ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የኢየሱስ ማዳን ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላለማዊ ይዘት ያለው ነው ማለታቸው ተገልጸ!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን ሆነው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው 09/2013 ዓ.ም ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም እ.አ.አ በግንቦት 06/2020 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ በጸሎት ዙሪያ ላይ ሲያደርጉት የነበረው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የመጨረሻና 38ኛው ክፍል እንደ ነበረ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን የኢየሱስ ማዳን ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላለማዊ ይዘት ያለውን ነው፣ መቼም ቢሆን ብቻችንን አይተወንም ማለታቸው ተገልጿል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
በዚህ በተከታታይ በጸሎት ዙሪያ ላይ ስናደርገው የነበረው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ውስጥ ጸሎት በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ በጣም ግልፅ ከሆኑት ገጽታዎች አንዱ መሆኑን ደጋግመን ተመልክተናል። በተልእኮው ሂደት ውስጥ ከአባቱ ጋር ሲያደርገው በነበረው ውይይት ውስጥ ደምቆ የሚያበራ ውይይት ውስጥ በሕልውናው ውስጥ ሁሉ ዋና እና ቦግ ብሎ የሚያበራ አመላካች ምልክት ስለነበረ ራሱን በጽሎት ውስጥ አስርጾ ነበር።
የኢየሱስ ጸሎት በስቃዩ እና በሞቱ ሰዓት ይበልጥ በጭንቀት እና በጥልቀት የተደረገ እንደነበረ ቅዱስ ወንጌል ይነግረናል። በእርግጥ እነዚህ የመጨረሻ ክስተቶች የክርስቲያን ስብከት ዋና ፍሬ-ነገር ናቸው-እነዚያ ኢየሱስ በመጨረሻ የሕይወቱ ሰዓታት በኢየሩሳሌም ውስጥ የኖረባቸው ወቅቶች የቅዱስ ወንጌል እምብርት ናቸው፤ ምክንያቱም ወንጌላውያን ለዚህ ትረካ በተመጣጣኝ ሁኔታ ሰፊ ቦታ ስለሰጡ ብቻ ሳይሆን የእሱ ክስተት ሞትና ትንሣኤ - እንደ መብረቅ ብልጭታ - በቀሪው የኢየሱስ ሕይወት ላይ ብርሃን ስለሚፈነጥቅ ነው። እሱ የሰውን ልጅ ስቃይ እና ህመም የሚንከባከብ የበጎ አድራጎት ሰው አልነበረም-እርሱ ከእዚያም እጅግ በጣም የላቀ ነው። በእርሱ ውስጥ የምናገኘው መልካም ነገሮችን ብቻ አይደለም ፣ በእርሱ ውስጥ መዳን አለ፣ ይህ መዳን ግን ከበሽታ ወይም ከተስፋ መቁረጥ የሚያድን ጊዜያዊ ደህንነት ሳይሆን ነገር ግን አጠቃላይ ደህንነት፣ መሲሃዊ ደህንነት በህይወት ላይ ወሳኝ በሆነ በሞት ላይ ድል በማጎናጸፍ ተስፋን የሚሰጥ ደህንነት ነው።
በመጨረሻው የሕይወት ቀናት ውስጥ ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ በጸሎት ውስጥ ተዘፍቆ ነበር።
በሞት ጭንቀት ውስጥ ገብቶ በተመታበት ወቅት በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ በአስደናቂ ሁኔታ ይጸልያል። ሆኖም ኢየሱስ በትክክል በዚያ ቅጽበት እግዚአብሔርን “አባ” አባት ብሎ ይጠራዋል (ማርቆስ 14፡36)። ይህ ቃል ፣ በአራማይክ ፣ በኢየሱስ ቋንቋ ፣ ቅርርብ እና መተማመንን ይገልጻል። ልክ ጨለማው በዙሪያው ሲከበው እንደተሰማው ፣ ኢየሱስ በዚያ ትንሽ ቃል አባ በማለት ጨለማውን ገፈፈው!
በተጨማሪም ኢየሱስ በግልፅ እግዚአብሔር ዝም ያለ በመሰለው ወቅት እንኳን ሳይቀር በመስቀል ላይ ይጸልያል። እናም አሁንም እንደገና “አባት” የሚለው ቃል ከአፉ ይወጣል። እሱ በጣም ትጉህ ጸሎት ነው ፣ ምክንያቱም በመስቀል ላይ ኢየሱስ ፍጹም አማላጅ ነው -እርሱ በእርሱ ላይ ሞት ለፈረዱበት ሰዎች ሳይቀር ለሁሉም በደለኞች ማንንም ሳይለይ እና ሳያገል ለሁሉም ለሚኮንኑት ሁሉ ሳይቀር “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው”(ሉቃ 23፡34) በማለት ጸለየላቸው። በዚህ ትይንት መካከል በነፍስ እና በአካል ላይ በአሰቃቂ ሥቃይ ውስጥ በነበረበት ወቅት ኢየሱስ በመዝሙራዊ ቃላት በመጠቀም “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” የሚለውን በመዝሙር 22፡2 ላይ የተጠቀሰውን ቃል በመጠቀም በዓለም ውስጥ ለሚገኙት ለሁሉም ድሆች በተለይም ለተረሱ ሰዎች ጸለየ። መስቀሉ የመዳን ዋጋ የከፈለ እጅግ በጣም የሚወደውን አንድያ ልጁን የሚያቀርበው የአብ የመጨረሻው ስጦታ ነው - ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአት ሁሉ ተሸክሞ ከእግዚአብሔር ወደ ተለየ ጥልቅ ገደል ይወርዳል። ሆኖም አሁንም “አምላኬ!” በማለት ወደ እሱ ይመለሳል።ኢየሱስ እስከ መጨረሻው እስትንፋስ ድረስ “አባት ሆይ ፣ መንፈሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” እስከሚል ድረስ በዚያ እጅግ አስጨናቂ ወቅት እንኳ በልጅነቱ ተማምኖ በእዚያ መንፈስ ውስጥ ተዘፍቆ ይኖራል (ሉቃ 23፡46)።
ስለዚህ ኢየሱስ በሕይወቱ እና በሞቱ ወሳኝ ሰዓታት ውስጥ ይጸልያል። በትንሳኤ አብ ለጸሎቱ ምላሽ ይሰጣል። ኢየሱስም እንዲሁ በልቡ ጭንቀት ውስጥ ነፃ ስሜትን በመስጠት ሰብዓዊ በሆነ መንገድ ይጸልያል። በእግዚአብሔር አብ ላይ ያለውን እምነት በጭራሽ ሳይጠራጠር ይጸልያል።
በኢየሱስ ጸሎት ምስጢር ውስጥ እራሳችንን ለመዝፈቅ እንችል ዘንድ በሕማማት ቀናት በጣም ጠንከር ያለ ፣ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የምናገኘው እጅግ ረጅም ጸሎት ምን እንደሆነ እና የኢየሱስ “ክህነታዊ ጸሎት” ተብሎ የሚጠራውን ማየት እንችላለን ፣ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 17 ላይ እንደ ተጠቀሰው። ዐውደ-ጽሑፉ እንደገና ከፋሲካ ጋር የተገናኘ ነው - ኢየሱስ ቅዱስ ቁርባንን በመሰረተበት የመጨረሻው እራት ላይ እንገኛለን። ይህ ጸሎት - የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚገልጸው “የፍጥረት እና የደህንነት ሥራ እንዲሁም ሞቱን እና ትንሳኤውን ያጠቃልላል” (ቁ. 2746) ይለናል። ሰዓቱ ሲቃረብ እና ኢየሱስ ወደ መጨረሻው የሕይወት ጉዞ ሲሄድ ጸሎቱ የበለጠ ይሆናል ስለ እኛ የሚያደርገው ምልጃ ጠንከር ያለ ነው። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሁሉም ነገር በዚያ ጸሎት እንደተጠቃለለ ያስረዳል-“እግዚአብሔር እና ዓለም፣ ቃል እና ሥጋ ፣ ዘላለማዊ ሕይወት እና ጊዜ፣ እራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ፍቅር እና እርሱን አሳልፎ የሚሰጠው ኃጢአት፣ ያለ ደቀመዛሙርቱ እና እርሱን በመስማት በኢየሱስ የማያምኑ ሰዎች፣ ውርደት እና ክብር ”(ቁጥር 2748) ተገልጿል። የላይኛው ክፍል ግድግዳዎች መላውን ዓለም ለማቀፍ የተከፈቱ ናቸው፣ እናም የኢየሱስ ዐይን ያረፈው ከእርሱ ጋር አብረው በበሉ ደቀ መዛሙርት ላይ ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም ጭምር ነው “በመጨረሻው እራት እና በመስቀል እንጨት ላይ ስለእናንተ ጸለይኩኝ” ለማለት የፈለገ ይመስል ነበር። በከፍተኛ የስቃይ ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም እንኳን ፣ እኛ መቼም ብቻችንን አይደለንም።
ይህንን በጸሎት ጭብጥ ዙሪያ ላይ በተከታታይ ስናደርገው የነበረውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዑደት ስናጠናቅቅ ማስታወስ የሚገባን በጣም ጥሩ ነገር ይመስለኛል - እኛ ብቻ አይደለንም የምንጸልየው ነገር ግን ለእኛም ቢሆን “ተጸልዮልናል” ቀድሞውኑም ቢሆን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመተባበር ኢየሱስ ከአብ ጋር ባደረገው ውይይት ተጽልዮልናል። እኛ በክርስቶስ ኢየሱስ ተዋጀን፣ በእሱ የፍቅሩ ፣ የሞቱ እና የትንሳኤው ሰዓት እንኳን ሁሉም ነገር ለእኛ ተሰጠ። ስለዚህ በጸሎት እና ሕይወት እኛ ማለት ያለብን ነገር ቢኖር ለአብ እና ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይሁን አሁንም፣ ዘወትርም ለዘለዓለም። አሜን።