በማዳጋስካር ውስጥ በተፈጥሮ እና በረሃብ አደጋ ለተጎዱት ቤተሰቦች የተደረገ የምግብ ዕርዳታ በማዳጋስካር ውስጥ በተፈጥሮ እና በረሃብ አደጋ ለተጎዱት ቤተሰቦች የተደረገ የምግብ ዕርዳታ 

ር. ሊ ጳ ፍራንችስኮስ፣ በጦነት ላይ ባለ ዓለማችን ውስጥ ወንድማማችነት እንዲቀድም አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጥቅምት 6/2015 ዓ. ም. የሚከበረውን የዓለም የምግብ ቀን ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል። በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት ዋና ጸሐፊ በላኩት መልዕክት፣ የሰዎችን ቁጥር ሳይሆን ስብዕናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ረሃብን ለማስወገድ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ውስጥ ሰብዓዊነት እና አጋርነት እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ማንም ወደ ኋላ መተው የለበት” በሚል መሪ ሃሳብ የዘንድሮ የዓለም የምግብ ቀን ጥቅምት 6/2015 ዓ. ም. እንደሚከበር ታውቋል። “ማንም ወደ ኋላ መተው የለበት” የሚለው የዘንድሮ መሪ ሃሳብ ብዙ ፈተናዎች ከፊታችን እንዳሉብን ያስታውሰናል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ አለመታደል ሆኖ ዛሬ የምንገኘው በጦርነት አውድ ውስጥ መሆኑን ተናግረው፣ ይህንንም ‘ሦስተኛው የዓለም ጦርነት’ ብለን ልንጠራው እንችላለን ብለዋል። ከተመሠረተ 77 ዓመታት ያስቆጠረውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፣ በመንግሥታቱ ኅብረት ሥር የሆነው የምግብ እና የእርሻ ድርጅት፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በችግር እና በረሃብ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሰዎች ፍላጎት ለማሟላት የተቋቋመ መሆኑን አስታውሰዋል።

ማንም ወደ ኋላ እንዳይቀር መተባበር ያስፈልጋል

አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር፣ የተሻለ ምርት፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ የተሻለ አካባቢ እና ሕይወት ሁሉ ሰው እንዲኖረው የዓለም የምግብ ቀን የሚያሳስብ መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሱ በርካታ ቀውሶችን በኅብረት ካልሆነ መፍታት እንደማይቻል፣ ማንም ወደ ኋላ እንዳይቀር በኅብረት መሥራት እና በኅብረት መጓዝ ያስፈልጋል ብለዋል። ይህም ከሁሉ አስቀድሞ ሌሎችን እንደ ወንድሞች እና እህቶች መመልከት፣ እንደ ግል የቤተሰብ አባላት በመመልከት መከራቸውን እና ፍላጎታቸውን መጋራትን እንደሚጠይቅ ገልጸው፣ አንዱ የአካል ክፍላችን ሲሰቃይ ሌሎች ክፍሎች በሙሉ አብሮ እንደሚሰቃዩ ቅዱስ ወንጌልን በመጥቀስ ተናግረዋል። 

ፍትሃዊ እና ዘላቂ መፍትሄዎች

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አያይዘውም፣ ረሃብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጦትን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የበኩሉን አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ የሚገኘው ድርጅቱ፣ ለሚቀጥሉት አሥርት ዓመታት የያዘው ስትራቴጂካዊ ማዕቀፍ ያለውን ጠቀሜታ አስታውሰው፣ የመርሃ ግብሩ እቅዶች ድንገተኛ ለሆኑ ቀውሶች ወይም ችግሮች አስቸኳይ ምላሽ ለመስጠት ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን ፍትሃዊ እና ዘላቂ መፍትሄዎችን የሚያገኝ መሆን አለበት ብለዋል። የተመጣጠነ ምግብ ካለማግኘት ጋር የተገናኘውን የድህነት ችግር በየደረጃው በጋራ የመታገል አስፈላጊነትን ደጋግሞ መግለጽ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም በዓለም አቀፍ ትብብር ላይ የተሰማሩት ሁሉ ይህን ፈጽሞ መዘንጋት እንደማያስፈልግ ቅዱስነታቸው አሳስበው፣ የማንኛውም ስልት እና ጥረት ተጠቃሚ የሚሆኑት ተጨባጭ የስቃይ ታሪክ ያሏቸው ሰዎች እንጂ ቁጥራቸው አለመሆኑን አስረድተዋል።

ፍቅርን መግለጽ

በዓለም አቀፍ የትብብር ቋንቋ የፍቅርን ምድብ ማስተዋውቅ እንደሚገባ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ የጋራ ጥቅምን መሠረት ያደረጉ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን ከሰብአዊነት እና ከአብሮነት ጋር አዋህዶ ተግባርዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ ዓይናችንን አስፈላጊ ወደሆነው አቅጣጫ እንድናዞር መጠራታችንን፣ ሥራችን ሌሎችን መንከባከብ፣ ትኩረታችንም በነፃ በተሰጡን ፍጥረታት ላይ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቁርጠኝነት

የቅድስት መንበር እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቁርጠኝነትን በማረጋገጥ ለዋና ጸሐፊው መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅትን ጨምሮ የድሆችን ሕይወት ለማሻሻል ከሚሠሩት ሌሎች መንግሥታዊ ድርጅቶች ጋርም በጋራ ለመሥራት እንደሚፈልጉ ገልጸው፣ ይህን የሚያደርጉትም ወንድማማችነትን፣ መግባባትን እና የጋራ ትብብርን በማስቀደም፣ ለዛሬ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድም እውነተኛ ጥቅም የሚያስገኙ ሐሳቦችን ለማፍለቅ እንደሆነ ገልጸው፣ ይህን ዓላማ ለማሳከት የእግዚአብሔር ዕርዳታ እንዲታከልበት በጸሎት ጠይቀዋል።

15 October 2022, 16:15