በባርሴሎና ከተማ በሚገኝ የቅድስት ቤተሰብ ካቴድራል ላይ መብራት የማስቀመጥ ሥራ በባርሴሎና ከተማ በሚገኝ የቅድስት ቤተሰብ ካቴድራል ላይ መብራት የማስቀመጥ ሥራ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ምዕመናን የእግዚአብሔርን ጸጋ እንዲቀበሉ የማርያምን ዕርዳታ ለመኑ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በስፔን-ባርሴሎና ከተማ በሚገኝ የቅድስት ቤተሰብ ካቴድራል ከፍታ ላይ የተቀመጠ የመብራት ምረቃን በማስመልከት በላኩት የቪዲዮ መልዕክት፣ የእግዚአብሔርን ጸጋ መቀበል እንዲቻም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልብን እንድታበራ ተመኝተዋል። ቅዱስነታቸው ለአገሪቱ ካቶሊካዊ ምዕመናን መልካም ምኞታቸውን የገለጹት የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ኅዳር 29/2014 ዓ. ም. በተከበረው የጽንሰታ ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ዕለት መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነቸው በመልዕክታቸው፣ ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር የጥበብ ሥራ የተገለጸባት በመሆኗ በእርሷ በኩል ለአረጋውያን፣ ለድሆች እና ከኅብረተሰቡ ለተገለሉት በሙሉ የእግዚአብሔርን እርዳታ ለማግኘት ዘወትር መጸለይ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ትናንት ጽንሰታ ማርያም ዓመታዊ በዓል በተከበረበት ዕለት ለስፔን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፣ በቅድስት ቤተሰብ ካቴድራል ከፍታ ላይ የተሰቀለውን የኮከብ ብርሃን የሚመለከቱት በሙሉ ሕይወታቸው እንዲበራ እና በብርሃኑ አማካይነት እመቤታችን ቅድስት ማርያምን እንዲመለከቱ በማለት በጸሎታቸው አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የርኅራኄ እና የፍቅር ኃይል ማመን የምንችለው ወደ እርሷ ስንመለከት ብቻ ነው ብለዋል። በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ለተገኙት በሙሉ በላኩት ሰላምታ ላይ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተጎዱ ድሆችን፣ በሽተኞችን፣ አረጋዊያንን እና ወጣቶችንም አስታው፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአዲስ ሐዋርያዊ አገልግሎት ብርሃን እንደሆነች አረጋግጠዋል።

የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ኅዳር 29/2014 ዓ. ም. የጽንሰታ ማርያም ዓመታዊ በዓል መከበሩን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ማርያም የእግዚአብሔር ጥበብ የተገለጸባት፣ እግዚአብሔር ለእሷ ካላት እቅድ ጋር ፍጹም በመስማማት፣ በእግዚአብሔር ፊት ቅድስት፣ ትሑት፣ እጅግ ታዛዥ እና ግልጽ ሆና መገኘቷንም አስታውሰዋል። ይህ ምሥጢር የእምነት መግቢያ በር እንዲሆን ጋውዲ ፈልጎ የሠራው የመጀመሪያ ሥራ እንደሆነ፣ ወደ ቅድስት ሥላሴ በሚያቀርቡት ጸሎት ምዕመናን እንደ ማርያም የዚህ ምሥጢር ቤተ መቅደስ መሆንን በመማር እግዚአብሔርንም በመንፈስና በእውነት ማምለክ እንዲቻል መገንባቱን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። 

በየዕለቱ የሚታዩ የፍቅር እና የአገልግሎት ምልክቶች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጋውዲ ይህን ሥራ ሲያቀርብ፣ ማርያምን የሥራው ማዕከል በማድረግ  ሕፃኑን ኢየሱስ ክርስቶስን ለእኛ በማቅረብ የበጎ ተግባር ምሳሌ እንደሆነች ማስረዳቱን አስታውሰው፣ ቅዱስ ዮሴፍ ለማርያም በሚሰጣት ትኩረት እና በቤተክርስቲያን አማካይነት እግዚአብሔርን እና ሰዎችን ማፍቀር እንደሚቻል መናገሩን ጠቅሰው፣ በየቀኑ በምናሳየው ፍቅር እና በምናቀርበው አገልግሎት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ምሳሌ እንድንከተል ቅዱስነታቸው ጋብዘዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለስፔን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በላኩት መልዕክት፣ ከዛሬ ጀምሮ በከፍታ ላይ የሚታይ ብርሃን፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚመጣውን ጸጋ በመቀበል ኃጢአትን ለመቃወም የሚያስችል ኃይል የሚገኝበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ ከማርያም ጋር ሆኖ መጸለይ ማለት በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ምስጢር ላይ እንድናሰላስል፣ እርሱ የሚያሳየንን መንገድ እንድናስተውል እና የጥቃት ፈተናዎችን በመቃወም ጥንካሬን የምናገኝበት ነው ብለዋል።

ለማርያም አደራ መስጠት

የባርሴሎና ከተማ ለእያንዳንዱ ሰው ሕይወት የበለጠ ምቹ ከተማ እንድትሆን እና ሁሉንም ሰው በእንግድነት የምትቀበል ከተማ እንድትሆን ቅዱስነታቸው በጸሎታቸው አስታውሰው፣ ይህን አገልግሎት ተግባራዊ ለማድረግ የበለጠ ኃላፊነትን ለሚወስዱት በሙሉ አደራቸውን አቅርበው፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥበብን፣ የአገልግሎት ዝግጁነትን እና የአመለካከት ስፋትን እንድትሰጣቸው እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውንም ትጠብቃቸው በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።  

በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ መሆን

ስቃይ ውስጥ የሚገኙ ድሆች “በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ናቸው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣

ከማኅበረሰቡ የተገለሉ እና በድህነት የሚሰቃዩ ሰዎች፣ “ለድህነታቸው እና ለመገለላቸው ተጠያቂዎች እኛ ነን” በማለት ተናግረዋል። በማከልም፣ በዚህ አጋጣሚ በሰዎች ላይ የሚደርስ መከራን ለማስወግድ የተጣለብንን ኃላፊነት ማሰብ እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው አደራ ብለዋል።

ዛፍ ያለ ሥር እንደማያድግ፣ አበባም እንደማያወጣ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ዛፍን እና አረጋዊያንን ፈጽሞ መዘንጋት እንደማያስፈልግ አሳስበው፣ አረጋውያን የታሪክ ማኅደር በመሆናቸው ወደ ጎን መባል እንደሌለባቸው አሳስበው፣ አረጋዊያን ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት የሚጠቅሙ ነገሮች ሁሉ ምንጭ መሆናቸውን አስረድተዋል። ከአረጋዊያን የሚገኝ ጥበብ ወደ ሌሎችም እንዲተላለፍ፣ እንዲያብብ እና እንዲያድግ ለማድረግ በወጣቶችና በአዛውንት መካከል የሚደረግ ውይይት ማደግ እንዳለበት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው አሳስበዋል።

09 December 2021, 16:39