ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ቫይረስ ሳይሆን የፍቅር ወረርሽኝ እንዲይዘን እንፍቀድ አሉ!
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በቤተ ውስጥ የመቀመጥ ግዴታ በነበረበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የተለያዩ የማሕበራዊ የመገናኛ መስመሮችን ተጠቅመው ያሳርጉ በነበረው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያሰሟቸውን ስብከቶች ቫቲካን በመጽሐፍ መልክ ያፋ ማደረጓ ተገለጸ።
የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
የቫቲካን የሕትመት ውጤቶች ክፍል እንደ ገለጸው በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያሳርጓቸው በነበሩ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ በእየለቱ ያደረጓቸውን ስብከቶች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አስገዳጅ በሆነ ምክንያት በቤት ውስጥ ለመቀመጥ ተገደው ለነበሩ ምዕመናን መጽናኛ ይሆን ዘንድ ያደረጓቸው ስብከቶች በመጽሐፍ መልክ መቅረቡን የቫቲካን የሕትመት ወጤቶች ቢሮ ይፋ ማደርጉ ተገልጿል።
በኮርና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለታመሙ፣ በገለልተኛ ስፍራ ብቻቸውን እንዲቀመጡ ለተገደዱ ሰዎች፣ ወይም በማንኛውም ምክንያት ከቤታቸው እንዳይወጡ ተደርገው ለነበሩ ሰዎች ያላቸውን ቅርበት ለመግለጽ በማሰብ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አደጋ እስኪቀንስ ድረስ በእየለቱ መስዋዕተ ቅዳሴ በማሳረግ ሕዝቡን ለማጽናናት የሚያግዙ አስተንትኖዎችን ያደርጉ እንደ ነበረ ይታወሳል።
እ.ኤ.አ. ከመጋቢት 9 እስከ ግንቦት 18/2020 ዓ.ም ድረስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በየቀኑ ጠዋት በማለዳ በማሕበራዊ የመገናኛ አውታሮች አማካይነት በዓለም ዙሪያ ይሰራጭ የነበረ መስዋዕተ ቅዳሴ ማደረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ፣ ምንም ዓይነት የሃይማኖት ልዩነት ቢኖራቸውም ፣ የተለያዩ የቫቲካን ሚዲያ ጣቢያዎችን እና ሌሎች የሬዲዮ እና ቴሌቪዥኖች ጣቢያዎችን ወይም ዲጂታል መድረኮችን በመጠቀም መከታተል እና ማዳመጥ ችለው እንደ ነበረ ይታወሳል።
የርዕሰ ሊቃና ጳጳሳቱ ስብከት እና ዲጂታል እትመት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያሳረጓቸው መስዋዕተ ቅዳሴዎች እና ስብከቶቻቸው በቫቲካን ዜና እና በዩቱብ ጣቢያ እና በድረ ገጾች በኩል ለዓለም ተደራሽ ሆነዋል። የአማርኛ እና የትግረኛ ቋንቋዎችን ጨምሮ ስብከቶቻቸው በ39 የተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉመው ነበር።
በመከራ ጊዜ ጠንካራ ሆኖ መገኘት በሚል አርእስይ ይፋ የሆነው ይህ መጽሐፍ ኅብረት በቤተክርስቲያን ውስጥ ያስፈልጋል በችግር ወቅት እውነተኛ ድጋፍ ማደረግ ይገባል የሚሉ እንድምታዎችን አቅፎ የያዘ መጽሐፍ ነው።
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከተጠቀሱት የቅዱነታቸው ስብከቶች መካከል ዓርብ መጋቢት 18/2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 2 ሰዓት (በሮም የሰዓት አቆጣጠር ደግሞ ከምሽቱ 18፡00) ላይ ቅዱስነታቸው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ደጃፍ ላይ ሆነው ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በመመልከት የዓለማችን ስጋት የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዲቆም በማለት ቅዱስነታቸው ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ጸሎት አቅርበዋል። የሰው ልጅ በሙሉ ከሚገኝበት ፈተና መውጣት እንዲችል ምዕመናን በጽኑ እምነት ተስፋን በመያዝ ሕይወቱን እንዲገፋ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው፣ ዓርብ መጋቢት 18/2012 ዓ. ም. በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 2:00 ላይ፣ ከሮም ከተማ ሕዝብ እና ከመላው የዓለም ሕዝብ ጋር በመንፈስ በመተባበር የቅዱስ ቁርባን ቡራኬ ጸሎትን አቅርበው፣ ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ደጃፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቡራኬ ይድረሳችሁ በማለት ቡራኬአቸውን አስተላልፈዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ደጃፍ በተከናወነው የቅዱስ ቁርባን ቡራኬ ጸሎት ላይ የቅዱስ ወንጌል ንባብ ቀርቧል።
‘ያ ቀን በመሸ ጊዜ፣ ‘ወደ ማዶ እንሻገር’ አላቸው። እነርሱ ሕዝቡን ትተው በጀልባዋ ውስጥ እንዳለ በዚያው ይዘውት ሄዱ፤ ሌሎች ጀልባዎችም አብረውት ነበሩ። በዚህ ጊዜ ኀይለኛ ዐውሎ ነፋስ ተነሣ፤ ማዕበሉም ውሃ እስኪሞላት ድረስ ጀልባዋን ያናውጣት ነበር። ኢየሱስ ግን ትራስ ተንተርሶ ከጀልባዋ በስተ ኋላ በኩል ተኝቶ ነበር። እነርሱም ቀስቅሰውት፣ ‘መምህር ሆይ፤ ስናልቅ አይገድህምን?’ አሉት። እርሱም ተነሥቶ ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም፣ ‘ጸጥ፣ ረጭ በል!’ አለው። ነፋሱም ጸጥ፣ ረጭ አለ፤ ፍጹምም ጸጥታ ሆነ። ደቀ መዛሙርቱንም፣ ‘ስለ ምን እንዲህ ፈራችሁ? እስከዚህ እምነት የላችሁምን?’ አላቸው። እነርሱም በፍርሀት ተውጠው እርስ በርሳቸው፣ ‘ነፋሱም ሞገዱም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?’ ተባባሉ። (ማር. 4፡35-41)
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከማር. 4፡35-41 የተነበበውን የቅዱስ ወንጌል ክፍል መሠረት ያደረገ አስተንትኖአቸውን ለመላው ካቶሊካዊ ምዕመናን አቅርበዋል። የቅዱስነታቸው አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ይነበባል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።
"አሁን ሲነበብ የሰማነው የቅዱስ ወንጌል ክፍል “በመሸ ጊዜ” (ማር. 4:35) በማለት ይጀምራል። ለሳምንታት ያህል ጨለማ ዎርሶናል። አደባባዮቻችን፣ ጎዳናዎቻችን እና ከተሞቻችን በድቅድቅ ጨለማ ተውጠዋል። ሕይወታችንን በሙሉ ጨለማ ተቆጣጥሮታል። አካባቢያችን በሚያስጨንቅ ጸጥታ እና ባዶነት ተውጧል። ከሰዎች ፊት መረዳት ይቻላል። የጠፋን ይመስል ፍርሃት አስጨንቆናል። በወንጌል ውስጥ ታሪክ እንዳየናቸው ደቀ መዛሙርት ያላሰብነው እና ያልጠበቅነው በኃይለኛ ዐውሎ ነፋስ መቶናል። በአንድ ጀልባ ላይ መሳፈራችንን ተገነዘብን። እያንዳንዳችን ምን ማድረግ እንድሚገባን ግራ ተጋብተናል። አንዳችን ለአንዳችን እንደምናስፈልግ እናውቃለን። ሁላችንም በአንድ መደዳ ቆመን እንጣራለን፣ አንዱ ሌላውን እንዲያጽናና እንፈልጋለን። ሁላችንም ይህን በመሰለ ሁኔታ ላይ እንገኛለን። ደቀ መዛሙርት ተጨንቀው በአንድ ድምጽ ‘መምህር ሆይ፤ ስናልቅ አይገድህምን?’ እንዳሉት ሁሉ (ማር. 4:38) እኛም ብቻችን ምንም ማድረግ እንደማንችል ነገር ግን በኅብረት ማሰብ እንዳለብን ተገንዝበናል።
በዚህ ታሪክ ውስጥ ራሳችንን ማግኘት ቀላል ነው። ለመረዳት የሚዳግተን ኢየሱስ ያሳየው ባሕርይ ነው። ደቀ መዛሙርቱ በድንጋጤ ብዛት ተረብሸው ሲጮኹ እርሱ ግን ቀድሞ በሚሰምጥ የጀልባ ጥግ ቆሞ ነበር። ዐውሎ ነፋሱ ጀልባዋን ሲያናውጣት እርሱ ግን በአባቱ ኃይል በመተማመን በስተኋላ በኩል ተኝቶ ነበር። በወንጌል ታሪክ ውስጥ ኢየሱስ ሲተኛ ያየነው በዚህ ጊዜ ብቻ ነበር። ወጅቡ ካለፈ እና ወሃውም ከቆመ በኋላ ከተኛበት ነቅቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዞሮ በነቀፋ ድምጽ፥ ‘ይህን ያህል ለምን ፈራችሁ? እምነት የላችሁምን?’ አላቸው (ማር. 4:40)።
እስቲ ለመረዳት እንሞክር። ደቀ መዛሙርቱ የሚጎድላቸው ነገር ምንድር ነው? ኢየሱስም እንዳላቸው የጎደላቸው እምነት ነውን? በእርሱ ማመን ትተዋል እንዳባል ከዐውሎ ነፋሱ አደጋ እንዲያተርፋቸው ለምነውታል። ሲጠሩትም፥ ‘መምህር ሆይ’! ብለው በመጥራት ስንጠፋ ዝም ትላልህን? አሉት። (ማር. 4:38) ዝም ትላልህን ባሉ ጊዜ ኢየሱስ ትኩርት ያልሰጣቸው መሰላቸው። እኛን እና ቤተሰቦቻችንን የሚጎዳን ነገር ቢኖር “ስለ እኔ ምንም አያስጨንቅህም?” ሲባል መስማት ነው። በልባችን ውስጥ ቁስልን የሚፈጥር እና ዕውሎ ነፋስ የሚያስነሳ አባባል ነው። ኢየሱስንም የሚያስደነግጥ አባባል ነው። ምክንያቱም እርሱ ከሁሉ በላይ ለእኛ የሚጨነቅ አምላክ ነው። ደቀ መዛሙርቱ በጠሩት ጊዜ ከአደጋው በማዳን ብርታትን ሰጣቸው።
አውሎ ነፋሱ የእኛን ደካማነት እና ኑሮአችንን የመሠረትንበትን የሐሰት መተማመኛችንን፣ ዕለታዊ ውጥኖቻችንን፣ ልማዳችንን እና ማድረግ ያለብንን ትተን ቅድሚያ የሰጣናቸውን ነገሮች ሁሉ ግልጽ አድርጎታል። ሕይወታችንን እና ማኅበረሰባችንን በእውነት ሊያሳድግ እና ሊደግፍ የሚችለውን ነገር ምን ያህል ወደ ጎን እንዳደረግን አሳይቶናል። ዐውሎ ነፋሱ ሃሳባችንን በማጋለጥ የሕዝባችንን ህይወት ሊቀይረው የሚችለውን ቀዳሚ ነገር መዘንጋታችንን ይፋ አድርጓል። ከእኛ በፊት የነበሩ አባቶቻችን የተከተሉትን መንገድ፣ ከእነርሱ ጋር ያለንን ትስስር ጠብቀን ከመያዝ ይልቅ ለሕይወታችን መልካም እና አስፈላጊ ባልሆነው ነገር ላይ እንድናተኩር አድርጎናል። አካላችንን ለሚጎዱ ተዋሲያን ራሳችንን አሳልፈን ሰጥተናል።
ዐውሎ ነፋሱ ስለ ራሳችን ያለን የተሳሳቱ አመለካከቶችን በማጉላት በአንድ ወቅት ክብር የተቸረለትን የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት ባሕል እየጠፋ እንዲሄድ ተደርጓል።
‘ይህን ያህል ለምን ፈራችሁ? እምነት የላችሁምን?’ ጌታ ሆይ፣ ይህ ቃልህ ዛሬ እኛን አንድ ነገር ያሳስበናል። በዚህ ቃልህ እኛ ከምንወድህ በላይ ትወደናለህ። እኛ ራሳችንን ከፍ በማድረግ፣ ሁሉን ነገር ለማከናወን አቅም እንዳለን በመቁጠር በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ፊት እንገስግሳለን። በስግብግብነታችን ምክንያት ትርፍን ለመሰብሰብ እንቸኩላለን። ያንተን ተግሳጽ ችላ ብለናል። በዓለም ዙሪያ በሚነሱ ጦርነቶችን እና ፍትህ አልባነትን ልባችን አልተረበሸም። የድሆችን ጩኸት ለማዳመጥ እና የምድራችንን ሕመመ ለማስታገስ ችላ ብለናል። በሕመም ላይ በምትገኝ ምድራችን በጤና እንኖራለን ብለን አስበናል። ነገር ግን አሁን በሚናወጥ ባሕር ውስጥ እንገኛለን። “አቤቱ ጌታ ሆይ አድነን” በማለት ድምጻችንን ወደ አንተ እናነሳለን።
‘ይህን ያህል ለምን ፈራችሁ? እምነት የላችሁምን?’ ጌታ ሆይ! አንተ ወደ እምነት ትጠራናለህ። በሕያውነትህ ብዙም ባናምንም ወደ አንተ እንቀርባለን፣ አንተን ማመን እንፈልጋለን። ይህ የዓብይ ጾም እንድንለወጥ ያሳስበናል። በሙሉ ልብ ወደ አንተ እንድንቀርብ ይጠራናል። (ኢዩ. 2፡12) ይህን የዓብይ ጾም የሙከራ ወቅት አንተን የምንመርጥበት ጊዜ እንዲሆን ጥሪ በማቅረብ ላይ ትገኛለህ። ይህ ጊዜ ያንተ የፍርድ ጊዜ ሳይሆን ለእኛ የተሰጠን የምርጫ ጊዜ ነው። የሚጠቅመንን እና የማይጠቅመንን ለይተን የምንመርጥበት ጊዜ ነው። ይህ ጊዜ ወደ አንተ እና ወደ ሌሎች የምንመለስበት ጊዜ ነው። ምንም እንኳን በፍርሃት የተያዙ ቢሆንም ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ በመሆናቸው ለመገዳችን መልካም ምሳሌ የሚሆኑትን እንፈልጋለን። ይህም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የታገዘ በድፍረት ራስን የመካድ ዘዴ ነው። ሕይወታችን በተረሱት እና ስማቸው በማይነሳ፣ ዝና በሌላቸው ሰዎች አማካይነት የሚዋጀው በመንፈስ ቅዱስ በሚኖረን ሕይወት ነው። እነዚህ ሰዎች ያለ ምንም ጥርጥር አሁን በምንገኝበት ወሳኝ ጊዜ በመዝገባቸው በመጻፍ ላይ ይገኛሉ። የህክምና ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ የገበያ ማዕከል ውስጥ ሰራተኞች፣ የጽዳት ሰራተኞች፣ የሰው ልጅ ተንከባካቢዎች፣ የማመላለሽ ሰራተኞች፣ ሕግ እና ሥርዓት አስከባሪዎች፣ በጎ ፈቃደኞች፣ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት እንዲሁም ሌሎች በሙሉ የሰው ልጅ ብቻውን የትም መድረስ እንደማይችል ተገንዝበዋል። በርካታ ሰዎች በስቃይ ላይ በሚገኙበት ባሁኑ ወቅት፣ እውነተኛ የሰው ልጅ እድገት ምንጭ እየተፈለገ ባለበት ባሁኑ ጊዜ እንዲህ የሚል የኢየሱስ ክርስቶስ ክህነታዊ ጸሎት እናስታውሳለን፥ ‘እኔም የምለምነው ፣ ሁሉም አንድ እንዲሆኑ ነው፤ እንዲሁም አባት ሆይ! አንተ በእኔ እንዳለህ፣ እኔም ባንተ እንዳለሁ እነርሱም በእኛ እንዲሆኑ ነው፤ አንተ እንደላክኽኝ ዓለም እንዲያምን ነው’ (ዮሐ. 17:21)። በየቀኑ ምን ያህል ሰዎች ፍርሃትን በማስወገድ ሃላፊነትን ተሸክመው በትዕግስት እና በተስፋ ይኖራሉ? ምን ያህል አባቶች እና እናቶች፣ አረጋዊያን እና መምህራን በዕለታዊ ሕይወታቸው ጥሩ ምሳሌ በመሆን ሕጻናት ችግራቸውን የሚያልፉበትን መንገድ በጸሎት እንዲያገኙ ያግዛሉ? ምን ያህል ሰዎችስ አቅም የፈቀደውን ያህል አውጥተው በመለገስ ሌሎችን በመርዳት ላይ ይገኛሉ? ጸሎት እና አግልግሎት ድል የሚገኝባቸው መሣሪያዎች ናችው።
‘ይህን ያህል ለምን ፈራችሁ? እምነት የላችሁምን?’ እምነት የሚጀምረው መዳን እንደሚያስፈልገን ስንገነዘብ ነው። ብቻችን ራስን ችለን መቆም አንችልም። የቀድሞ ተጉዦች ኮከብን አይተው እንደሚጓዙ እኛም እግዚአብሔርን እንፈልጋለን። ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ሕይወታችን ውስጥ እንዲገባ እንጋብዘው። እርሱ ድልን እንዲቀዳጅ ፍርሃታችንን በሙሉ ለእርሱ እንስጠው። እንደ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ጋር ካለ ጀልባችን አይሰምጥም። ነገሮችን በሙሉ ወደ መልካም የሚለውጥ የእግዚአብሔር ኃይል ነው። በተረበሽን ጊዜ ሰላምን የሚሰጥ እግዚ አብሔር ስለሆነ አንሞትም።
በችግራችን ጊዜ ጠንክረን በመቆም፣ ሁሉ ነገር የጠፋ በሚመስለን ባሁኑ ሰዓት ኃይል የሚሰጠንን አንድነት እና ተስፋ እንድንሰንቅ እግዚአብሔር ይጠይቀናል። በብርሃነ ትንሳኤው እምነት እንድንበረታ እግዚአብሔር ይረዳናል። መከታ በሆነን መስቀሉ ድነናል፤ መሪያችን በሆነው መስቀል ድነናል፤ ተስፋችን በሆነው መስቀሉ የተፈወስን በመሆናችን ከአዳኝ ፍቅሩ ማንም ሊለየን አይችልም። ተለያይተን በስቃይ ውስጥ ስንገኝ ብዙ ማጣትን ተመልክተናል። ከሞት ተነስቶ ከእኛ ጋር የሚገኘውን የኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ዜና እንስማ። በመስቀል ላይ ሆኖ ዘለዓለማዊ ሕይወት እንድንቀበል እግዚአብሔር ይጠይቀናል። ሊጠፋ የተቃረበውን መብራት አናጥፋ። (ኢሳ. 42:3) ተስፋችን በድጋሚ እንዲቀጣጠል እናድርግ።
የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል መያዝ ማለት በዚህ ጊዜ የሚያጋጥሙ መከራዎችን በትዕግስት መቀበል ማለት ነው። ለሥልጣን እና ለምድራዊ ሃብት ያለንን ምኞት ወደ ጎን አድርገን መንፈስ ቅዱስ ለሚያሳየን ጥበብ ሥፍራን እናዘጋጅ። ይህ ማለት ደግሞ እያንዳንዳችን አንዱ ሌላውን በእንግድነት መቀበልን፣ ወንድማማችነትን እና አንድነትን ለመፍጠር አዲስ መገድን ለማግኘት መጠራታችንን ማወቅ ማለት ነው። ኃይል የሚሰጠንን ተስፋን አጥብቀን ይዘል እራሳችንን እና ሌሎችን ለማገዝ የምንችልበትን መንገድ እንድንጓዝ በመስቀሉ ድነትን አግኝተናል። ከፍርሃት ነጻ የሚያደርገንን የእምነት ኃይል አጥብቀን እንያዝ።
‘ይህን ያህል ለምን ፈራችሁ? እምነት የላችሁምን?’ ወድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ከዚህ የቅዱስ ጴጥሮስ ጠንካራ እምነት ከሚገለጥበት ሥፍራ፣ የሕዝቦች ፈውስ በሆነች በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በአደራ ላቀርባችሁ እወዳለሁ። ሮምን እና መላውን ዓለም ከሚይዘው ከቅዱስ ጴጥሮስ አደባባብ የእግዚአብሔር ቡራኬ በእያንዳንዳችሁ ላይ ይሁን። ጌታ ሆይ ዓለምን ባርክ፤ ለስጋችን ጤናን፤ ለልባችንም ዕረፍትን ስጠው፤ እንዳንፈራ ብርታትን ተሰተናለህ፤ ነገር ግን እምነታችን ደካማ ከመሆኑ የተነሳ በፍርሃት ውስጥ እንወድቃለን። ነገር ግን ጌታ ሆይ አንተ ለዐውሎ ነፋስ አሳልፈህ አትሰጠንም። ‘አትፍሩ’ በለን (ማቴ. 28:5)። ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ሆነን የሚያስጨንቀንን ሃሳብ ሁሉ በአንተ ላይ እንጥላለን”።