ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስልክ ሲነጋገሩ - የፋይል ፎቶ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስልክ ሲነጋገሩ - የፋይል ፎቶ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከፕሬዝደንት ኢብራሂም ራይሲ ጋር በስልክ መነጋገራቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ጋር በስልክ መወያየታቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ጽ/ቤት አስታወቀ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ጥቅምት 25/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ ከኢራኑ ፕሬዝደንት ኢብራሂም ራይሲ ጋር በስልክ መነጋገራቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ጽ/ቤት ዳይሬክተር ማቴዮ ብሩኒ ገልጸው፥ ውይይቱ የተካሄደው በኢራኑ ፕሬዝደንት ኢብራሂም ራይሲ ጥያቄ መሠረት መሆኑን በመግለጫቸው አረጋግጠዋል። የፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት ድረ-ገጽ በዘገባው፥ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ላቀረቡት ጥሪ፥ ፕሬዝደንቱ አድናቆታቸውን መግለጻቸውን ገልጿዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እሑድ ጥቅምት 25/2016 ዓ. ም. ለእኩለ ቀኑ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባሰሙት ንግግር፥ በእስራኤል ጦር ሠራዊት እና በሐማስ ታጣቂዎች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ በማለት ከዚህ በፊት ያቀረቡትን ጥሪ በማደስ በፍልስጤም እና በእስራኤል ውስጥ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡበትን አስጨናቂ ሁኔታ ማሰብ መቀጠላቸውን ገልጸው፥ ሁለቱ ወገኖች የጦር መሣሪያን መጠቀም እንዲያቆሙ በእግዚአብሔር ስም በመማጸን፥ ይህን ተግባራዊ ካደረጉ ግጭቱ ሊወገድ እንደሚችል እና የቆሰሉትን ለመታደግ እና ሰብዓዊ ቀውስ እጅግ አሳሳቢ በሆነበት ጋዛ ውስጥ ዕርዳታ ይደርስ ዘንድ ታጋቾቹ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ቅዱስነታቸው በጥሪያቸው፥ ታጋቾቹ መካከል በርካታ ሕጻናት እንደሚገኙ አስታውሰው፥ ሕጻናቱ ወደ መጡበት ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ በማለት ተማጽነዋል። በዚህ ጦርነት የተጎዱትን፣ በዩክሬን እና ሌሎች ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ሕጻናት በማስታወስ የወደፊት ሕይወታቸው በዚህ መንገድ እየጠፋ በመሆኑ፥ ጦርነቱ እንዲቆም ሁሉም ሰው ድምጹን የሚያሰማበት ድፍረት እንዲኖረው በማሳሰብ፥ "ጦርነት ይብቃ!” ለማለት የሚያስችል ጥንካሬ እንዲኖረን እንጸልይ" በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፉት ቅርብ ቀናት ውስጥ ከፍልስጤም ፕሬዝደንት ማህሙድ አባስ ጋር ጥቅምት 22 ቀን፣ ከቱርክ ፕሬዝዳደንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር ጥቅምት 15 ቀን እና ከአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ጋር ጥቅምት 11/2016 ዓ. ም. በስልክ መገናኘታቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከእነዚህ የዓለም መሪዎች ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች ከተነሱት ርዕሠ ጉዳዮች መካከል አንዱ ወደ ሰላም ለመድረስ የሚያስችሉ መንገዶችን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ እና የኢየሩሳሌምን ሉዓላዊነት ወደሚያረጋግጥ የሁለት መንግሥታት የመፍትሄ ሃሳብ ወደ ሰላም እንደሚያደርስ ያላቸውን ተስፋ ጠቁመዋል።

 

06 November 2023, 16:03