ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የኢየሱስ ትንሳኤ የመጨረሻው ቃል ሞት ሳይሆን ሕይወት እንደሆነ ይነግረናል” አሉ!
የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል ባለፈው እሁድ በሚያዝያ 04/2012 ዓ.ም ተከብሮ ማለፉ የሚታወስ ሲሆን ከፋሲካ በዓል (እሁድ እለት) ቀጥሎ የሚገኘው ሰኞ ቀን “የመልአክት ሰኞ” በመባል ይጠራል። ይህንን መጠሪያ ያገኘው ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ምንጮች ጋር በተገናኘ መልኩ በጥንት ጊዜ በነበረው በጣም ውብ በሆነ ባህል ላይ መሰረቱን ያደርገ ነው። በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ (ማቴዎስ 28:1-10፣ ማርቆስ 16:1-7፣ ሉቃስ 24:1-12) እንደ ተጠቀሰው ሴቶቹ ማለትም ማርያም እና መቅደላዊት ማርያም ኢየሱስ ወደ ተቀበረበት መካነ መቃብር በሄዱበት ወቅት መካነ መቃብሩ ክፍት ሆኖ አገኙት። ከእዚህ ቀደም መቃብሩ በአንድ ትልቅ ድንጋይ ተዘግቶ ስለነበር ወደ መቃብሩ ውስጥ ለመግባት ፈርተው ነበር። አሁን ግን ክፍት ሆኖ አገኙት፣ ከመቃብሩ ውስጥም “ኢየሱስ በእዚህ ስፍራ የለም፣ ከሞት ተነስቱዋል” የሚለውን ድምጽ ሰሙ፣ እነርሱም “ክርስቶስ ከሙታን ተነስቱዋል” በማለት ለመጀመሪያ ጊዜ ለደቀመዛሙርት መናገራቸው በማሰብ የሚከበር አመታዊ በዓል በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ማለፉ ተገልጹዋል።
የአዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
ቅዱስነታቸው መስዋዕተ ቅዳሴውን አሳርገው ካጠናቀቁ በኋላ በእኩለ ቀን ላይ እንደ ተለመደ እና ዘወትር በታላላቅ መንፈሳዊ በዓላት በተለይም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት የገና በዓል ቀን እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በተነሳበት የትንሳኤ ቀን ልማዳዊ በሆነ መልኩ አንድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በላቲን ቋንቋ Urbi et Orbi በአማሪኛው ለከተማው (ሮም) እና ለዓለም የተሰኘ መልእክት በዓላቱን አስመልክተው እንደ ሚያስተላልፉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሚያዚያ 05/2012 ዓ.ም ረፋዱ ላይ በላቲን ቋንቋ Urbi et Orbi በአማሪኛው ለከተማው (ሮም) እና ለዓለም የተሰኘው ምልእክት በቫቲካን በቅድስት ማርታ ቤት ከሚገኘው ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ውስጥ ሆነው ማስተላለፋቸው የተገለጸ ሲሆን “የኢየሱስ ትንሳኤ የመጨረሻው ቃል ሞት ሳይሆን ህይወት እንደሆነ ይነግረናል” ማለታቸው ተገልጹዋል።
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያስተላለፉትን መልእክት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው እናቀርብላችኋለን ተከታተሉን።
ውድ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!
ዛሬ (ሚያዚያ 05/2012 ዓ.ም) የመላእክት ሰኞ በመባል በሚታወቀው እለት ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ የተነገረው አስደሳች መልእክት በደስታ እንድንሞላ ያደርገናል። በቅዱስ ወንጌል ውስጥ (ማቴ 28፡ 8-15) ሴቶቹ (ማርያም እና መቅደላዊት ማርያም) ኢየሱስ የተቀበረበት መካነ መቃብር ባዶ መሆኑን ባዩ ጊዜ በፍጥነት ተመልሰው እንደ ሄዱ ይናገራል። ነገር ግን ኢየሱስ ራሱ በመንገድ ላይ ተገለጠላቸው: “አትፍሩ፤ ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው፤ በዚያ ያዩኛል” (ማቴ፡ 10) አላቸው። በእነዚህ ቃላት ከሙታን የተነሳው ጌታ ሴቶቹ ለሐዋርያቱ ይህንን መልእክት ያደርሱ ዘንድ ተልእኮ ሰጣቸው። በእርግጥ እርሱ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን በይፋ በሚያከናውንበት ጊዜ እና መከራ በሚቀበልበት ወቅት ሳይቀር በገዛ ፍላጎታቸው ለክርስቶስ ያላቸውን ታማኝነት እና ከፍተኛ ፍቅር በምያስደንቅ መልኩ በአርያነት ሊጠቀስ በሚችል መልኩ ምላሽ ሰጥተው ነበር። አሁን በዚህ መልኩ ለሰጡት ከፍተኛ ትኩረት እና ፍቅር ተገቢ የሆነውን የእሱን ሽልማት አግኝተዋል። ሴቶች ሁል ጊዜም ቢሆን ቀዳሚ ናቸው፣ ከመጀመርያው ጊዜ ጀምሮ ነበሩ፣ ማርያም ከመጀመርያው ጊዜ ጀምሮ ነበረች፣ ሴቶች በመጀመሪያም ነበሩ።
በመጀመሪያ ሴቶቹ፣ ከዚያም በመቀጠል ደቀመዛሙርቱ በተለይም ጴጥሮስ የትንሳኤውን እውነታ ያስተውላሉ። ከተሰቃየ እና በመስቀል ላይ ተስቅሎ ከሞተ በኋላ እንደገና ከሞት እንደሚነሳ ኢየሱስ ደጋግሞ ነግሯቸው ነበር፣ ነገር ግን ደቀመዛሙርቱ ገና አልተረዱም፣ ምክንያቱም ገና አልተዘጋጁም ነበርና። እምነታቸው የትንሳኤ ስጦታ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ብቻ ሊሰጠው የሚችለው ደረጃውን የጠበቀ እምነት ላይ ገና አልደረሰም ነበር።
በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በመጀመሪያ ክፍል ላይ ጴጥሮስ በግልፅ እና በድፍረት “ይህን ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው፤ እኛም ሁላችን ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን” (ሐዋ. 2.32) በማለት በድፍረት ሲናገር እንሰማለን። ይህም “ለእርሱ ራሴን አቀርባለሁ፣ ሕይወቴን ለእርሱ እሰጠዋለሁ” እንደ ማለት ነው። ከዛም ነፍሱን ለእርሱ ይሰጣል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ክርስቶስ ከሞት መነሳቱን የሚገልጽ አዋጅ በሁሉም ስፍራ ተስፋፍቶ በዓለም ማዕዘናት ሁሉ ሳይቀር ይዳረሳል፣ ለሁሉም የተስፋ መልእክት ይሆናል። የኢየሱስ ትንሳኤ የመጨረሻው ቃል ሞት ሳይሆን ህይወት እንደሆነ ይነግረናል። አንድያ ልጁን ከሙታን እንዲነሳ በማድረጉ እግዚአብሔር አብ ለሁሉም ሰው ፍቅሩን እና ምህረቱን ሙሉ በሙሉ ገልጹዋል።
ክርስቶስ ከሙታን ከተነሳ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ በልበ ሙሉነት፣ አስጨናቂ በሚባሉ ጊዜያትን ሳይቀር በእምነት እና በራስ የመተማመን ስሜት መመልከት ይቻላል ማለት ነው። በቃላት እና ከሁሉም በላይ ደግሞ በሕይወት ሳይቀር ምስክርነት በመስጠት እንድንሰብክ የተጠራነው የ‹ፋሲካ› መልእክት እዚህ አለ። ይህም በቤታችን እና በልባችን ውስጥ ሳይቀር ሊመላለስ የሚችል አስደሳች የሆነው “ተስፋዬ የሆነው ክርስቶስ ከሙታን ተነስቱዋል” የሚለው መልእክት ነው። ይህ በእርግጠኛነት እያንዳንዱ ምስጢረ ጥምቀት የተቀበለ ሰው እምነት ያጠናክራል፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ታላቅ መከራ እና ችግር እየገጠማቸው ያሉትን ሰዎች ያበረታታል።
የልጁዋን የኢየሱስ ሞት እና ትንሳኤ በዝምታ መስካሪ የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ የመዳን ምስጢር ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖረን ትርዳን፣ በእምነት የተቀበልነው ሕይወትን መለወጥ ይችላል። ለሁላችሁም የማስተላልፈው የፋሲካ በዓል መልእክቴ ይህ ነው። ‘የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበለሽ’ የሚለውን ጸሎት በመድገም እናታችን ለሆነችው ለእርሷ ይህንን በአደራ እንስጣት ።