ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የጤና እንክብካቤ ለሁሉም ሰው ተደራሽ መሆን አለበት አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ  ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ በእለቱ በሚነበበው የቅዱስ ወንጌል ቃል ላይ ተንተርሰው በቫቲካን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በሐምሌ 04/2013 ዓ.ም ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተከናወነው እንደ ተለመደው በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ሆነው ሳይሆን ነገር ግን በቅርቡ በገጠማቸው መጠነኛ የጤና እክል ምክንያት የሕክምና እርዳታ እየተሰጣቸው ከሚገኘው “ጄሜሊ” በመባል ከሚታወቀው ሆስፒታል ውስጥ ሆነው እንደ ነበረ ተገልጿል። ቅዱስነታቸው በወቅቱ ከሆስፒታል ሆነው ባደረጉት አጭር አስተንትኖ የጤና እንክብካቤ ለሁሉም ሰው ተደራሽ መሆን እንዳለበት ተረድቻለሁ ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን  

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ቅዱስነታቸው በወቅቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከትተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

እዚህ አሁን ካለውበት “ጄሜሊ” በመባል በሚታወቀው ሆስፒታል ውስጥ ሆኜ እንኳን ይህንን ዘወትር እሁድ የምናደርገውን የብስራተ ግብርኤል ጸሎት ለማደረግ በመቻሌ ደስ ብሎኛል። ሁላችሁንም አመሰግናለሁ-የእናንተን ቅርበት እና የፀሎቶቻችሁን ድጋፍ በጥልቀት ተረድቻለሁ። ከልቤ አመሰግናለሁ!

የዛሬው የቅዱስ ወንጌል ክፍል እንደሚናገረው በእርሱ የተላኩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “ብዙ በሽተኞችን በዘይት ቀብተው ፈወሷቸው” (ማርቆስ 6፡13) ይለናል። ይህ “ዘይት” በእርግጥ የመንፈስ እና የአካል ምቾት የሚሰጥ የታመሙ ሰዎች የሚቀቡት በምስጢረ ቀንዲል አማካይነት የሚከናወን ቅባ ቅዱስ ነው። ነገር ግን ይህ “ዘይት” እንዲሁ የታመመውን ሰው በእንክብካቤ በመስማት፣ በመቅርበ፣ በማገዝ፣ ርህራሄ በማሳየት መከናወን እንዳለበት የሚያሳይ ነው። ይህም ስሜትዎን የበለጠ እንደሚያሳድገው ፣ ህመምዎን እንደሚያረጋጋ እና እንደሚያዝናና የሚረዳ እንክብካቤ ማድረግ ጭምር ነው። ይዋል ይደር እንጂ ሁላችንም ይህንን “ቅባት” እንፈልጋለን ፣ እናም ሁላችንም ለሌላ ሰው መስጠት እንችላለን ፣ በጉብኝት ፣ በስልክ ጥሪ ፣ እርዳታ ለሚፈልግ ሰው በተዘረጋ እጅ ይህንን ማከናወን እንችላለን።

በሆስፒታል ውስጥ በቆየሁባቸው በእነዚህ ቀናት ውስጥ በጣሊያን እና በሌሎችም ሀገሮች እንደሚደረገው ሁሉ ጥሩ የጤና ክብካቤ ለሁሉም ተደራሽ መሆን እንዳለበት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አይቻለሁ። ለሁሉም ሰው ተደራሽ የሆነ ጥሩ አገልግሎት የሚያረጋግጥ የጤና እንክብካቤ ሥርዓት አስፈላጊ ነው። ይህ ውድ የሆነ ጥቅም ለሁሉም ተደራሽ ሊሆን ይገባዋል። ተደራሽነቱ ቀጣይ መሆን አለበት! እናም ለዚህ ሁሉም ሰው ቁርጠኛ መሆን አለበት ፣ ምክንያቱም ሁሉንም የሚረዳ እና የሁሉንም አስተዋፅዖ የሚጠይቅ ስለሆነ ነው።

ለዶክተሮች እና ለሁሉም የጤና እንክብካቤ ሰራተኞች እና ለሆስፒታል ሰራተኞች ያለኝን አድናቆት እና ማበረታቻ ለመግለጽ እፈልጋለሁ። እናም ለታመሙ ሁሉ እንጸልይ ፣ በተለይም በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ላሉት ፣ ማንም ብቻውን እንዳይቀር ፣ ሁሉም ሰው በመደመጥ ፣ በመቀራረብ እና በእንክብካቤ ቅባት እንዲቀባ መጸለይ ይኖርብናል። ይህንን ፀጋ የበሽተኞች እናት በሆነችው በማርያም አማላጅነት እንጠይቅ።

 

11 July 2021, 12:37