ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የጥላቻ እና የበቀል ስሜት ማሸነፍ ያስፈልጋል”።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሑድ የካቲት 15/2012 ዓ. ም. የደቡብ ጣሊያን ከተማ፣ በባሪ ተገኝተው ካሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ስርዓት በመቀጠል፣ በሥፍራው ከተገኙት ምዕመናን ጋር ሆነው የዕኩለ ቀኑን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አድርሰዋል። ቅዱስነታቸው የመስዋዕተ ቅዳሴውን ጸሎት ከተካፈሉት በርካታ ምዕመናን ጋር የዕኩለ ቀኑን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማቅረባቸው አስቀድመው ንግግር አድርገዋል። የቅዱስነታቸውን ንግግር ሙሉ ይዘት ተርጉመን እንደሚከተለው አርቅርበነዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ!
በዛሬው ዕለት በአንድነት ሆነን በምንጸልይበት፣ ስለ ሰላም በማናስተነትንበት በዚህ ሰዓት፣ በሜዲቴራንያን ባሕር ወዲያኛው በኩል የሚገኙ፣ በተለይም በሰሜን ምዕራብ ሶርያ ግዛት በሚገኙ ሕዝቦች ላይ የተነሳው ጦርነት የበርካታ ሰዎችን ሕይወት እያጠፋ ይገኛል። በመሆኑም እኛ የሐይማኖት መሪዎች፣ በዚህ አስከፊ ጦርነት የተሳተፉት እና የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም፣ የሕጻናትን እና የአቅመ ደካሞችን ለቅሶ እና ዋይታን በማዳመጥ፣ የግል ጥቅም ፍለጋን ወደ ጎን በማድረግ፣ የንጹሃን ዘጎችን ነፍስ ከሞት አደጋ እንዲያተርፉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
እያንዳንዱ ሰው መጥፎ አስተሳሰብን ከልቡ እንዲያስወግድ ፣ የጥላቻ እና የበቀል ስሜትን እንዲያሸንፍ፣ የአንድ አባት ልጆች መሆናችንን እንዲገነዘቡ ጸሎታችንን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ እናቀርባለን። ምክንያቱም እግዚአብሔር ለክፉዎችና ለቅኖች ፀሐዩን ያወጣል (የማቴ. 5:45)። እያንዳንዳችን በእለታዊ የፍቅር ተግባራችን በኩል መልካምን በማድረግ አዲስ ወዳጅነትን እንድንፈጥር፣ እርስ በእርስ በመደማመጥ፣ አንዱ ሌላውን በትዕግስት በመረዳት፣ አንዱ ሌላውን በእንግድነት ተቀብሎ በማስተናገድ፣ ከቅዱስ ወንጌል የሚገኘውን እውነተኛ ደስታ በራሳችን ውስጥ እና በምንኖርበት አካባቢ ማምጣት የሚያስችለንን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ እንለምን። የመድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናት የሆነች፣ የታማኝነት ምሳሌ ሆና የተገኘች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መልካም የሆነውን ሁሉ እንድናደርግ ብርታትን እንድትሰጠን፣ የእርሷን እገዛ በጸሎት እንጠይቅ።
የዛሬውን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማቅረባችን አስቀድሞ፣ ባለፉት ቀናት ውስጥ፣ እዚህ በባሪ ከተማ “የሜዲቴራኒያን አካባቢ አገሮች ሰላም” በሚል ርዕሥ ሲወያዩ ለቆዩት የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ከብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በተጨማሪ ለጉባኤው ጠቃሚ ሃሳቦችን በማቅረብ ለመልካም ውጤት እንዲበቁ ለተባበሩት በርካታ አባላት ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በዓለማችን ሰላም ይሰፍን ዘንድ ከፍተኛ እገዛን በማድረግ ላይ በሚገኝ በዚህ አካባቢ፣ እርስ በእርስ የመገናኘት፣ በጋራ የመወያየት እና አብሮ የመኖር ባሕል እንዲያድግ የበኩላችሁን አስተዋጽዖ ላደረጋችሁ እና በማድረግ ላይ ላላችሁ በሙሉ ምስጋናዬን አቀርብላችኋለሁ”።