ር. ሊ. ጳ ፍራንቸስኮስ፥ “ኢየሱስ ፊትን ሳይሆን ሕይወትን የሚቀይር እምነት እንዲኖረን ይጠይቀናል”
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመስከረም 17/2013 ዓ. ም፣ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን፣ በዕለቱ በተነበበውን የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ ያደረጉትን አስተንትኖ አሰምተዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ያቀረቡት አስተንትኖ ከማቴ. 21፥28-32 ላይ የተወሰደ ሲሆን ይህም፥ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ወደ አንደኛው ቀርቦ፦ ልጄ ሆይ! ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ አለው፡፡ እርሱም መልሶ፦ አልሄድም አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ፡፡ አባት ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው፤ ልጅም መልሶ፦ እሺ ጌታዬ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም” የሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በአስተንትኖአቸው እግዚአብሔር ይታገሰናል፤ ይጠብቀናልም፡፡ እንቢ ካልን በኋላም እንመለስ ዘንድ በታጋሽነቱ የጸና ነው፡፡ በነጻነት እንድንኖርም ፈቃዱ ነው፤ በምርጫችን ከእርሱ በመራቅም ስሕተት ብንሰራም እንድንመለስ በትዕግስት ይጠባበቃል፡፡ እንዲሁም "መታዘዝ በተግባር የሚመለስ እና የሚኖር ነው" በማለት ገልጸዋል።
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፥ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእለቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፥
የቫቲካን ዜና፤
"የተወደዳችሁ ወንድቼ እና እህቶቼ! እንደምን አረፈዳችሁ!
የዛሬው የወንጌል አስተንትኖ፥ በማቴ. 21፥ከ28-32 ላይ ያተኮረ ይሆናል፡፡ የዛሬው የወንጌል አስተምህሮ፥ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት በሚያስተምርበት ጊዜ፥ ሰብዓዊነትን ያላገናዘበ እንዲሁም ክፉ እና ደጉን ከመለየት ባሻገር ሕሊናን በሃላፊነት ተጠያቂ የማያደርግ ሐይማኖተኝነትን ተቃውሟል፡፡ ይህም በማቴ. 21፥28-32 በተነበበው በዛሬው የወንጌል ክፍል በሁለቱ ልጆች ምሳሌ በሚገባ ተብራርቷል፡፡በወይኑ አትክልት ሥፍራ ሄዶ ለመሥራት ከአባት በኩል ለልጆቹ ግብዣ ቀረበላቸው፡፡አባትም ወደ አንደኛው ቀርቦ፦ ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ አለው፡፡ እርሱም መልሶ፦ አልሄድም አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ፡፡ አባት ወደ ሁለተኛውም ልጁ ቀርቦ እንዲሁ አለው፤ ልጅም መልሶ፦ እሺ ጌታዬ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም፡፡ መታዘዝ በተግባር የሚመለስ እና የሚኖር ነው፤ በወይኑ አትክልት ስፍራ ሄዶ በመሥራት ይታያል፤ ለእግዚአብሔር መንግሥት በመሥራትም ይገለጻል፡፡ በዚህ ቀላል ምሳሌ፥ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮ የሰዎችን ሕይወት ከማበልጸግ አንጸር ሐይማኖት ከሚያደርገው ውጫዊ እና ልማዳዊ ተግባራት ባሻገር ነው፡፡
ከላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚቃወመው ሐይማኖተኝነት የሚያስተምረው፥ ልክ በማቴ. 21፥23 የተጠቀሱት የካህናት አለቆች እና የሕዝብ ሽማግሌዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከመግባት አንጻር በማቴ. 21፥31 በተጠቀሱት ቀራጮች እና ጋለሞቶች እንደሚቀደሙ ነው፡፡ እዚህ ጋር በሚገባ መረዳት ያለብን ደግሞ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ የማይፈጽሙ እና ስነ-ምግባር የጎደላቸው ሰዎች መልካም አደረጉ ማለት አይደለም፡፡”ቀራጮች እና ጋለሞቶች በመልካም አኗኗራቸው የተመሠከረላቸው ናቸው” በማለት እያስተዋወቀም አይደለም፡፡ ነገር ግን በፀጋው የታገዙ ናቸው፤ ይህም በክርስቶስ የሚሠጥ ፀጋ ነው፤ ማንኛውም ሰው በመለወጥ እና ወደ እርሱ በመቅረብ የሚያገኘው ማለት ነው። በእርግጥም እነዚህ ሰዎች የክርስቶስን አስተምህሮ በማዳመጥ እና ንስሐ በመግባታቸው ሕወታቸው ተለውጧል፡፡
በዛሬው የወንጌል ክፍል የሚያስደንቅ ነገር የሠራው፥ የመጀመሪያው ወንድም ነው፤ምክንያቱም እንቢታውን ወደ እሺታ በመቀየሩ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ይታገሰናል፤ይጠብቀናልም፡፡ እንቢ ካልን በኋላም በትዕግስት ይጠብቀናል፡፡ እግዚአብሔር በነጻነት እንድንኖርም ፈቃዱ ነው፤ በምርጫችን ከእርሱ በመራቅም ስሕተት ብንሰራም እንመለስ ዘንድ በትዕግስት ይጠባበቃል፡፡ እንቢታችንም ወደ እሺታ እንዲቀየር በጉጉት ይጠብቃል፤በመሆኑም ታድሰን በአባታዊ እቅፉ እና ገደብ በሌለው ምሕረቱ ይቀበለናል፡፡በእግዚአብሔር ማመን፦ እውነትን ከሐሰት፣ ከክፋት መልካምነትን እንዲሁም ከራስ ወዳድነት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን መውደድን መምረጥ ቅድመ ሁኔታው ነው፡፡በኃጢአት ወድቀው ነገር ግን በመለወጥ እና ምርጫቸውን በማስተካከል በእግዚአብሔር ያመኑት በመንግሥተ ሰማያት የቀደመውን ሥፍራ ያገኛሉ፡፡ ይህም በሉቃ. 15፥7 ላይ እንደተጠቀሰው፦ “እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል” እንደሚለው ማለት ነው።
መለወጥ የመንጻት ሂደት በመሆኑ በሕመም የተሞላ ነው፤ በመሆኑም ሥቃይ የለሽ አይደለም፡፡ ክርስቶስን በመምረጥ በሙላት ወደ እርሱ የምንቀርበው ደግሞ መስቀሉን በመደገፍ ነው፡፡ ያለ እርቅ፣ አንድነት እና መንፈሳዊ ተጋድሎ ቅድስና አይኖርም፡፡ መንፈሳዊ እድገት እራስን መካድን እና መዋረድን ያካትታል፤ ይህም ቀስ በቀስ በብፁዕነት በሚገኝ ሰላም እና ደስታ እንድንኖር ይመራናል፡፡ የዛሬው የወንጌል ክፍልም ስለ ክርስቲያናዊ ሕይወት አኗኗር ጥያቄን ያነሳል፤ ይህም በሕልም ወይም በምኞት ብቻ ሳይሆን በመሰጠት የሚኖር ነው፡፡ እንዲሁም እራሳችንን ለእግዚአብሔር ፈቃድ በማስገዛት፣ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንን በመውደድ በተግባር በመኖር ነው ክርስቶስን መምሰል የምንችለው።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ ታዛዦች እንድንሆን ትርዳን።እርሱም ደንዳናን ልብ ሠብሮ፣ ለንስሐ አብቅቶ እና በክርስቶስ ቃል የተገባልንን መዳንን እንድናገኝ ያበረታናልና"።