ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የእግዚኣብሔር ሕግ ከኃጢአት ባርነት ነጻ እንድንሆን የሚረዳን መሳሪያ ነው” አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ ከማቴዎስ ወንጌል (5፡17-37) ተወስዶ በተነበበው ኢየሱስ በተራራ ላይ ሆኖ በሰበከው ስብከት ላይ መሰረቱን ያደርገ አስተንትኖ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በየካቲት 08/2012 ዓ.ም ባደረጉት አስተንትኖ “የእግዚኣብሔር ሕግ ከኃጢአት ባርነት ነጻ ሆነን እንድንኖር የሚረዳን መሳሪያ ነው” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 08/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!

የዛሬው (የካቲት 08/2012 ዓ.ም) ቅዱስ ወንጌል (ማቴዎስ 5፡17-37) “ኢየሱስ በተራራ ላይ ካደርገው ስብከት” የተወሰደ እና ሕግ ሁሉ ፍጻሜን እንደ ሚያገኝ የሚገልጽ ነው፣ እኔ ሕግን በሕይወቴ እንዴት ተፈጻሚ ማድረግ እንዳለብኝ የሚገልጽ ነው። በሕጉ አማካይነት እውነተኛ ነፃነት እና ኃላፊነቶችን መቀበል እንዳለብን እግዚአብሔርም በእነርሱ ውስጥ እንደሚገኝ በመናገር ለሙሴ የተሰጡት ትእዛዛት ትክክለኛ መንገድ እንዲያገኙ ኢየሱስ አድማጮቹን ሊረዳቸው ይፈልጋል። እሱ እንደ አንድ የነፃነት መሳሪያ ሆኖ መኖር ነው። ይህንን መርሳት የለብንም - ህጉን እንደ ነጻነት መሳሪያ አድርጎ መኖር፣ ነፃ እንድንሆን የሚረዳን፣ ለስሜቶች እና ለኃጢያት ባሪያ ላለመሆን የሚረዳን ሕግ ነው። ስለ ጦርነቶች እናስባለን፣ ጦርነቶች የሚያስከትሏቸውን ውጤቶች እናስባለን፣ በእርስ በእርስ ጦርነት በፈራረሰቺው በሶሪያ በቅዝቃዜ ምክንያት በቅርቡ የሞተችውን ሕጻን ልጅ እናስባለን። እጅግ ብዙ መከራዎች እጅግ ብዙ መከራ። ይህ የፍላጎቶች እና የስሜት ውጤት ነው እናም ጦርነት የሚያደርጉ ሰዎች ፍላጎቶቻቸውን መቆጣጠር አይችሉም። በእዚህ ረገድ የእግዚኣብሔር ሕግ ሳይፈጽም ቀርቷል። ለፈተናዎች እና ምኞቶች ስንሸነፍ የሕይወታችን ጌታ እና ዋና ገጸ-ባሕሪ መሆናችን ይቀራል፣  ነገሮችን በፍቃዳችን እና በኃላፊነት ለማስተዳደር አንችልም።

የኢየሱስ ንግግር በአራት ተቃራኒ ውቅሮች የተዋቀረ ነው “እንዲህ እንደ ተባለ ሰምታችኋል . . . እኔ ግን እንዲህ እላችኋለሁ” የሚለው የመጀመሪያው ነው። እነዚህ ተቃርኖዎች የዕለት ተዕለት ኑሮን ሁኔታዎችን ያመለክታሉ - ግድያን፣ ማመንዘርን፣ ፍቺን እና መሐላን ያመለክታሉ። ኢየሱስ እነዚህን ችግሮች የሚመለከቱትን ሕጎች አልሻራቸውም፣ ነገር ግን ጥልቅ ፍቺዎቻቸውን ያብራራል፣ እናም እነሱን በተግባር ላይ ለማዋል አስፈላጊ የሆነውን መንፈስ ያመለክታል። እርሱ መደበኛ በሆነ መልኩ ሕግን ከማክበር መሰረታዊ በሆነ መልኩ ሕግን ወደ ማክበር በመሻገር ህጉን በልባችን ውስጥ መቀበል እንዳለብን፣ ይህም የእያንዳንዳችንን ዓላማ፣ ውሳኔዎች፣ ቃላት እና አካላዊ መገለጫዎች እንድሆኑ ያበረታታናል። ጥሩ እና መጥፎ ድርጊቶች የሚጀምሩት ከልብ ነውና።

በልብህ ውስጥ የእግዚአብሔርን ህግ ተቀብለህ ጎረቤትህን የማትወድ ከሆነ ራስህን እና ሌሎችን በተወሰነ ደረጃ እንደምትገድል ትገነዘባለህ ምክንያቱም ጥላቻ፣ መቀናቀን እና መከፋፈል የግለሰባዊ ግንኙነቶች መሠረት የሆነውን የበጎ አድራጎት ተግባር ይገድላልና። ይህ ደግሞ ስለ ጦርነት ከእዚህ ቀደም የተናገርኩትን ይመለከታል፣ ምክንያቱም ምላስ ይገድላል። በልባችን ውስጥ የእግዚአብሔርን ህግ መቀበል ስሜቶቻችንን በምን መልኩ መመራት እንዳለባቸው እንድንገነዘብ ይረዱናል፣ ምክንያቱም የምንፈልገውን ነገር ሁሉ ማግኘት አንችልም፣ እናም ለራስ ወዳድነት እና ለግል ስሜታችን ቦታ መስጠት ጥሩ እንዳልሆነ እንረዳለን። የእግዚአብሔርን ህግ በልብህ ስትቀበል በየጊዜው በምናፈርሳቸው ቃል ኪዳኖች ላይ የተገነባውን የአኗኗር ዘይቤዎች መተው እንዳለብን፣ እንዲሁም በውሸት መሐላ ከማደረግ ይልቅ ከእውነት ጋር ሙሉ በሙሉ ቅንነት እንዲሰማህ ማድረግ እንደሚቻል ትገነዘባለህ።

ትእዛዛቱን በዚህ በተሟላ መንገድ መኖር ቀላል እንዳልሆነ ኢየሱስ ያውቃል። በዚህም ምክንያት የፍቅሩን ዕርዳታ ይሰጠናል ወደ ዓለም የመጣው ሕግ ተፈጻሚ እንዲሆን ለማደረግ ብቻ ሳይሆን እርሱን ሆነ ወንድሞቻችንን በመወደድ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸም እንድንችል ጸጋውን ሊሰጠን ጭምር ነው። ሁሉም ነገር በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ተመስርተን ማድረግ እንችላለን! ከሁሉም በላይ ደግሞ ቅድስና እግዚአብሔር የሰጠንን ይህንን ጸጋ ከመጠበቅ ጋር የተያያዘ ነው። በእርሱ መልካምነት እና በእርሱ ጸጋ በመታመን እና በመተማመን እርሱ ቀጣይነት ባለው መልኩ በነጻ ከሚያደርግልን እርዳታ መታገዝ አስፈላጊነት እና ቁርጠኝነት በተሞላ መልኩ እርሱ በሚሰጠን ጸጋ በመደገፍ በምሕረቱም ተሞልተን ወደ ፊት መጓዝ ይኖርብናል።

ዛሬ ኢየሱስ ባሳየን እና ከልባችን በሚጀምረው የፍቅር መንገድ ላይ እንድጓዝ ኢየሱስ ይጠይቀናል። እንደ ክርስቲያን ለመኖር ከፈለግን መንገዱ ይህ ነው። እውነተኛ ደስታ ለማግኘት እና ፍትህና ሰላምን በሁሉም ቦታ ለማሰራጨት ልጇ የተጓዘበትን መንገድ መከተል እንችል ዘንድ እመቤታችን ድንግል ማርያም እንድትረዳን አማላጅነቷን መማጸን ያስፈልጋል።

Photogallery

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በየካቲት 08/2012 ዓ.ም ያደረጉት የብስራተ ገብርኤል ጸሎት
16 February 2020, 12:16