ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በጸሎት ዙሪያ ላይ ሲያደርጉት የነበረውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አጠናቀቁ! ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በጸሎት ዙሪያ ላይ ሲያደርጉት የነበረውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አጠናቀቁ! 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በጸሎት ዙሪያ ላይ ሲያደርጉት የነበረውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አጠናቀቁ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው እ.ኤ.አ. ከግንቦት 06/2020 ዓ.ም ጀምረው በጸሎት ዙሪያ ላይ በ38 ምዕራፎች የተከፈለ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሲያደርጉ እንደ ነበረ የሚታወቅ ሲሆን ይህ በጸሎት ዙሪያ ላይ ሲያደርጉት የነበረው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እ.አ.አ በሰኔ 16/2020 ዓ.ም አጠናቀዋል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጸሎትን በተመለከተ 38 ምዕራፎች የተከፈለ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አድርገዋል ፣ የመጨረሻው እ.ኤ.አ. ሰኔ 16/2021 ዓ.ም ላይ መጠናቀቁን ቀደም ሲል መግለፃችን የሚታወስ ሲሆን ከእዚህ ቀደም ቅዱስነታቸው በተከታታይ አድርገዋቸው የነበረውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አጠር አጠር አድርገን እንደ ሚከተልው እናቀርብላችኋለን ተከታተሉን።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በግንቦት 06/2020 ዓ.ም አድርገውት የነበረው የመጀመሪያ ክፍል የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “የጸሎት ምስጢር” በሚል አርእስት የቀረበ ሲሆን ዓለም እየተከሰተ በሚገኘው የኮርና ወረርሽኝ ምክንያት እየተናወጠች ትገኛለች በማለት ተናግረው እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን “ዛሬ በጸሎት ጭብጥ ላይ ያጠነጠነ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንጀምራለን። ጸሎት የእምነት እስትንፋስ ነው ፣ እሱ በጣም ትክክለኛ አገላለጽ ነው። ከእነዚያ እምነት ካላቸው ልቦች በአደራ መልክ ወደ እግዚአብሔር የሚደረግ እና ከእነዚያ ልቦች ውስጥ እንደ ሚወጣ ጩኸት ነው” ማለታቸው ይታወሳል። አክለውም ጸሎት የእምነት እስትንፋስ ነው ፣ እሱ በጣም ትክክለኛው መገለጫው ነው። እመነት ካለው እና በእግዚአብሔር ከሚታመኑ ሰዎች ልብ የሚወጣ ጩኸት ይመስላል ማለታቸው ይታወሳል።

እ.ኤ.አ. ግንቦት 13/2020 ዓ.ም ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “የክርስቲያን ጸሎት” በሚል አርእስት የቀረበ የክፍል ሁለት አስተምህሮ ሲሆን በክርስቲያን ጸሎት ባህሪዎች ላይ ያጠነጠነ ነበር። "የክርስቲያኖች ጸሎት በሰዎች ላይ ምንም ዓይነት ፍርሃት እንዲኖር የማይፈልግ በጣም ርኅራኄ ካለው ከአምላክ ፊት ጋር ግንኙነት ይፈጥራል" ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን "እግዚአብሔር ወዳጅ ፣ አጋር ፣ ሙሽራ ነው። በጸሎት ውስጥ ከእሱ ጋር የመተማመን ግንኙነት መመስረት ትችላላችሁ” ማለታቸው ይታወሳል።

እ.አ.አ በግንቦት 20/2020 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “የፍጥረታት ምስጢር” በሚል አርእስት የቀረበ የክፍል ሦስት አስተምህሮ እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን የፍጥረታት ምስጢር በውስጣችን የውዳሴ መዝሙር ማምጣት እንዳለበት አጥብቀው የተናገሩ ሲሆን ጸሎት “የመጀመሪያው የተስፋ ኃይል ነው” በማለት አክለው መግለጻቸው ይታወሳል።

እ.አ.አ በግንቦት 27/2020 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “የጻድቃን ጸሎት” በሚል አርእስት የቀረበ የክፍል አራት አስተምህሮ እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው እንዳስታወሱት ፣ ክፋት እንደ ሰደድ እሳት እየተስፋፋ ቢሆንም ፣ የፃድቃን ጸሎት ተስፋን የማለምለም አቅም ያለው እና “የሕይወት ሰንሰለት” መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል። አክለውም “ጸሎት ድንጋይ የሆነ ልባችንን ወደ ሰው ልብ በመለወጥ ለእግዚአብሔር በሩን ይከፍታል” ማለታቸው ይታወሳል።

እ.አ.አ በግንቦት በሰኔ 03/2020 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “የአብርሃም ጸሎት” በሚል አርእስት የቀረበ የክፍል አምስት አስተምህሮ ሲሆን አንድ ሰው በእምነት መጸለይ መማር አለበት ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ውይይት እስኪመስል ድረስ መጸለይ አለበት ማለታቸው ይታወሳል። አክለውም በድንገት በአብርሃም ሕይወት ውስጥ ድምፁን ከፍ አድርጎ የሚያቃጭል ድምፅ አለ፣ የሚረባ የማይመስል ጭካኔ የተሞላበት ጉዞ እንዲጀምር የሚጋብዘው ድምፅ-ከትውልድ አገሩ ፣ ከቤተሰቦቹ ከሥር መሰረቶቹ ራሱን ነቅሎ ወደ አዲስ የወደፊት ፣ ወደ ተለየ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንዲወስድ የሚያነቃቃ ድምፅ” አለ ማለታቸው ይታወሳል።

እ.አ.አ በሰኔ 10/2020 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “የያዕቆብ ጸሎት” በሚል አርእስት የቀረበ የክፍል ስድስት አስተምህሮ እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን “ከእግዚአብሔር ጋር ይታገል” ስለነበረው ያዕቆብ ላይ ያተኮረ እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን እራሱን እንደ አቅመ ደካማ፣ ተሰባሪ ነገር ግን መለኮታዊ ምሕረት ያገኘ ሰው አድርጎ ይቆጥር ነበር ብለዋል። አክለውም ያዕቆብ ከደካማነቱ እና ከአቅም ማነስ ፣ ከኃጢአቶቹ እንኳን የተሻለ ሌላ ነገር ለእግዚአብሔር ማቅረብ አልቻለም ነበር፣ ነገር ግን ከእግዚአብሔር በረከትን የሚቀበል ይህ ያዕቆብ ነው” ማለታቸው ይታወሳል። 

እ.አ.አ በሰኔ 17/2020 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “የሙሴ ጸሎት” በሚል አርእስት የቀረበ የክፍል ሰባት አስተምህሮ እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን “አትፍረዱ! ነገር ግን ብዙ ኃጢአት ለሰሩስ ሰዎች አማልዱ” ማለታቸው ይታወሳል። አክለውም ሙሴ በፍርሃቶቹ እና በተቃውሞዎች የተነሳ የእስራኤልን ሕዝብ እንደገና እንዲንከባከብ የሚናገረውን እግዚአብሔር ለዚያ ተልእኮ ብቁ አይደለሁኝም በማለት ይቃወማል ፣ የእግዚአብሔርን ስም አያውቅም ፣ በእስራኤላዊያንም የሚታመን አልመሰለውም፣ የሚንተባተብ ምላስ ነበረው። በሙሴ ከንፈሮች ላይ በብዛት የሚታየው ቃል ፣ በሚያቀርበው ጸሎት ሁሉ የሚነሳው ቃል “ለምን?” የሚለው ጥያቄ ነው። ለምን ላከኝ? ይህንን ሕዝብ ለምን ነፃ ማውጣት ፈለክህ? እነዚህን የመሳሰሉ ብዙ ጥያቄዎችን ያነሳ ነበር። በመጀመርያዎቹ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ የሕግ መጽሐፍት ውስጥ አንድ አስገራሚ ታሪካዊ የሆነ ነገር እናነባለን፣ እግዚአብሔር ሙሴን “በእስራኤላውያን ፊት እኔን ቅዱስ አድርጋችሁ ለማክበር ስላልታመናችሁብኝ ይህን ማኅበረሰብ ወደ ምሰጠው ምድር ይዛችሁ አትገቡም” (ዘኁልቁ 20፡12) በማለት ይናገራል።

በእነዚህ ፍርሀቶች፣ ሙሴ ብዙውን ጊዜ የሚያቅማማ ልብ ስለነበረው በዚህ ባሕሪው እኛን ይመስላል። እኛም በእርሱ ድክመቶች እና በእርሱ ጥንካሬዎች የተነሳ ተደነቅን። የመለኮታዊ አምልኮ መስራች፣ በታላቅ ምስጢሮች መካከል የሚገኝ፣ ሕጉን ለሕዝቡ እንዲያስተላልፍ በአደራ የተሰጠው ፣ በዚህ ምክንያት በተለይ በፈተና እና ኃጢያት በሚፈጽሙበት ወቅት ከህዝቦቹ ጋር የጠበቀ ትብብር እንዲኖር አደረገ። ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ወዳጅነት በመመስረቱ የተነሳ ፊት ለፊት ከእርሱ ጋር መነጋገር ይችላል (ዘፀ 33፡11 ይመልከቱ) ፣ እናም ለፈጸሙት ኃጢአት ምሕረት ከሚያስፈልጋቸው፣ በፈተና ውስጥ ለሚገኙ፣ በግብፅ በግዞት ላይ እያሉ ‘መልካም ኑሮ እንኖር ነበረ’ ብለው ድንገተኛ የቁጭት ስሜት ለሚሰማቸው ሰዎች እርሱ ቅርብ እና ወዳጃዊ የሆነ ግንኙነት ነበረው።

ስለሆነም ሙሴ ባለሥልጣንና አምባገነን መሪ አልነበረም፣ የኦሪት ዘኁልቁ መጽሐፍ እሱን በተመለከተ “ሙሴ በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበር” (ዘኁልቁ 12፡3) በማለት ሙሴን ይገልጸዋል። ሙሴ ትልቅ ቦታ ቢሰጠውም በጉዞአቸው በእግዚአብሔር በመተማመን በሚጓዙ በመንፈስ ድሆች ከሆኑ ሰዎች ጋር አንዱ በመሆን አብሯቸው ይጓዝ ነበር።

ስለዚህ ሙሴ ያደርገው የነበረው ፀሎት የምልጃ ጸሎት ነው (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2574 ይመልከቱ) ። በእግዚአብሔር ላይ ያለው እምነት ሙሉ በሙሉ አንድ ነው፣ ለህዝቡ የአባትነት ስሜት እንዲኖረው አድርጎታል። ወደ እግዚአብሔር እጁን በመዘርጋት በሰማይ እና በምድር መካከል ድልድይ ሆኖ ያገለግል ነበር በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ስለእርሱ ይናገራል። በጣም አስቸጋሪ በሆኑባቸው ወቅቶች እንኳን ሳይቀር፣ ሰዎች እግዚአብሔርንና እርሱን መሪዎች መሆናቸውን ውድቅ በሚያደርጉበት እና በወርቅ የተሰራ ጥጃ ማምለክ በጀመሩበት ቀን እንኳን ሳይቀር ሙሴ ህዝቡን ለመተው አልፈለገም ማለታቸው ይታወሳል።

እ.አ.አ በሰኔ 24/2020 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “የዳዊት ጸሎት” በሚል አርእስት የቀረበ የክፍል ስምንት አስተምህሮ እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን “በጸሎት ዙሪያ ላይ ጀምረነው የነበረውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በመቀጠል ዛሬ ደግሞ ከንጉሥ ዳዊት ጋር እንገናኛለን። ከልጅነቱ ጀምሮ እንኳን በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ፣ በእግዚአብሔር ህዝብ እና በእምነታችን ታሪክ ማዕከላዊ የሆነ ሚና ለሚጫወት ለልዩ ተልእኮ ተመርጧል። በወንጌል ውስጥ ኢየሱስ “የዳዊት ልጅ” በመባል ብዙ ጊዜ ተጠርቷል፣ እንደ እርሱ በእውነቱ እርሱም በቤተልሔም ነው የተወለደው። በተሰጣቸው ተስፋዎች መሠረት መሲሁ ከዳዊት ዘር ይመጣል፣ እርሱም ሙሉ በሙሉ ከእግዚአብሔር ልብ የተጣጣመ ንጉሥ የሚመጣው የመዳን እቅዱን በታማኝነት የሚያፀና ነው” ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

አክለውም “ስለሆነም ዳዊት በመጀመሪያ እረኛ ነበር፣ እንስሳትን የሚጠብቅ ፣ አደጋ እንዳይመጣ የሚከላከል ሰው ፣ ምግብ የሚሰጣቸው እረኛ ነበር። ዳዊት በእግዚአብሔር ፈቃድ ህዝቡን መንከባከብ በሚጀምርበት ወቅት እርሱ የሚያደርጋቸው ነገሮች በጣም የተለዩ አይሆኑም፣ ምክንያቱም የእረኝነት ልምድ ነበረውና። ለዚህ ነው የእረኛ ምስሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ደጋግሞ የሚከሰተው። ኢየሱስ እራሱን እንኳን “መልካም እረኛ” ሲል ገልጿል፣ ባህሪው ከተቀጣሪ እረኛ የተለየ ነው፣ በበጎቹ ምትክ ሕይወቱን ይሰጣል ፣ ይመራቸዋል፣ እያንዳንዳቸውን በስም ያውቃቸዋል” (ዮሐ 10 11-18 ይመልከቱ) ማለታቸው ይታወሳል።

አክለውም “በዳዊት ሙያ ውስጥ የቀረበው ሁለተኛው ባሕርይ ገጣሚ የነበረው ባህርይ ነው። ከዚህ አነስተኛ ምልከታ ፣ ዳዊት ከህብረተሰቡ ተነጥለው ለረጅም ጊዜ ለመኖር በሚገደዱ ግለሰቦች ላይ እንደሚታየው ፣ ዳዊት መጥፎ ሰው አለመሆኑን እንገምታለን። እሱ ይልቁንም ሙዚቃ እና መዘመር የሚወድ አሳቢ ሰው ነበር። በገና ሁል ጊዜ ከእርሱ አይለይም ነበር፣ አንዳንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር የውዳሴ መዝሙር በማቅረብ ያመሰግነው ነበር (2 ሳሙ 6: 16 ይመልከቱ) ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሐዘኑን ለመግለጽ ወይም የገዛ ኃጢአቱን ለመናዘዝ (መዝ 51፡3 ይመልከቱ) ይዘምር ነበር” ማለታቸው ይታወሳል።

 እ.አ.አ በጥቅምት 07/2020 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “የኤሊያስ ጽሎት” በሚል አርእስት የቀረበ የክፍል ዘጠኝ አስተምህሮ እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን “ጸሎት የግል ነፍሳችንን ብቻ የምንመግበት ሳይሆን የሰውን ልጅ በሙሉ ለማገልገል የሚያስችለንን ኃይል ከእግዚአብሔር የምናገኝበት መንገድ ነው” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

ነብዩ ኤልያስ ኢፍትሃዊ መንገድ ይከተል የነበረውን ንጉሥ በድፍረት ይቃወም እንደነበር አስታውሰው፣ እንደ ነብዩ ኤልያስ የመሪዎችን ኢፍትሃዊ ተግባሮችን በድፍረት በመቃወም፣ ስህተታቸውንም መናገር የሚችሉ ክርስቲያኖች ያስፈልጋሉ ብለዋል። ስለ ጸሎት ባቀረቡት አስተምህሮአቸውም፣ ነብዩ ኤልያስ ጠንካራ የጸሎት ሕይወት የነበረው ነብይ መሆኑን አስታውሰዋል።

ክርስቲያኖች በአንድ ሃሳብ እንዲጸኑ መጠራታቸውን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ እምነትን በእግዚአብሔር ላይ በማድረግ እርሱ ለአገልግሎት ወደሚልከን ማንኛውም ቦታ በደስታ ለመሄድ ራስን ነጻ ማድረግን ይጠይቃል ብለዋል። ጸሎት የግል ነፍስን ብቻ ለመንከባከብ ሲባል ከእግዚአብሔር ጋር የምናደርገው ግንኙነት ከሆነ፣ ይህ እውነተኛ ጸሎት ሊሆን እንደማይችል አስረድተው፣ ጸሎት ማለት እግዚአብሔር በፈለገው ጊዜ እና ሥፍራ ወንድሞችን እና እህቶችን ለማገልገል በሚጠራን ጊዜ ራስን ነጻ እና ዝግጁ አድርጎ መቅረብ ነው ብለዋል።  የጸሎት መለኪያው ለጎረቤቶቻችን ተጨባጭ ፍቅር ማሳየት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ክርስቲያኖች በቅድሚያ በሚፈልጉት ነገር ማስተንተን እና ቀጥሎም በጸሎት መጠየቅ ይኖርባቸዋል ብለው ይህ ካልሆነ ግን በርካታ ኢፍትሃዊ ድርጊቶችን ሊፈጽሙ ይችላሉ ብለዋል። ምክንያቱም ምን ማድረግ ወይም ምን መሥራት እንዳለባቸው አስቀድመው እግዚአብሔርን በጸሎት ስለማይጠይቁ ነው ብለዋል።

እ.አ.አ በጥቅምት 07/2020 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “የመዝሙረ ዳዊት ጸሎት” በሚል አርእስት የቀረበ የክፍል ዐስር አስተምህሮ እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን የእያንዳንዱ ምዕመን ጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰሚነት አለው ማለታቸው ይታወሳል። በወቅቱ በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የመስብሰቢያ አዳራሽ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ያቀረቡት አስተምህሮ ስለ ጸሎት በሚያስተምረው በመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ላይ መሠረት ያደረገ እንደነበር ለመገንዘብ ተችሏል። ቅዱስነታቸው በዛሬ አስተምህሮአቸው እንደገለጹት፣ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ እንደማንነታችን መሆነ እንዳለብን ገልጸው፣ በችግርም ሆነ በማንኛውም ሕይወት ውስጥ ሆነው ጸሎታቸውን የሚያቀርቡትን እግዚአብሔር ሳይተዋቸው የሚያደምጣቸው መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም “በመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ውስጥ ሁሉንም የሰው ልጅ ስሜቶች እናገኛለን፤ ደስታን፣ ሐዘንን፣ ጥርጣሬን፣ ተስፋን እና በሕይወታችን ውስጥ ሊያጋጥሙን የሚችሉትን ሁሉ እናገኛለን። ትምህርተ ክርስቶስ እንደሚያረጋግጥልን በመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹት መዝሙሮች፣ ሁሉም ሰው በማንኛውም ቦታ እና ጊዜ ላይ ሆኖ ማቅረብ የሚችለውን የጸሎት ዓይነቶችን የያዘነው” ብለዋል።

በመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ውስጥ ስሜታችንን የምንገልጽበት፣ ውዳሴን እና ምስጋናን የምናቀርብበት፣ በደስታ እና በመከራ ጊዜ ሆነን ልመናችንን ወደ እግዚአብሔርን የምናቀርብበትን ቃል እናገኛለን። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እውነተኛ የሕይወት ልምድ ያላቸውን ሰዎች ብቻ እናገኛቸዋለን።

"ጸሎታችንን ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ስንፈልግ እንደ ማንነታችን መቅረብ አለብን። በሚገባ ለመጸለይ ከፈለግን ጸሎታችን የምንገኝበትን ሁኔታ የሚገልጽ መሆን ይኖርበታል። በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ፣ እኛ ራሳችን ብቻ የምናውቃቸውን ውስጣዊ ችግሮቻችንን ሆነ መልካም ነገሮቻችንን ይዘን መቅረብ ያስፈልጋል"።          

መከራዬ እስከ መቼ ይሆን?

በጸሎት በኩል ከምናቀርባቸው በርካታ ጥያቄዎች መካከል አንዱ፥ “ጌታ ሆይ! ይህን መከራ እስከ መቼ ልታገሰው”? በማለት ስንት ጊዜ ጸልየናል? ያሉት ቅዱስነታቸው፣

"የእያንዳንዱ ምዕመን ጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ትርጉም አለው ብለው፣ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ስንቀርብ፣ እግዚአብሔር በቸርነት ዓይኖቹ ስለሚመለከተን እና ስለሚሰማን ወደ እርሱ እንሄዳለን ብለዋል። ወደ እግዚአብሔር ዘንድ እንድንቀርብ በውስጣችን ያለው መንፈስ ቅዱስ ስለሚገፋፋን ነው፤ የእግዚአብሔር ውድ ልጆች በመሆናችን እና እግዚአብሔርም ይህን ስለሚመለከት ወደ እርሱ በጸሎት እንቀርባለን"።

እ.አ.አ በጥቅምት 21/2020 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀደም ሲል “የመዝሙረ ዳዊት ጸሎት” በሚል አርእስት ጀምረውት ከነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በዚህ የክፍል 11 የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ጸሎት እንዴት መጸለይ እንደ ሚገባን ያስተምረናል ማለታቸው ተገልጿል። በሕይወት ውስጥ ፈተና እና ችግር በሚያጋጥመን ሰዓት እግዚአብሔር የሁላችንም ጸሎት እንደ ሚሰማ በመግለጽ አስተምህሮዋቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው በዚህም መሠረት ሁልጊዜም ቢሆን በርትተን ልንጸልይ ይገባል ብለዋል። አክለውም በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ ሁሉንም የሰዎች ስሜቶችን እናገኛለን - ደስታን ፣ ህመምን ፣ ጥርጣሬዎችን ፣ ተስፋዎችን ፣ ህይወታችንን ፣ በቀለማት ያሸበረቁ ሕይወቶችን የመሳሰሉትን ሐሳቦች የሚገኝበት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደ ሆነ በመግለጽ አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እያንዳንዱ መዝሙር “በሁሉም ሁኔታዎች እና በሁሉም ጊዜያት በእውነት ሊጸልይ የሚችል የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል” መሆኑን ገልፀዋል ፣ መዝሙረ ዳዊትን በማንበብ የጸሎትን ቋንቋ እንማራለን በማለት አክለው ገልጸዋል።

ሁሉም ስሜቶቻችን በጸሎት ውስጥ ቦታቸውን ያገኛሉ

በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ ስሜታችንን ለመግለጽ ፣ እግዚአብሔርን ለመለመን ፣ ለማመስገን ፣ እግዚአብሔርን በደስታ እና በመከራ ለመጠየቅ ቃላቱን እናገኛለን በማለት አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በእነዚህ ጽሑፎች ውስጥ ረቂቅ ሰዎችን አናገኝም ፣ ነገር ግን በሕይወት ካለው ተመክሮ የተወሰዱ ጸሎቶችን እናገኛለን ብለዋል።

ወደ እርሱ ለመጸለይ እኛ ማን መሆናችንን ማወቁ በራሱ በቂ ነው ፣ እናም ይህንን አይዘንጉ-በደንብ ለመጸለይ፣ ጸሎታችን ተጨባጭ እና አሁናዊ ሊሆን ይገባል በማለት አስተምሕሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ጌታ ሆይ ፣ እኔ እንደዚህ ነኝ” በማለት ማንነታችንን ለእግዚአብሔር በመናገር በእውነተኛ ስሜት ጸሎታችንን ማቅረብ ይኖርብናል ማለታቸው ተገልጿል።

ጌታ ሆይ እስከ መቼ?

ጸሎቶች በውስጣቸው ከያዙት በርካታ ጥያቄዎች መካከል አንዱ “የማያቋርጥ ጩኸት” ይሰማል-ይሄው “እስከ መቼ?” የሚለው ቃል እንደ ሆነ የገለፁት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “ጌታ ሆይ ፣ እስከ መቼ ድረስ እንዲህ እሰቃያለሁ? ጌታ ሆይ ስማኝ!”: - “እስከመቼ? ፣ ጌታ ሆይ… እስከ መቼ?” በማለት ወደ እግዚአብሔር ጸሎታችንን በመንፈሳዊነት ማቅረብ ይኖርብናል ብለዋል። እ.አ.አ በጥቅምት 28/2020 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “ኢየሱስ የጸሎት ሰው ነበር” በሚል አርእስት የቀረበ የክፍል 12 አስተምህሮ እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን ጸሎት በምናደርግበት ጊዜያት ሁሉ ኢየሱስ ከእኛ ጋር ይጸልያል ማለታቸው ይታወሳል። አክለውም በጸሎት ዙሪያ ላይ በብሉይ ኪዳን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ስናደርገው የነበረውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዛሬም በመቀጠል አሁን ደግሞ ወደ ኢየሱስ መጥተናል።  ኢየሱስም ይጸልይ ነበር። ተልእኮውን በይፋ ከጀመሩ በፊት ጥምቀት በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ያከናውናል። ወንጌላዊያኑ ለዚህ ክፍል መሠረታዊ ጠቀሜታ በመስጠት ይስማማሉ። እነሱ ሁሉም ሰዎች በጸሎት እንዴት እንደተሰበሰቡ ይተረካሉ ፣ እናም ይህ ስብስብ እንዴት የንስሃ ባህሪ እንዳለው ግልፅ ያደርጉታል (ማርቆስ 1፡5 ፣ ማቴዎስ 3፡8)። ሕዝቡ ለኃጢአት ይቅርታ ሊጠመቅ ወደ ዮሐንስ በመሄድ ይጠመቁ ነበር -በዚህ ውስጥ የንስሃ ባሕርይ አለ ፣ የመለወጥ ማለታቸው ይታወሳል። ቀጥለውም ከሁሉም በላይ የሉቃስ ወንጌል የኢየሱስ ጥምቀት የተካሄደበትን የጸሎት ሁኔታ አጉልቶ ያሳያል- “ሕዝቡ ሁሉ ሲጠመቁ ኢየሱስም ደግሞ ከተጠመቀ በኋላ በጸሎት መንፈስ ቆሞ በነበረበት ወቅት የሰማይ በር ተከፈተ” (ሉቃስ 3፡21)  በማለት ይናገራል።  በመጸለይ ኢየሱስ የሰማይን በር ይከፍታል ፣ እናም መንፈስ ቅዱስ ከዚያ ውስጥ ይወርዳል። ከሰማይም አንድ ከፍተኛ ድምጽ እውነቱን ያውጃል - “የምወደው ልጄ እርሱ ነው ፣ በእርሱም እጅግ ደስ ይለኛል” (ሉቃስ 3፡ 22) የሚል ድምጽ ይሰማል። ይህ ቀላል የሚመስል ሐረግ እጅግ ብዙ ድንቅ ነገሮችን አካቶ የያዘ ነው፣ ይህም የኢየሱስን ምስጢር የሚገልጽ እና ልቡ ሁልጊዜ ወደ አብ የሚዞር አንድ ነገር እንድናደርግ ያደርገናል። እርሱን ለመኮነን በሚመጣው የሕይወት ዐውሎ ነፋስ እና ዓለም ውስጥ ፣ እሱ በሚጸናበት በጣም ከባድ እና አሳዛኝ ልምዶች ውስጥ እንኳን ፣ እሱ ራሱን የሚያስቀምጥበት ቦታ እንደሌለ ቢገልፅም ፣ በዙሪያው ጥላቻ እና ስደት እያንዣበበ ቢሆንም ፣ የኢየሱስ መሸሸጊያ አብ ራሱ ነበር ማለታቸው ይታወሳል።

እ.አ.አ በሕዳር 04/2020 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “ኢየሱስ የጸሎት አስተማሪ ነው” በሚል አርእስት የቀረበ የክፍል 13 አስተምህሮ እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን ጸሎት የሕወታችን አቅጣጫ መሪ መሣሪያ ነው ማለታቸው ይታወሳል። ሲቀጥሉም ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወቱን በይፋ መኖር በጀመረበት ወቅት ሁል ጊዜም የጸሎትን ኃይል ይጠቀም ነበር። ኢየሱስ ወደ ገለልተኛ ስፋራዎች በመሄድ በእነዚያ ስፍራዎች እንደ ነበረ ቅዱሳን ወንጌላዊያን ይገልፃሉ። እነዚህ በጣም ወሳኝ የሆኑና አስተዋይ ምልከታዎች ናቸው ፣ እነዚያን የጸሎት ሁኔታዎች በዓይነ ሕሊናችን ለመመልከት ያስችሉናል። እነሱ በግልጽ የሚያሳዩት ለድሆች እና ለታመሙ ሰዎች ኢየሱስ የበለጠ ቦታ በሚሰጥበት ጊዜያት እንኳን ኢየሱስ ከአብ ጋር ያለውን የጠበቀ ውይይት በጭራሽ እንደማይረሳ ነው። የሰዎችን ችግሮች ለመፍታት በሚሠራበት ወቅት ወደ ቅድስት ሥላሴ ፣ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ወደ አለው ሕብረት መመለሱ አስፈላጊ መሆኑን እርሱ ይስማማበታል።

እ.አ.አ በሕዳር 11/2020 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “በጽናት የሚደረግ ጸሎት” በሚል አርእስት የቀረበ የክፍል 14 አስተምህሮ እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን የሚጸልይ አንድ ክርስቲያን ምንም ነገር አይፈራም ማለታቸው ተገለጸ ሲሆን ይህንን በሚመለከት ደግሞ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ማለታቸው ይታወሳል።

ኢየሱስ በፅናት እና የማያቋርጥ ቀጣይነት ባለው መልኩ ሊደረግ ስለሚገባ ጸሎት ምሳሌ ስጥቶናል። ከአብ ጋር የማያቋርጥ ውይይት ፣ በዝምታ እና በማሰላሰል ያድርገው የነበረው ግንኙኘት የሁሉም የእርሱ ተልእኮው ምሰሶ ነበር። ቅዱሳን ወንጌላዊያን ለደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ጸሎትን በተመለከተ የሰጠውን ማሳሰቢያ በገለጹበት ወቅት እነርሱ ማለትም ደቀመዛሙርቱ ሳይታክቱ በፅናት እንዲጸልዩ ኢየሱስ አሳስቦዋቸው እንደ ነበረ ይገልፁልናል። ይህንን በተመለከተ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ (ቁ. 2613) ሲናገር በሉቃስ ወንጌል ውስጥ የተካተቱትን ሦስት ምሳሌዎች ያስታውሰናል ፣ ይህም የኢየሱስን የጸሎት ባህሪ የሚያጎላ ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ ጸሎት በፅናት መደረግ የሚገባው ሲሆን ለምሳሌም በቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንደ ተጠቀሰው ድንገት የመጣውን እንግዳ ለመቀበል ፣ እኩለ ሌሊት ላይ የጓደኛውን ቤት በማንኳኳት ዳቦ እንደለመነው ሰው መሆን ማለት ነው። እኩለ ሌሊት ስለሆነና ጓደኛው ተኝቶ ስለነበረ በቤቱ ውስጥ ተኝቶ የነበረው ጓደኛው “አይሆንም!” ተኝቻለሁኝ ሲል ይመልስለታል ፣ እሱ ግን ተነስቶ ዳቦ እንዲሰጠው እስከሚያስገድደው ድረስ አጥብቆ ይጠይቃል (ሉቃ. 11፡5-8) በፅናት የተደርገ ጥያቄ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ከእኛ የበለጠ ታጋሽ በመሆኑ የተነሳ በእርሱ በልቡ በር ላይ በእምነት እና በፅናት መንፈስ ሆነው የሚያንኳኩ ሰዎች አያፍሩም። እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ይመልሳል ፡፡ ሁል ጊዜም። አባታችን የምንፈልገውን ነገር ገና ሳንጠይቀው በፊት በደንብ ጠንቅቆ ይውቃል። አጥብቆ በፅናት እርሱን መለመናችን እርሱን ምን እንደ ሚያስፈልገን ለማሳወቅ ወይም ለማሳመን አይጠቅመንም ፣ ነገር ግን በውስጣችን ፍላጎትን እና ተስፋን ለመመገብ ይጠቅማል።

ሁለተኛው ምሳሌ ደግሞ ‘ከባላጋራዬ ጋር ስላለብኝ ጒዳይ ፍረድልኝ’ እያለች ፍትህ ፈልጋ ወደ አንድ ዳኛ ትመላለስ የነበረች ሴት ታሪክ እናያለን።  ይህ ዳኛ ሙሰኛ ነው ፣ እሱ ሥነ ምግባር የጎደለው ሰው ነበር፣ ነገር ግን በመጨረሻ ይህች መበለት ስለ ምትጨቀጭቀኝ እፈርድላታለሁ ፤ አለበለዚያ ዘወትር እየተመላለሰች ታሰለቸኛለች (ሉቃ 18፡1-8) በማለት ይፈርድላታል። እናም እንዲህ ያስብ ነበር “ነገር ግን እኔ ችግሯን ፈትቼ ብገላገል ይሻላል ምክንያቱም ያለማቋረጥ እየመጣች ትጨቀጭቀኛለች፣ ታማርራለች” በማለት ይፈርድላታል። ይህ ምሳሌ እምነት ለክፉ ነገሮች እና ፍትህ መጓደልን ለመቅረፍ አንድ አፍታ በችኮላ አድርገነው የምንተወው ነገር ሳይሆን ይልቁኑ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ድፍረት የተሞላበት ዝንባሌ መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል።

ሦስተኛው ምሳሌ ለመጸለይ ወደ ቤተ መቅደስ የሄዱ አንድ ፈሪሳዊ እና አንድ ቀራጭ የነበረ ሰው ታሪክ ያቀርባል። የመጀመሪያው በብቃቱ በመኩራራት ልቡን ነፍቶ ወደ እግዚአብሔር ይቀርባል፤ ሌላው ወደ መቅደሱ ለመግባት እንኳን ብቁ እንዳልሆነ ይሰማዋል። ሆኖም እግዚአብሔር የመጀመሪያውን ማለትም የትዕቢተኞችን ጸሎት አልሰማም፣ እሱ ማለትም እግዚአብሔር ደግሞ ለትሑታን መልስ ይሰጣል (ሉቃ. 18: 9-14። የትህትና መንፈስ ከሌለ እውነተኛ ጸሎት የለም። በጸሎት እንድንጠይቅ የሚያደርገን የትህትና መንፈስ ነው።

 

 

 


 

 

 

 

 

 

17 June 2021, 10:29