ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “እግዚኣብሔር ጸሎታችንን ይሰማል!”

እ.አ.አ በ2017 ዓ.ም “ወንድሜ” በማባል የሚታወቀው በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የተቋቋመ ማህበር ከኅዳር 04-07/2012 ዓ.ም ድረስ ሦስተኛውን ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ለማክበር በፈረንሳይ አገር ወደ ሚገኘው እና ሉርድ ማርያም በመባል በሚታወቀው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቀድስ ንግደት በማደረግ ላይ እንደ ሚገኙ የተገለጸ ሲሆን በእዚህም የንግደት ስነ-ስረዓት ላይ ለድሆች እና ለአቅመ ደካማ ለሆኑ የማኅበርሰብ ክፍሎች ያላቸውን ድጋፍ እና ቁርጠኛ ድጋፍ ለመገለጽ እና ለማበረታታት በማሰብ ጸሎት እና ሱባሄ በማድረግ ላይ እንደ ሚገኙ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ይህንን ሦስተኛውን ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ለማክበር በፈረንሳይ አገር ወደ ሚገኘው ሉርድ ማርያም በመባል በሚታወቀው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቀድስ ንግደት ላደረጉ “ወንድሜ” በመባል ለሚታወቀው ማኅበር አባላት በቪዲዮ መልእክት አስተላልፈዋል፣ የእዚህን የቅዱስነታቸውን መልእክት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አስናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ የ”ወንድሜ” ማኅበር ነጋዲያን

ሦስተኛውን የዓለም የድሆች ቀን ለማክበር ወደ ሉርድ ማርያም እንኳን በሰላም መጣችሁ። እዚያ የተቀበለቻችሁ ማርያም ራሷዋ ናት። እርሷ እንከን የሌለባት ንፅህት ናት!

እርሷ ሕጻን ደሃ እረኛ ለነበረችው ለበርናዲት ተገለጸች። ለእኛ ድሃ እና ትናንሽ መሆናችንን ለምናውቅ ለሁላችንም መልካም ዜና ነው፣ ይህም ማለት “እግዚአብሔር ራሱን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውሮ ለሕፃናት ገለጠላቸው” ማለት ነው።

እግዚአብሔር የእሱን ጣፋጭ የሆነ ግልጸት ለሁሉም ሰው ማሳየት ይፈልጋል።

ወንድሞች እና እህቶች እያንዳንዳችሁን እፈልጋችኋለሁ። ምናልባትም ብቸኛ ፣ ገለልተኛ ፣ የተዘነጋችሁ፣ መኖሪያ ቤት የሌላችሁ፣ ቤተሰቦቻችሁን እና አገራችሁን ለቃችሁ ለመሰደድ የተገደዳችሁ፣ የአልኮል መጠጥ ሱሰኛ የሆናችሁ፣ አስገዳጅ በሆነ መልኩ በዝሙት አዳሪነት ሥራ ላይ የተሰማራችሁ፣ በሕመም ውስጥ የምትገኙ ሁላችሁ፣ እናንተ በመስቀሉ እግር ሥር ትገኛላችሁ። እግዚአብሔር እንደሚወዳችሁ አስተውሉ።  እግዚአብሔር በተለየ ሁኔታ የእናንተን ጸሎት ይሰማል።

ዓለም በስቃይ ውስጥ ይገኛል፣ እናም የእናንተ ጸሎት ጌታን ያነቃቃዋል።

እናንተ አናሳ የምትባሉ ድሆች፣ አቅመ ደካሞች፣ ለጥቃት ተጋላጭ የሆናችሁ ሰዎች፣ እናንተ የቤተክርስቲያን ሀብት ናችሁ። እናንተ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ፣ በማርያም እና በእግዚኣብሔር ልብ ውስጥ ትገኛላችሁ።

የእናንተ ሕይወት በሚረገጥበት፣ በሚበደልበት፣ በሚዋረደበት ጊዜያት ሁሉ የሚረገጠው፣ የሚበደለው የሚዋረደው ኢየሱስ ራሱ ነው።

ዛሬ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊያጽናናችሁ ይፈልጋሉ፣ እንደሚወዱዋችሁ እና ወደ ሥር መሰረታችሁ እንድትመለሱ ይጋብዙዋችኋል።

1. ጸልዩ፣ ማርያምን በውስጣችሁ ተቀበሉ፣ በእርስዋ ጠለላ ሥር ተቀመጡ። እርሷ ክፍት የሆነ የቤተክርስቲያን በር ናት። እርሷ መንፈስ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ ተቀብላለች። እርሷ ኢየሱስን ሰጠችን ወደ እርሱም ትመራናለች። ጸልዩ እግዚኣብሔርን ለምኑት፣ እርሱ ወደ ሕይወታችን እንዲገባ ጠይቁት “ልትወደኝ የመጣህ ጌታ ሆይ ፣ እኔም እንድወድህ ወደ እኔ ና! ጣፋጩን ርህራሄውን በዓለም ሁሉ ላይ እንዲያሰራጭ እግዚአብሔርን ጠይቁት።

2. ቅዱሳን ምስጢራንት በሕይወታችሁ ለመኖር ሞክሩ፣ ቤተክርስቲያኗ በምስጢራት የታገዘ ሕይወት እንዲኖራችሁ ሀሳብ ታቀርብላችኋለች፣ ምክንያቱም እነርሱ ስጦታዎች ናቸውና።

ክርስቲያን መሆን ትፈለጋላችሁን? እንግዲያውስ ምስጢረ ጥምቀት እንዲሰጣሁ ጠይቁ።

እግዚአብሔር ርህራሄውን የሚያሳየን እና ነፃ የሚያደርግበትን የምስጢር፣ የኃጢያት ሥርዕት ማስገኘት የሚችለውን ምስጢረ ንስሐን ልዩ በሆነ መንገድ ይገልጽላችሁ ዘንድ እንድትጠይቁት እጋብዛችኋለሁ።

ወደ ሰውነታችሁ እና ወደ ነፍሳችሁ ጭምር እንዲገባ እግዚአብሔርን በቅዱስ ቁርባን መቀበል ትችሉ ዘንድ ለምኑት።  እሱ እምነትን እና ደስታን ይሰጣችኋል። 

በአካል ወይም በአዕምሮ ቁስል ለሚሰቃዩ ለእናተ እና ለእናተ ባጣም ውድ ለሆኑ በጣም ቅርብ የሆኑ ሰዎችን ቁስል ይፈውስ ዘንድ የቅባ ቅዱስ ምስጢርን በሕይወታችሁ ለመኖር ጠይቁ። እናተ የበጎ አድርጎት ሥራ በመሥራት ለመኖር ሞክሩ፣ ለሰዎች መስጠት የማይችል ማንም ሰው በእዚህ ምድር የለምና።  በዙሪያችን ላሉት ሰዎች የበጎ ሥራ ተግባራትን እንድናከናውን እና መልካም ተግባር እንድንፈጽም መንፈስ ቅዱስ፣ የፍቅር መንፈስን እንዲያነሳሳ እንማጸነው።

ፍቅር ዓለምን ያድናል፣ እናም እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን በእኛ በኩል ማለፍ ይፈልጋል። በመጨረሻም ፣ ከእዚያ ስፍራ በምትመለሱበት ወቅት አመላለሳችሁ እንደ አካሄዳችሁ አይሁን።  በተስፋ ተሞልታችሁ ተመለሱ ፣ በዙሪያችሁ ያለውን የእግዚአብሔር ፍቅር መስካሪዎች ሁኑ።

ሐብታችሁ “ኢየሱስ” እንደ ሆነ ለዓለም ተናገሩ። ከማርያም ጋር አብራችሁ ተራመዱ፣ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ርህራሄ ሐዋርያ ታደርጋችኋለችና። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እናንተን ይወዳል፣ በእናንተም ይተማመናል። መንፈስ ቅዱስ በፍቅሩ ሁላችሁንም ያድሳችሁ ዘንድ ሁላችሁንም እባርካችኋለሁ! አሜን።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
15 November 2019, 16:14