ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እኛ ክርስቲያኖች በጋራ በፍቅር ዓለምን መለወጥ እንችላለን አሉ!
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንድነት እና ወዳጅነት እንዲኖር የሚያግዝ ሥነ-ምግባራዊ ተነሳሽነት እንዲያንሰራራ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል በማለት ቅዱስነታቸው በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ገልጸዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
ቅዱስነታቸው ይህንን መልእክት ያስተላለፉት የዮሐንስ 17 በመባል የሚታወቀው አለማቀፋዊ ንቅናቄ አባላት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ይህ ዮሐንስ 17 የተሰኘው አለማቀፋዊ ንቅናቄ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 17 ላይ በተጠቀሱት ጭብጦች ዙሪያ ላይ በማተኮር የሚሰራ እና በአማኞች ማህበረሰብ መካከል ያለውን የአንድነት ትስስር ለማጠናከር አብረው የሚሰሩ በርካታ የአማኞችን ያካተተ ንቅናቄ ሲሆን “እኛ አንድ እንደሆንን እነርሱም አንድ እንዲሆኑ፣ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ” በማለት ኢየሱስ ለአማኞች ሁሉ አንድነት በጸለየው ጸሎት ላይ መሰረቱን ያደረገ አለማቀፋዊ ይዘት ያለው ንቅናቄ ነው።
ሁሉም ነገር ከወንድማዊ ግንኙነቶች የተወለደ ነው። ፍቅር ዓለምን ይለውጣል ፣ ነገር ግን እሱ ማለትም ፍቅር ቀድሞ እኛን ሊለውጠን ይገባል በማለት የተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እነዚህን ሀሳቦች ያካፈሉት ዮሐንስ 17 በመባል ለሚታወቀው በኒው ዮርክ ውስጥ በሚገኘው የቅዱስ ዮሴፍ ሴሚናሪ እና ኮሌጅ ውስጥ ረቡዕ ሰኔ 02/2013 ዓ.ም ለሁለት ቀናት ያህል በበይነ መረብ አማካይነት የሚያደርጉትን ስብሰባ በጀመሩበት ወቅት እንደ ነበረ ተገልጿል።
ዮሐንስ 17 ንቅናቄ የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ 2013 ዓ.ም ጆዬ ቶዚኒ በመባል በሚታወቀው በአንድ የፕሮቴስታንት ፓስተር እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን ይህ መስራች የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አባል ባይሆንም ቅሉ በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ለተመረጡት ፍራንቸስኮስ ፓስተር ጆዬ ቶዚኒ እንዲፀልዩ በውስጣቸው ከፍተኛ ፍላጎት እንደ ተሰማቸው መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር ብዙ ጊዜ መገናኘታቸው ይታወሳል።
እንቅስቃሴው ስሙን የወሰደው ቀደም ሲል እንደ ተገለጸው ከቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 17 ሲሆን “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ” በማለት ኢየሱስ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ መሰረቱን በማደረግ የተቋቋመ አለም አቀፍ ንቅናቄ ነው። ንቅናቄው “ግንኙነት እና እርቅ ፣ ለክርስቲያኖች አዲስ የእርቅ መንገድ ነው” በሚል መሪ ቃል ሱባሄ በማድረጋ ላይ እንደ ሚገኙም ተገልጿል።
የአንድ አባት ልጆች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስፓኒሽ ቋንቋ ባስተላለፉት መልእክት የዮሐንስ 17 ንቅናቄ ካፕችቺኖ ፣ እራት ወይም አይስክሬም በጠረጴዛ ዙሪያ ሆነው በአንድነት ሲመገቡ ወንድማማቾች መሆናቸውን ስለሚገነዘቡ እንደ ሆነ የገለጹ ሲሆን ይህንን የሚገነዘቡት በቀለማቸው፣ በብሔራቸው ፣ በትውልድ ስፍራቸው ወይም በእምነታቸው የተለያዩ የአኗኗር ዘይቤዎች ሳይሆን ወንድማማቾች በመሆናቸው “የአንድ አባት ልጆች” በመሆናቸው የተነሳ ነው። እኛ እያንዳንዳችን ወንድማማቾች መሆናችንን መገንዘብ እንደ ሚኖርብን የገለጹት ቅዱስነታቸው “የትውልድ ቦታችንን ፣ ዜግነታችንን ፣ የቆዳችንን ቀለም ሳናስብ እኛ የአንድ አባት ልጆች ነን” ሲሉ አጥብቀው ተናግረዋል ፡፡
ከክርስቶስ ጋር መገናኘት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር ጥልቅ ሥነ-መለኮታዊ ዕውቀትን እንደማይፈልግ የጠቆሙ ሲሆን ፍቅር በመጀመሪያ ከኢየሱስ ጋር የሕይወት ገጠመኝ ነው ፤ እናም ከዚህ የፍቅር ገጠመኝ የተወለደው ጓደኝነት ፣ ወንድማማችነት እና የአንድ አባት ልጆች መሆናችንን እርግጠኛ እንድንሆን ያደርገና” ብለዋል። “ሁሉም ነገር” ፣ “ከወንድማዊ ግንኙነት ይጀምራል” ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለህይወት በጋራ እና ለከፍተኛ ዓላማ በተሰጠ መልኩ “ፍቅር ዓለምን ሊለውጥ ይችላል ፣ ግን በመጀመሪያ ፣ እኛን ፍቅር ሊልውጠን ይገባል፣ በፍቅር እኛ ክርስቲያኖች አንድ ላይ ዓለምን መለወጥ እንችላለን ፣ እግዚአብሄር ፍቅር ስለሆነ እራሳችንን መለወጥ እንችላለን!" ብለዋል።
ፍቅርን እንኖረዋለን እንጅ አንማረውም
ከዮሀንስ 17 ንቅናቄ ጋር ያደረጉት ግንኙነቶች እና ምስክርነታቸው ተስፋ እና ደስታ እንደ ሰጣቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው አብረው እንዲጓዙ እና ሕይወትን እና የወንድማማችነት ፍቅር መጋራታቸውን እንዲቀጥሉ የንቅናቄውን አባላት ቅዱስነታቸው አበረታተዋል።
በጣም ብዙ ጊዜ ፍቅር ከፕላቶኒካዊ አስተሳሰብ፣ ከምናባዊ ፍልስፍና ጋር ግራ በተጋባ መልኩ አያይዘን እንመለከተው ይሆናል ያሉት ቅዱስነታቸው ፍቅር ግን ልክ ኢየሱስ እንዳደረገው ፍቅር ለሌሎች ሕይወቱን ስለሚሰጥ ፍቅር ተጨባጭ የሆነ ነገር ነው ብለዋል። “ብትወድም ወይም ባትወድም ሥጋ የሆነው ፍቅር ፣ ሕይወትን የሰጠን ፍቅር መንገድ ነው” ብለዋል። ፍቅር የምንማረው ነገር ሳይሆን የምንኖረው ነገር ነው በማለት የተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የዮሐንስ 17 ንቅናቄም ፍቅርን በመኖር ያስተምሩናል ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ንግግራቸውን ደምድመዋል።