2020.08.15 Angelus 2020.08.15 Angelus 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ "የበደሉንን መውቀስ እና መገሰጽ፣ እና ከእኛ በላይ ሲሆን ለእግዚአብሔር መስጠት ይኖርብናል" አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጳጉሜ 1/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ፣ ዘወትር እሁድ በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የሚያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ አቅርበዋል። በስፍራው ለተገኙ ምዕመናን ባደረጉት አስተንትኖ በማቴ. 18፡15-22 ላይ በተጠቀሰው “ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔ እና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ" በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ በማስተንተን “የበደለን ወንድም መውቀስ፣ ማረም እና መመለስ ከእኛ በላይ ሲሆን ለእግዚአብሔር አሳልፎ መስጠት ይኖርብናል" ማለታቸው ተገልጿል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእለቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፥

የቫቲካን ዜና፤

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የዛሬው ቅዱስ ወንጌል አስተምህሮ በማቴ.18:15-22 ላይ ያጠነጠነ ይሆናል፡፡ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል አራተኛው ስለ አማኞች ሕብረት እና ስለ ቤተክርስቲያን ካስተማረው የተወሰደ ነው፡፡ ይህ የወንጌል ክፍል በወንድማማችነት ስለመተራረም እና መወቃቀስ እንዲሁም ሁለት የክርስቲያናዊ አኗኗር አቅጣጫዎች ላይ እንድናሰላስል ይጋብዘናል፡፡ የመጀመሪያው ስለ ሕብረት ነው፤ ይህም አንድነትን ስለመጠበቅ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ እያንዳንዱን ክርስቲያን የሚመለከት ነው፤ ይህም ለሌላው ትኩረት እና ክብርን ስለመስጠት የሚናገር ነው።

የተሳሳተን ወይም የበደለን ወንድም ለማረም፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት መመለስ እንደሚቻል ብልሃትን ያስተምራል፤ ይህም በሦስት መንገድ የተከፈለ ነው፡፡ መጀመሪያ ወንድምህ ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው (ቁ.15)፡፡ ይህም ስለበደሉ የነበረው ወቀሳ በምሥጢር እንዲያዝ ያደርጋል። በመሆኑም በማስተዋል ሳትፈርድ ወንድምህ ስለመተላለፈፉ በደንብ እንዲያውቅ ትረዳዋለህ።

በተለያዩ ምክንያቶች ይህንን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮን መተግበር ቀላል አይደለም። ምክንያቱም የበደለው ወንድማችን ወይም እህታችን ምላሻቸው ጥሩ ላይሆን ይችላል የሚል ፍርሃት ስሚያድርብን ነው፡፡በዚህም የተነሳ በቂ የሆነ በራስ መተማመን ስለማይኖር ነገሩን ፈታኝ ያደርገዋል።በመሆኑም የበደለን ወንድም የመገሰጹ ወይም የመውቀሱ የተቀደሰ ዓላማ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ግቡን ላይመታ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ተስፋ መቁረጥ ግን አያስፈልግም፤ በመሆኑም በጉዳዩ ላይ የሌሎች ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እርዳታ ፈልጎ ማግኘት ተገቢ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ አለ፦ “ወንድምህ ስለበደሉ ብቻችሁን ሆናችሁ ስትወቅሰው ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ” (ማቴ. 18:16)። ይህም በኦሪት ዘዳግ. 19፥15 ላይ ከተጠቀሰው "ስለ በደል ሁሉ፥ ክፉ በማድረግም ስለሠራት ኃጢአት ሁሉ በማንም ላይ አንድ ምስክር አይቁም፤ በሁለት ምስክሮች ወይም በሦስት ምስክሮች አፍ ነገር ሁሉ ይጸናል" ከሚለው የሙሴ ሕግ ጋር የተዛመደ ነው፡፡ ይህ ሃሳብ ምንም እንኳን ተከሳሹ ወይም በዳዩ የማይስማማበት ቢሆንም ነገር ግን ከሐሰት ከሳሾች የሚጠበቅበትም ነው፡፡ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ማስተማሩን በመቀጠል፦ ሁለቱ ምስክሮች የሚፈለጉት ለመክሰስ ወይም ለመፍረድ አይደለም፤ ነገር ግን ለመርዳት እና ለማገዝ ነው፡፡ በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህ በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች የሚኬደው መንገድም ላይሳካ እንደሚችልም ተናግሯል፡፡

ሁለት ወይም ሦስት ምስክሮች ባይሰማ፥ ለቤተክርስቲያን ንገራት (ማቴ፡18፥17) ይህም ለአማኞች ሕብረት ማለት ነው፤ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ሕዝበ ክርስቲያኑ ወይም ሕብረቱ በአንድነት ይሳተፋልና፡፡ በመሆኑም ይህ የሚያመላክተው አንድ የጠፋን ወንድም ለመመለስ በፍቅር መበርታት እንደሚያስፈልግም የሚያሳይ ቦታ ነው፡፡ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልሶም እንዲህ አለ፦ “ቤተክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ (ማቴ፡18፥17)፡፡ ይህ እንደ አረመኔ እና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ የሚለው አገላለጽ፥ መናቅን ወይም አለማክበበርን ሊያመላክት ይችላል፤ እውነታው ግን ወንድማችንን መልሰን ለእግዚአብሔር አሳልፈን መስጠትን ወይም በእግዚአብሔር እጅ ላይ እንድናስቀምጥ ይጋብዘናል፡፡ ይህም የሆነው ከሁላችንም በላይ የሆነው እግዚአብሔር በታላቅ ፍቅሩ ስለሚረዳ እና ስለሚያግዝ ነው፡፡ ክርስቶስ ቀራጮችን እና አረመኔዎችን በፍቅሩ ተቀበላቸው፤ ሁሉንም አካታች የሆነው የክርስቶስ ፍቅር በዘመኑ የነበሩ ጠቢባንን ያስፈራቸው ነበር፡፡ በእንደዚህ አይነት ጉዳይ ላይ ነገሮችን ለእግዚአብሔር አሳልፎ መስጠት፣ ከእኛ በላይ የሆነው ነገር ለእግዚአብሔር ቀላል በመሆኑ እና ለቤተክርስቲያንም ጭምር አልመለስ ያለው ወንድማችን በእግዚአብሔር ፊት ብቻውን ህሊናውን ሲያቀርብ የተሻለ ስለሚሆን ነው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በወንድማማችነት ልብ መወቃቀስ እና መተራረም እንድንችል፣ እንዲሁም በሕብረታችን በወንድማማችነት መዋደድ፣ በይቅር ባይነት እና እንዲሁም በእግዚአብሔር ምሕረት በመደገፍ እንድንበረታ ትርዳን”።

07 September 2020, 11:17