ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ማኅበረሰባችንን ከሚጎዱ ጎጂ ሱሶች መላቀቅ ያስፈልጋል”።
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለሚያዝያ ወር የሚሆን የጸሎት ሃሳባቸውን ይፋ አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ለመላው ምዕመናን በላኩት የቪዲዮ መልዕክት፣ ባሁኑ ጊዜ ጎጂ ሱሶች ሕብረተሰባችንን ክፉኛ እየጎዱ መሆኑን ገልጸው ዓመሉ ያለባቸው ሰዎች በሙሉ ነጻ እንዲወጡ በጸሎታችን እንድንረዳቸው አደራ ብለዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በዓለም አቀፍ የጸሎት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት በኩል ይፋ የሆነው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቪዲዮ መልዕክት ባሁኑ ጊዜ በዓላማችን ውስጥ በጎጂ ሱሶች የተጠቁ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መኖራቸውን አስታውቆ፣ ቅዱስነታቸው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በሰዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ ጭንቀት እና ስቃይ በማስታወስ በጸሎታችን እንድናግዛቸው አደራ ማለታቸውን ጽሕፈት ቤቱ ግልጿል።
ሕብረተሰባችንን በመጉዳት ላይ የሚገኙ ጎጂ ሱሶች በአደንዛዥ ዕጽ፣ በአልኮል መጠጦች እና በሲጃራ ብቻ አልተወሰኑም። በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው አዲስ መልክ ይዘው የወጡ ጎጂ ሱሶች እንዳሉ፣ ከእነዚህም መካከል ካለፉት አሥርት ዓመታት ወዲህ እያደገ የመጣው የኢንተርኔት አጠቃቀም፣ ኮምፒዩተሮች፣ ዘመናዊ ስልኮች እና ሌሎች ኤሌክትርኒክስ ዕቃዎች ለተጠቃሚዎቻቸው እና ለመላው ሕብረተሰብ ከሚሰጡት በርካታ ጥቅሞች በተጨማሪ ለበርካታ ሰዓታት በሚገለገሉባቸው ሰዎች ጤና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖችን እያስከተሉ መሆኑ ታውቋል። የቁማር ውድድሮች፣ ወሲባዊ ምስሎች፣ ከመጠን ያለፉ የቪዲዮ ጨዋታዎች፣ ዲጂታሉን ዓለም ያለማቋረጥ በተከታታይ መጠቀም ለጎጂ ሱሶች እንደሚያጋልጥ የጤና ድርጅቱ አስታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው እንዳስታወቁት በምናባዊ ዲጂታል ዓለም በኩል የሚመጡ ጎጂ ሱሶችን ማስወገድ የሚቻለው ምሕረት የሚገኝበትን ወንጌል በመስበክ፣ በአዳዲስ ዓይነት ጎጂ ሱሶች የተጠቁት ሰዎች እንክብካቤ ተደርጎላቸው ፈውስን እንዲያገኙ፣ ከችግሩ ወጥተው ራሳቸውን የሚችሉበትን እና ከማሕበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ የሚያግዙ ውጥኖችን መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።
የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ እና የቅዱስ ቁርባን ወጣቶች እንቅስቃሴ ጽ/ቤት አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ በበኩላቸው፣ የክርስቲያን ማሕበረሰብ ለችግሩ መፍትሄን ማግኘት ይኖርባቸዋል ብለው በተጨማሪም በጎጂ ሱሶች የተጠቁ ሰዎች ከችግራቸው እንዲያገግሙ አስፈላጊውን እርዳታ የሚያድረጉ ብቃት ያላቸው ድርጅቶች እና ማሕበራት መኖራቸውን ገልጸው ክርስቲያን ማሕበረሰብም በበኩሉ የማይናቅ ድጋፍ ማድረግ የሚችል መሆኑን ገልጸዋል። ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ በማከልም ክርስቲያን ማሕበረሰብ በጎጂ ሱሶች የተጎዱትን በወንድማዊ ፍቅር በመቀበል ምሕረትን በማድረግ ከሚገኙበት ችግር እና ከሌሎች ችግሮችም ነጻ ሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲገናኙ በማድረግ የእግዚአብሔርን የማዳን ኃይል እንዲያውቁ ማድረግ ይችላሉ ብለው፣ ክርስቲያናዊ የሕይወት ልምድ ሰዎች ወደ ሞት ከሚመራ ጨለማ መንገድ ወጥተው ዘለዓለማዊ ሕይወትን እንዲመርጡ ያግዛል ብለዋል። በሕመም የምትሰቃይ ነፍስ መኖሯን ያወቁ፣ ኤቫግሬዎስ ፖንቲኩስ የተባሉ የአራተኛው ክፍለ ዘመን መንፈሳዊ አባትን ያስታወሱት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ፣ ሕይወታችንን የእግዚአብሔር ቃል በመመገብ መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት (ዮሐ. 14፡6) ወደ ሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መመለስ እንደሚቻል አባ ኤቫግሬዎስ ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቪዲዮ መልዕክታቸው በጎጂ ሱሶች ተይዘው ለሚሰቃዩት የዘውትር ክትትል እና እርዳታን በማድረግ ከሚገኙበት ስቃይ ነጻ እንዲወጡ ማድረግ ያስፈልጋል ማለታቸው ታውቋል።