉት የክፍል 16 አስተምህሮ ማጠቃለያ ላይ እንደ ተለመደው ለዓለም ባስተላለፉት መልእክት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት ባለፈው ሳምንት በቡርኪና ፋሶ በክርስቲያኖች ላይ በተቃጣው ጥቃት በደርሰው አደጋ እጅግ ማዘናቸውን ቅዱስነታቸው የገለጹ ሲሆን ማነኛውንም መልኩ በክርስቲያኖች ላይ የሚቃጣውን ጥቃት ለማስወገድ ይችላ ዘንድ በሃይማኖት ተቋማት መካከል ተገናኝቶ የመወያየት ባሕል ሊጎለበት ይገባል ብለዋል።
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
“በተወደደው ቡርኪና ፋሶ ሕዝብ ላይ በተወሰኑ ጊዜያት ውስጥ ብቻ በተደጋጋሚ በተቃጣው ጥቃት ምክንያት በቅርቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት በመቅጠፉ እጅግ አዝኛለሁ፣ ሐሳቤም ከእናንተ ጋር ነው” ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን በእዚህች አፍሪካዊ እና እጅግ ድሃ በሆነች አገር ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በአክራሪ የእስልምና ኃይሎች አማካይነት እየተቃጣ በሚገኘው ጥቃት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለሞት፣ ለአካል ጉዳት እና ብሎም ለስደት በመዳረግ ላይ መሆናቸው ይታወቃል። ቅዱስነታቸው ይህንን በተመለከተ ሲናገሩ . . .
“በእጅጉ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ጥበቃ እንዲደረግላቸው እጠይቃለሁ፣ ስለሆነም የሲቪል ባለስልጣናት እና የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ሁሉ በቅርቡ በአቡ ዳቢ ሰብአዊ ወንድማማችነትን በተመለከተ በተፈራረምነው ሰነድ ላይ በመመስረት በሃይማኖት ተቋማት መካከል ውይይት እንዲደረግ እና ስምምነት እንዲፈጠር ጥረቶች እንዲያደርጉ ተነሳሽነትን እንዲወስዱ አበረታታለሁ”።
በቡርኪና ፋሶ 26 የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች እንደ ሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን 65 የተለያዩ ቋንቋዎች በአገሪቷ ውስጥ ይገኛሉ። አብዛኛውን የቡርኪና ፋሶ ሕዝብ የእስልምና እምነት ተከታይ እንደ ሆነ የሚታወቅ ሲሆን ከእዚህ ቀደም በነበሩ ጊዜያ በአፍሪካ አእጉር ከሚገኙ አገራት መካከል የተሻለ መረጋጋት እና ሰላም የሰፈነባት አገር እንደ ነበረች ይታወሳል። ከቅርብ አመታት ወዲህ አንሳር አል ኢስላም በመባል የሚታወቀው እና አልቃይዳ ከሚባለው የአሸባሪዎች ቡድን ጋር ትስስር ካለው ቡድን ጋር የቅረበ ግንኙነት ባለው የአሸባሪ ቡድን በአገሪቷ ከፍተኛ የሆነ ጥቃት በመፈጸም ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደ ሚገኝ የሚታወቅ ሲሆን ብዙዎችን ለሞት ገሚሱን ደግሞ ለአካል ጉዳት እና ለስደት መዳረጉ ይታወሳል።