የአቶሚክ ኃይልን ለጦርነት መጠቀምና ይህንን መሣሪያ ማከማቸት ሥነ ምግባር የጎደለው ተግባር ነው!
እ.አ.አ. በነሐሴ 6/1945 ዓ.ም የዛሬ 75 አመት ገደማ ማለት ነው ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ በመባል በሚታወቁ ሁለት ያጃፓን ከተሞች ላይ ሁለት የአቶሚክ ቦንቦች ተጥለው ሂሮሺማ እና ናጋሳኪን ማጥፋታቸው ይታወሳል። የአለማችንን ታሪክ በከፍተኛ ሁኔታ ካዛቡ አካሄዶች መካከል እና የዓለማችን ሕዝቦች ካበሳጩ ከእነዚያ ቀናት ጀምሮ በዓለም ዙሪያ የኒውክለር የጦር መሳሪያ አገልግሎት ላይ እንዳይውል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ የሆነ ጥረት ስታደርግ መቆየቷ ይታወሳል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ እና አዘጋጅ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ
አሰቃቂው እና በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ነፍስ የቀጠፈው እና ብዙዎችን ለስደት ዳርጎ የነበረው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ እ.አ.አ ከ1958-1978 ዓ.ም ድረስ በነበረው የታሪክ ሂደት ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ይንጸባረቅ በነበረው ምራባዊያን እና ምስራቃዊያን በሚል ጎራ ለሁለት በተከፈለችሁ ዓለማችን ምራቡን እንደ ባለጸጋ፣ ምስራቁን ደግሞ አንደ ድሃ በመቁጠር ርዕዮተ ዓለማዊ ጦርነቶች በነበሩበት ወቅት በወቅቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ዮሐንስ 23ኛ የሁለተኛውን የቫቲካን ጉባሄ በመጥራት “ሰላም በምድር ላይ ይሁን” በሚል ጭብጥ ዙሪያ ላይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳትን ያሳተፈ ጉባሄ እንዲደረግ ማድረጋቸው ይታወሳል። በወቅቱ ለነበረው ማኅበራዊ ቀውስ በተወሰነ መልኩም ቢሆን እንኳን ማኅበራዊ መግባባት እና መፍትሄ እንዲመጣ፣ አውዳሚ እና ጅምላ ጨራሽ የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን ከዓለማችን ማስወገድ እንደ ሚገባ የሚገልጽ ሐዋሪያዊ መልእክት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በተለይም ደግሞ በወቅቱ ምራባዊያን እና ምስራቃዊያን የሚል መጠሪያ ተስጥቶዋቸው በሁለት ጎራ ተፋጠው በነበሩ የዓለማችን አገራት ሳቢያ አለማችን ለከፍተኛ ጦርነት በመጋለጧ፣ አልፎም ተርፎም የቀዝቃዛው ጦርነት በመባል በሚታወቀው ሂደት ውስጥ በተለይም አሜርካ እና ራሻ ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ ገብተው ጅምላ ጨራሽ የሚባሉ የኒውክለር የጦር መሳሪያን ለማምረት በእሽቅድድም እንደ ነበሩ ይታወሳል። በወቅቱ የካቶሊክ ቤተ ክርርስቲያን በላቲን ቋንቋ “Pacem in terris” በአማሪኛው “ሰላም በምድር ላይ ይሁን” በሚል አርእስት ለንባብ ባበቃችሁ ሐዋሪያዊ መልእክት ሁለቱ የዓለማችን ኃያላን የሚባሉ ሀገራት ለማንም የማይበጀውን የጋራ መኖሪያ የሆነቺውን ዓለማችንን በጅምላ የሚያጠፈ የጦር መሳሪያዎችን ያስወግዱ ዘንድ በተደጋገሚ የሰላም ጥሪ በማቅረብ ሁለቱ ኃያላን የሚባሉ ሀገራት ፍጥጫቸውን አቁመው ወደ ሰላም እንዲመለሱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ አስተዋጾ ማደረጓ ይታወሳል።
ከኅዳር 09-16/2012 ዓ.ም ድረስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በታይላንድ እና በጃፓን በቅደም ተከተል 32ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን “ሕይወትን ከጉዳት እና ከሞት አደጋ እንታደግ” በሚል መሪ ቃል ከኅዳር 12-16/2012 ዓ.ም ድረሰ የ32ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሁለተኛ መዳረሻ አገር ወደ ሆነችው ጃፓን ማቅናታቸው ይታወሳል።
ቅዱስነታቸው በጃፓን በነበራቸው የአራት ቀን ቆያት የጃፓን ዋና ከተማ የሆነችውን ቶክዮን ጨምሮ፣ በሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወቅት በኒውክለር የጦር መሣርያ ድብደባ ምክንያት ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸውን እና እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ የሰው ልጆች ሕይወት የተቀጠፈበት አደጋ ተከስቶ የነበረባቸውን ናጋሳኪ እና ሂሮስሺማን መጎብኘታቸው ይታወሳል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ በጃፓን ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት የጀመሩት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ስፍራዎች አንዷ በሆነቺው ሄሮሽማ እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው በእዚያው “የሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ” በመባል በሚታወቀው የመታሰቢያ ስፍራ ለተገኙ ሕዝቦች ባደርጉት ንግግር እንደ ገለጹት “የአቶሚክ የጦር መሣሪያ ኃይልን ለጦርነት መጠቀምና ይህንን መሣሪያ ማከማቸት ሥነ ምግባር የጎደለው ተግባር ነው” በማለት በአጽኖት መግለጻቸው ይታወሳል።
በጃፓን በነበራቸው የመጀመሪያው ቀን ሐዋርያዊ ጉብኝት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “የሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ” ሥፍራን በጎበኙበት ወቅት ይህ “የሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ” ስፍራ ሞትና ሕይወት ፣ ኪሳራ እና ዳግም ልደት ፣ ሥቃይና ርህራሄ የተገናኙበት ስፍራ እንደሆነ” መግለጻቸው ይታወሳል። ለጦርነት ዓላማ አቶሚክ ኃይል መጠቀምና ማከማቸት በራሱ ሥነ-ምግባር የጎደለው ተግባር መሆኑን ከታሪክ መማር እንደ ሚቻል ቅዱስነታቸው ጨምረው መግለጻቸው ይታወሳል።
እ.አ.አ በነሐሴ 6/1945 ዓ.ም 8፡15 ደቂቃ ላይ በሂሮሺማ ከተማ ላይ በተጣለው የመጀመሪያው አቶሚክ ቦንብ በወቅቱ ከተማይቱን ሙሉ በሙሉ እንድትወድም ማድርጉ የሚታወስ ሲሆን ከእዚህም ጋር በተያያዘ መልኩ በእዚህ አቶሚክ ቦንብ አማካይነት በቅጽበት ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ሲሆን ከእዚያም በመቀጠል ደግሞ የአቶሚክ ቦንቡ ባደርሰው የጨረር አደጋ ቀስ በቀስ የ 70 ሺህ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ይታወሳል።
ከእዚህ ከተጣለው የአቶሚክ ቦንብ መሣርያ ፍንዳታ የተረፈው ብቸኛው ሕንፃ የጄንባኩ ዶም በመባል የሚታወቀው የፈረሰ ሕንጻ ሲሆን ይህ ሕንጻ በሰው ልጆች ላይ እና በአጠቃላይ በሰብዓዊነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እና ውድመት ያስከተለ እጅግ አስከፊ የሆነ አደጋ መሆኑን ለማስታወስ፣ ይህ ስፍራ ዛሬ በሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ ፓርክ እምብርት ላይ ቆሞ ይታያል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኅዳር 14/2012 ዓ.ም ይህንን የሰላም መታሰቢያ ሥፍራ ለመጎብኘት ወደ እዚያው ማቅናታቸው የሚታወስ ሲሆን በሂሮሽማ በሚገኘው የጄንባኩ ዶም በመባል የሚታወቀው የፈረሰ ሕንጻ ሥር ሆነው ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል። በወቅቱ ቅዱስነታቸው ይህንን በአቶሚክ ቦንብ መሣሪያ አማካይነት የተቃጣው አደጋ በተመለከተ ሲገልጹ “በእዚህ ነጎድጓድ መብርቅ በመሰለ ከፍተኛ ጥቃት እና የእሳት ፍንዳታ፣ ብዙ ወንዶች እና ሴቶች ፣ ብዙ ህልሞች እና ተስፋዎች ጠፍተዋል፣ ጥለውት ያለፉት ጥላ እና ዝምታ ብቻ ነው፣ በቅጽበት ሁሉም ነገር በሞት ጥላ ተውጦ ነበር” ማለታቸው ይታወሳል።
የጥቃቱ ሰለባዎች እና ከአደጋው የተረፉ ሰዎች
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ወደ እዚያው ሥፍራ ያቀኑት በእዚህ አሳዛኝ አደጋ ተጎጅ ለሆኑ ሰዎች ያላቸውን ክብር ለመግለጽ እና እነርሱ በወቅቱ የነበራቸውን ጥንካሬ ምንጭ ለመገንዘብ እንደ ሆነ በወቅቱ የገለጹ ሲሆን “አሁን በሕይወት ለሌሉ እና የእዚህ አደጋ ሰላብ የሆኑ ሰዎችን ጩኸት እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ማሰማታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል። የእዚህ የአቶሚክ ቦንብ ጥቃት ሰለባ የነበሩ ሰዎች “ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ፣ የተለያዩ ስሞች የነበሯቸው፣ የተወሰኑት ደግሞ የተለያዩ ቋንቋዎችን ይናገሩ እንደ ነበረ፣ ሆኖም ሁሉም በዚህች ክፉ እጣ ፈንታ በአንድነት ገፈት ቀማሽ ሆነዋል ፣ በዚህች ሀገር ታሪክ ላይ ብቻ ሳይሆን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ሳይቀር እስከ መጨረሻው ድረስ ዘለቄታዊ የሆነ ምልክት ጥሎ ያለፈ ክስተት ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
የሰላም ተጓዥ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጨምረው እንደ ገለጹት እርሳቸው በበኩላቸው ወደ እዚህ ስፍራ የመጡት “የሰላም ተጓዥ” በመሆን “የጥላቻ እና የግጭት ሰለባዎች የሆኑትን ድሆች ጩኸት ይዘው ወደ እዚያ ስፍራ መምጣታቸውን” በወቅቱ የተናገሩ ሲሆን “አሁን እኛ ባለንበት ጊዜ ውስጥ እያደገ የመጣውን ውዝግብ እና ጭንቀት የሚሰብኩ እና ሕዝቡን የሚያስጨንቁ፣ የእዚህ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ድምፅ አልባ” የሆኑ ሰዎችን ድምጽ ለማስተጋባት ጭምር እንደ ሆነ ገልጸው ነበር። “የሰውን ልጅ አብሮ የመኖር ሕልውና አደጋ የሚጥሉ ተቀባይነት የሌላቸው ኢፍትሃዊ የሆኑ ተገባሮች እና በደሎች፣ የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን መንከባከብ አለመቻላችን፣ በተጠናከረ መልኩ በቀጣይነት አየተካሄዱ የሚገኙት በጦር መሣርያ የታገዙ ግጭቶች ለሰላም ዋስትና የማይሰጡ ተግባራት በመሆናቸው የተነሳ” እነዚህን እኩይ ተግባራት ለማውገዝ ጭምር ነው ወደ አዚህ ስፋር የመጣሁት ብለዋል።
የኑክሌር ጦርነት ሥነ ምግባር የጎደለው ነው
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን ንግግር በቀጠሉበት ወቅት በድጋሚ እንደ ተናገሩት “የአቶሚክ ኃይልን ተጠቅሞ ጦርነት ማካሄድ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ በሰው ልጆች ክብር ላይ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱ የጋራ መኖርያ ቤታችን በሆነች በምድራችን ላይ የሚፈጸም በደል ነው፣ የአቶሚክ ኃይል ለጦርነት መጠቀም ሥነ ምግባር የጎደለው ተግባር እንደመሆኑ መጠን፣ የአቶሚክ የጦር መሥርያ አምርቶ ማከማቸት በራሱ ሥነ ምግባር የጎደለው ተግባር ነው” በማለት የተናገሩት ይታወሳል። “ስለሰላም ብቻ በማውራት ሰላምን ግን በተጨባጭ በምድር ላይ በሚኖሩ ሕዝቦች መካከል ለማምጣት ባለመቻላችን ምጪው ትውልድ በእኛ ላይ እንደ ሚፈርድ” በወቅቱ የተናገሩት ቅዱስነታቸው አክለውም “ሰላም በእውነት ላይ የተመሠረተ ፣ በፍትህ የተገነባ ፣ በልግስና የተሟላ እና ነጻነትን የሚያስገኝ መሆን አለበት” ማለታቸው ይታወሳል።
በእጆቻችን ላይ የሚገኙ የኒውክለር የጦር መሣሪያዎችን እናስወግድ
“ይበልጡኑ ፍትሃዊ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ መገንባት ከፈለግን በእጆቻችን ላይ የሚገኙትን የኒውክለር የጦር መሣሪያዎችን ማስወገድ ይኖርብናል” በማለት በንግግራቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው “ግጭቶችን ለመፍታት እና ለግጭቶች መፍትሄ ለመስጠት የኑውክሌር ጦርነት መሳሪያ ይህንን ስጋት ለመቀረፍ የሚያስችል ሕጋዊ የሆነ መስመር ነው ብለን በማሰብ የኒውክሌር የጦር መሳሪያዎችን ለማጋበስ በምናደርገው ሩጫ የተነሳ እንዴት ሰላምን ማረጋገጥ እንችላለን?” በማለት ቅዱስነታቸው ጥያቄ አንስተው እንደ ነበረ ይታወሳል። “እውነተኛ ሰላም የሚረጋገጠው የጦር መሳሪያዎችን በማስወገድ ብቻ አይደለም ፣ ምክንያቱም ሰላም ማለት የጦርነት አለመኖር ብቻ ማለት ስላልሆነ! በአንጻሩ ሰላም ማለት ከታሪክ እንደ ተማርነው እና እንደ ተረዳነው የፍትህ፣ የልማት፣ የአንድነት፣ የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን መንከባከብ እና የጋራ ተጠቃሚነትን ማስፈን” ማለት በመሆኑ የተነሳ ጭምር ነው ማለታቸው ይታወሳል።
አስታውሱ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉን ንግግር በቀጠሉበት ወቅት ሦስት ሥነ ምግባራዊ እሳቤዎችን ማስታወስ እንደ ሚገባ በገለጹበት ወቅት እንደ ተናገሩት “ማስታወስ ፣ አብሮ መጓዝ ፣ መንከባከብ” የሚሉትን ሥነ ምግባራዊ እሳቤዎችን ያመላከቱ ሲሆን በተጨማሪም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አጽኖት ሰጥተው እንደ ተናገሩት “የአሁኑ እና የወደፊቱ ትውልድ በእዚህ ስፍራ ምን እንደ ተካሄደ እንዳያስታወሱ ማደረግ አንችልም” በማለት አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል። “ይበልጡኑ ፍትሐዊ እና በወንድማማችነት መንፈስ የተሞላ መጻይ ጊዜ መገንባትን የሚያረጋግጥ እና የሚያበረታታ ያለፉ ክስተቶች ትውስታ አስፈላጊ ነው፣ የወንዶችና የሴቶች ንቃተ ሂሊና በተለይም በአገራት ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱትን ሁሉ የሚያነሳሳ ሰፊ የሆነ የባለፉ ጊዜያትን ሁኔታ የማስታወስ ችሎታ አስፈላጊ ነው፣ ይህንን ለሁሉም ትውልዶች መናገር እና ማስተላለፍ የሚገባን ሕያው ትውስታ ሆኖ ሊቀጥል ይገባዋል፣ መጪው ትውልድ እንደነዚህ ያሉ ክስተቶች በጭራሽ እንዳይከሰቱ ያለፈውን ዘግናኝ ክስተት ማሰብ ያስፈልጋል” ማለታቸው ይታወሳል።
በጋራ ወደ ፊት መጓዝ
“እኛ በመግባባት መንፈስ እና በይቅርታ እይታ በመታገዝ አብረን በጋራ ወደ ፊት መጓዛችንን እንቀጥል” በማለት በወቅቱ ባደረጉት ንግግር የገለጹት ቅዱስነታቸው በመቀጠል “ዛሬ የተስፋን አድማስ ለማስፋት እና በጨለማ በተሞላው ሰማይ ውስጥ ማብራት የሚችል የብርሃን ነጸብራቅ እንዲፈነጥቅ” ሁላችንም በጋራ መሥራት እንደ ሚጠበቅብን ቅዱስነታቸው ጨምረው ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “ተስፋ ማደረግ እንችል ዘንድ ልባችንን እንክፈት፣ የእርቅ እና የሰላም መሳሪያዎች እንሁን” ብለዋል።
“እርስ በእርሳችን አንዱ አንደኛውን መንከባከብ ከቻለ እና አንድ የጋራ የሆነ እጣ ፈንታ እንዳለን ከተገነዘብን ሰላምን እውን ማደረግ ይችላል” በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ዓለማችን፣ እርስ በእርስ እንድትገናኝ እና እንድትተሳሰር ያደረገው አለማቀፋዊነት (globalization) ብቻ ሳይሆን በጋራ እየተጠቀምናት የምንገኘው ምድራችን ጭምር ናት፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዛሬ የተወሰኑ ቡድኖች ወይም ዘርፎች ፍላጎቶችን ወደ ጎን በመተው አንድ የጋራ የወደፊት ሕይወት እንዲኖረን ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ በጋራ መሥራት” ይኖርብናል ማለታቸው ይታወሳል።