ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እየተሰጠ ያለው የሕክምና ዕርዳታ መልካም ውጤቶችን በማሳየት ላይ ይገኛል     ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እየተሰጠ ያለው የሕክምና ዕርዳታ መልካም ውጤቶችን በማሳየት ላይ ይገኛል  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ውጤታማ የሕክምና ዕርዳታ ተደርጎላቸው በማገገም ላይ መሆናቸው ተገለጸ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ካለፈው እሑድ ጀምሮ በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኝ ጀመሊ ሆስፒታል ገብተው ሕክምናቸውን በመከታተል ላይ መሆናቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው ባለፉት ቀናት ውስጥ በተደረገላቸው የሕክምና ዕርዳታ በጥሩ ሁኔታ በማገገም ላይ መሆናቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ አስታውቀው፣ ዘወትር እሑድ እኩለ ቀን ላይ የሚያቀርቡትን ሳምንታዊ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በሆስፒታሉ ከሚገኙ የማዕከሉ ማኅበረሰብ ጋር በመሆን ነገ እሑድ ሐምሌ 4/2013 ዓ. ም. የሚያቀርቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሁን የሚገኙበት የጤና ሁኔታ እጅግ መልካም መሆኑን  የገለጹት የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩኒ፣ በመደበኛ ሰዓት የሚቀርብላቸውን ምግብ መውሰድ መጀመራቸውን እና ዕለታዊ የሕክምና ዕርዳታዎችም መልካም ውጤቶች ማሳየታቸውን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም በተጨማሪ በማረፊያ ክፍላቸው አካባቢ መንቀሳቀስ መጀመራቸውን፣ ቅዱሳት መጽሐፍትን እያነበቡ ያለ ሕመም መልካም የዕረፍት ጊዜን በማሳለፍ ላይ መሆናቸውን፣ በሆስፒታሉ በሚገኝ ጸሎት ቤት ውስጥ ተገኝተው በምዕመናን እገዛ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ማቅረባቸውን አቶ ማቴዎ ብሩኒ አስታውቀዋል።

ቅዱስነታቸው በሆስፒታል ቆይታቸው ወቅት በጸሎት የረዷቸውን፣ የመልካም ጤና ምኞታቸውን ለገለጹላቸው በሙሉ ልባዊ ምስጋና ማቅረባቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ አስታውቀዋል።

 

10 July 2021, 12:49