PORTUGAL-VATICAN-POPE-RELIGION-WYD

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለ38ኛው ዓለም አቀፍ የሀገረ ስብከት ወጣቶች ቀን ያስተላለፉት መልዕክት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በሀገረ ስብከት ደረጃ ለ38ኛ ጊዜ ለተከበረው የዓለም ወጣቶች ቀን መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው እሑድ ኅዳር 16/2016 ዓ. ም. ተከብሮ ለዋለው የወጣቶች ቀን ያስተላለፉት መልዕክት መሪ ጥቅስ፥ “በተስፋ ደስ ይበላችሁ” (ሮሜ 12፡12) የሚል ሲሆን፥ የላቲን የአምልኮ ሥርዓት በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዘንድ የክርስቶስ ንጉሥ በዓል የተከበረበት ዕለት በመሆኑ ሁለቱም በዓላት አንድ ላይ የተከበሩበት ዕለት ነበር። ክቡራት እና ክቡራን አንባቢያን፥ የቅዱስነታቸውን መልዕክት ትርጉም ሙሉ ይዘቱ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

የተወደዳችሁ ወጣቶች ሆይ! ባለፈው ዓመት (2015 ዓ. ም.) ነሐሴ ወር ለ37ኛ ጊዜ በተከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ለመገኘት ከዓለም ዙሪያ ወደ ፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ከመጡት በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ ወጣቶች ጋር መገናኘቴ ይታወሳል። ወቅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሞት አደጋን እያስከተለ የነበረበት ወቅት በመሆኑ ሁላችንም ስጋት ውስጥ የወደቅንበት ጊዜ ነበር። ቢሆንም ይህ ታላቅ በዓል ወጣቶች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እና ከሌሎች ወንድሞች እና እህቶች ጋር ለመገናኘት ተስፋ ያደረጉበት ነበር። ተስፋችንም እውን ሆነ። ከእኔም ጭምር ለብዙዎቻችን ያ በዓል ከጠበቅነው በላይ ነበር። በሊዝበን ያደረግነው ስብሰባ አስደሳች፣ እውነተኛ የመታደስ ልምድ የተቀሰመበት፣ የብርሃን እና የደስታ ምልክት የታየበት ነበር ማለት ይቻላል።

ሊዝበን ከተማ ውስጥ “የጸጋ መስክ” እየተባለ በሚጠራ ሥፍራ በቀረበው የመጨረሻ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2027 ዓ. ም. ቀጣዩ የዓለም የወጣቶች ንግደት ወደ ኮሪያ መዲና ሴኡል እንደሚደረግ ይፋ ማድረጌ የሚታወስ ሲሆን፥ ከዚያ ጊዜ አስቀድሞ እንደ ጎሮጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. በሮም በሚከበረው የወጣቶች ኢዮቤልዩ ላይ “የተስፋ ተጓዦች” በመሆን እንድትገኙ ጋብዣችኋለሁ።

እናንተ እንደ ወጣቶች ዘወትር እንቅስቃሴ ላይ የምትገኙ የቤተ ክርስቲያን ደስተኛ ተስፋዎች ናችሁ። እጆቻችሁንም ይዤ በተስፋ ጎዳና ላይ አብሬአችሁ መራመድ እፈልጋለሁ። ስለ ደስታዎቻችን እና ተስፋዎቻችን እንዲሁም በሁሉም የሰብዓዊ ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የሚያጋጥማቸውን ሐዘን እና ጭንቀት ላካፍላችሁ እወዳለሁ (‘ደስታ እና ተስፋ’ ሐዋርያዊ ሠነድ ቁ. 1)። ለኢዮቤልዩ በዓል ዝግጅት በሚደረግባቸው በእነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ በቅድሚያ “በተስፋ ደስ ይበላችሁ” (ሮሜ 12፡12) በሚለው በቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ላይ እና ቀጥሎም “ጌታን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ አይደክሙም” (ኢሳ 40፡31) በሚለው የነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት ላይ እናሰላስል።

የዚህ ተስፋ መነሻ ምንድነው?

“በተስፋ ደስ ይበላችሁ” የሚለው ጥቅስ ቅዱስ ጳውሎስ የሮም ማኅበረሰብን ከባድ ስደት በደረሰበት ወቅት የሰጣቸው የማበረታቻ መልዕክት ነው። "በተስፋ ውስጥ ያለ ደስታ" በማለት ሐዋርያው የላከው መልዕክት፥ የኢየሱስ ክርስቶስ የፋሲካ ምስጢር ፍሬ እና የትንሣኤው ኃይል ነው። ይህም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስንገናኝ የሚገኝ ጉልበት እንጂ በጥረታችን፣ በዕቅዳችን ወይም በችሎታችን የሚገኝ አይደለም። ክርስቲያናዊ ደስታ እግዚአብሔር ለእኛ ያለንን ፍቅር ከማወቅ የሚገኝ ነው።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2011 ዓ. ም. በማድሪድ በተከበረው በዓለም የወጣቶች ፌስቲቫል ልምድ ላይ በማሰላሰል ሲናገሩ፥ “ደስታ የሚመጣው ከየት ነው? እንዴት ሊገለጽ ይችላል? በማለት ጠይቀው ነበር። በእርግጥ ይህን ጥያቄ ለመመለስ የሚያግዙን ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩንም ነገር ግን ዋናው በእምነት ላይ የተመሠረተ እርግጠኛነት ነው። ተፈላጊ ነኝ፤ በታሪክ መካከል ማከናወን ያለብኝ አንድ ተግባር አለኝ፤ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት አለኝ፤ ተወዳጅም ነኝ” ማለት እንደሚገባ ተናግረው፥ በመቀጠልም “ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀባይነት አለኝ የሚል ስሜት ሊኖረን ያስፈልጋል፤ ይህን በእርግጠኝነት የማውቀው እግዚአብሔር ከማንነቴ ጋር እንደ ተቀበለኝ ሳረጋግጥ ብቻ ነው፣ እንደ ሰው በመከራ ጊዜም ቢሆን በሕይወት መቆየቴ መልካም ነው። እምነት አንድን ሰው ከውስጥ ደስተኛ እንዲሆን ያደርገዋል።” (በሮም ለከፍተኛ ጳጳሳዊ ምክር ቤቶች የላኩት መልዕክት፤ 2011 እ.አ.አ)

የእኔ ተስፋ የት ነው?

ወጣትነት በተስፋ እና በህልም የተሞላ እንዲሁም ሕይወታችንን በሚያበለጽጉ በርካታ ውብ ነገሮች የሚቀሰቅስበት ጊዜ ነው። የእግዚአብሔር የፍጥረት ግርማን የምናይበት፣ ከጓደኞቻችን እና ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር ግንኙነትን የምንመሠርትበት፣ ከሥነ-ጥበብ፣ ከተለያዩ ባሕሎች፣ ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ጋር የምንገናኝበት፣ ለሰላም፣ ለፍትህ፣ ለወንድማማችነት እና ሌሎችም ብዙ መልካም ነገሮችን ለማየት ጥረት የምናደርግበት ጊዜ ነው። ወጣቶችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ተስፋ የሌለ በሚመስል ጊዜ ውስጥ ይገኛሉ። በሚያሳዝን ሁኔታ በርካታ እኩዮቻችሁ በጦርነቶች፣ በሃይለኛ ግጭቶች፣ ጉልበተኞች በሚያስፈራሩበት እና በሌሎች ችግሮች ውስጥ በመሆናቸው በተስፋ መቁረጥ፣ በፍርሃት እና በጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ። የፀሐይ ብርሃን በማይገባበት ጨለማ እስር ቤት ውስጥ እንዳሉ ይሰማቸዋል። ይህ አስደንጋጭ ሁኔታ በተለያዩ አገሮች ውስጥ በሚኖሩ ወጣቶች መካከል ራስን የማጥፋት ተግባር እንዲስፋፋ አድርጎታል። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረውን ደስታ እና ተስፋ እንዴት ልንለማመደው እንችላለን? በጎ ሥራን መሥራት በማንም ዘንድ ተቀባይነት እና ጥቅም እንደሌለው ተደርጎ ስለሚታሰብ ተስፋ የመቁረጥ ስጋት ከፍተኛ ነው። እንደ ኢዮብ፥ “እንግዲህ ተስፋዬ ወዴት ነው? ተስፋዬንስ የሚያይ ማን ነው?” (ኢዮብ 17:15) ብለን ራሳችንን እንጠይቃለን።

የሰውን አሳዛኝ ሁኔታ ስናስብ፥ በተለይም የንጹሃን ሰዎች ስቃይ፣ እኛም ከመጽሐፈ መዝሙረ ውስጥ አንዳንድ ዝማሬውችን በመድገም ጌታን፥ “ይህ ለምን ይሆናል?” ብለን ልንጠይቀው እንችላለን። እንደዚሁም ከእግዚአብሔር ጋር በመሆን የመልሱ አካል ልንሆንም እንችላለን። በእርሱ አምሳል የተፈጠረን በመሆናችን፥ ተስፋ ቢስ በሚመስሉ ሁኔታዎች ውስጥ ደስታን እና ተስፋን በመስጠት የፍቅሩ ምልክቶች ልንሆን እንችላለን። አንድ ወጣት አባት በታላቅ ችሎታው አስፈሪ እውነታን ወደ ቀልድ የቀየረበትን፥ “ሕይወት ውብ ናት” የሚለውን ፊልም አስታውሳለሁ። በዚህ ችሎታው ልጁ ነገሮችን “በተስፋ ዓይን” እንዲመለከት ያስችለዋል። ከማጎሪያ ካምፑ አስፈሪነት ይጠብቀዋል፤ ምስኪንነቱን በመጠበቅ የሰው ልጅ ክፋት የወደፊት ዕድሉን እንዳይወስድበት ይከለክላል። እንደነዚህ ያሉት ታሪኮች ልበ ወለድ ብቻ ሳይሆኑ በሰው ልጅ የክፋት ምሳሌዎች ውስጥ የተስፋ ምስክሮች በሆኑት በብዙ የቅዱሳን ሕይወት ውስጥ ሲከሰቱ እናያለን። ስለ ቅዱስ ማክስሚሊያን ማርያ ኮልቤ፣ ስለ ቅድስት ጆሴፊን ባኪታ፣ ስለ ብፁዕ ጆሴፍ እና ቪክቶሪያ ኡልማ እና ሰባት ልጆቻቸው የሕይወት ታሪክ ልናስብ እንችላለን።

በሰዎች ልብ ውስጥ ተስፋን የማፍራት ችሎታ በተመለከተ የቀድሞው ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ በሚያስደንቅ መንገድ ገልጸውታል፡- “አንድ ክርስቲያን ወይም የክርስቲያን ማኅበራት በማኅበረሰባቸው ውስጥ ቀላል በሆነ እና ሌላውን በማጎዳ መልኩ የእምነታቸውን ዘላቂ እሴቶች እና ተስፋ በስውር እና ባልተጠበቀ መንገድ ሊያሳዩ ይችላሉ” (ወንጌልን መስበክ ቁ. 21)።

ተስፋ፥ ትንሿ በጎ ሥነ-ምግባር ናት

ቻርለስ ፔጊ የተባለ ፈረንሳዊ ጸሃፊ፥ ስለ ተስፋ በገጠመው ግጥሙ መጀመሪያ ላይ፥ ስለ ሦስቱ ሥነ-መለኮታዊ በጎነቶች፥ እምነት፣ ተስፋ እና የፍቅር ሥራ አብረው እንደሚጓዙ ሦስት እህትማማቾች አድርጎ ተናግሯል። ከእነርሱም መካከል ትንሿ የሆነችው ተስፋ፥ ከሁለት ታላላቅ እህቶቿ ጋር የምትራመድ እና ከትንሽነቷ የተነሳ ጎልታ የማትታይ” በማለት ሲገልጻት፥ … እርሷ ትንሿ ተስፋ ሁሉንም የምትጎትት፥ እምነት ተጨባጭ የሆነውን ብቻ የሚያይ፣ የፍቅር ሥራ ተጨባጭ የሆነውን ብቻ የሚወድ፥ ነገር ግን ተስፋ ወደ ፊት የሚሆነውን የምትወድ ናት። …ሌሎች እንዲራመዱ የምታደርግ ተስፋ ናት፤ የምትመራቸውም እርሷ ናት፤ ተስፋ ሁሉንም በአንድነት እንዲጓዙ ታደርጋለች” (የሁለተኛው በጎነት ምስጢር)።

ተስፋ ትሁት እና ትንሽ ነገር ግን እጅግ አስፈላጊ እንደሆነች እኔም እርግጠኛ ነኝ። እስቲ ለአፍታ ያህል እናስብ። ያለ ተስፋ እንዴት መኖር እንችላለን? ቀኖቻችን ያለ ተስፋ ምን ሊመስሉ ይችሉ ነበር? ተስፋ ዕለታዊ ሕይወታችንን የምታጣፍት ጨው ናት።

ተስፋ፥ በሌሊት የሚያበራ ብርሃን ነው

በክርስትና እምነት ባሕል፥ ከብርሃነ ትንሳኤው እሑድ ቀደም ብሎ የሚውለው ቅዳሜ የተስፋ ቀን ነው። በስቅለተ ዓርብ እና በብርሃነ ትንሳኤው እሑድ መካከል ያለው ቅዳሜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ተስፋ በመቁረጡበት እና በብርሃነ ትንሳኤው ደስታቸውን በገለጹበት እሑድ መካከል የሚገኝ ቀን ነው። በዚህ መሠረት በሕማማት ሳምንት ውስጥ የሚውለው ቅዳሜ ተስፋ የሚወለድበት ቀን ነው። ይህ ቅዳሜ ዕለት ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ ወደ ሲኦል የወረደበትን በጽሞና የምታስታውስበት ቀን ነው። ይህንን ጌታ በብርሃኑ ጮራ ድቅድቅ ጨለማን ተሻግሮ መውጣቱን በሚገልጹ ቅዱሳት ምስሎች በኩል እናያለን። እኛ ወደ ሞት አዘቅት ስንወርድ እግዚአብሔር በርኅራኄ ዓይኑ ዝም ብሎ አያየንም። ወይም ከሩቅ ሆኖ አይጣራንም። ጨለማን በብርሃን እንደሚያሸንፈው እና ሲኦል በሚመስሉ ገጠመኞቻችን ውስጥ ብርሃን ሆኖ ይገባል (ዮሐ. 1፡5)። ‘ሱይዛ’ በተባለ የደቡብ አፍሪካ ቋንቋ የተዘጋጀ ግጥም ይህን በጥሩ ሁኔታ ይገልጸዋል፡- “ተስፋ ቢያልቅም በዚህ ግጥም አማካይነት ተስፋዬ ዛሬም ጽኑ ነው። ተስፋ የማደርገው በእግዚአብሔር ስለሆነ ዘወትር ይታደሳል። ሁላችንም አንድ እንደምንሆን ተስፋ አደርጋለሁ! መልካም ውጤት የምናይበት ጊዜ ቀርቧልና በተስፋ ጸንታችሁ ኑሩ።

በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሥር ጸንታ ስለ ቆመችው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተስፋ ካሰብን፥ መልካም የሆነው ሁሉ በአጠገባችን እንደሚገኝ እርግጠኛ ነው። ቅድስት ድንግል ማርያም የተስፋ እናት ናት። በቀራንዮ ላይ “በተስፋ ላይ ተስፋን በማድረግ” (ሮሜ 4፡18)፥ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ያወጀውን ትንሣኤ ለማመን አላመነታችም። እመቤታችን ቅድስት ማርያም የሕማማት ሳምንት ቅዳሜን በጽሞና፣ በፍቅር እና በተስፋ ተሞልታ የጠበቀች እና ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ በመሆኗ ለደቀ መዛሙርቱ ብርታትን አስገኝታለች።

የክርስቲያን ተስፋ ከንቱ አይደለም። እግዚአብሔር ልጆቹን ፈጽሞ እንደማይተው እና ለቃ ኪዳኑም ታማኝ በመሆኑ በፍቅር እና በእምነት ላይ የተመሠረተ እርግጠኝነት አለን። “በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፥ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል” (መዝ. 23፡4)። የክርስቲያን ተስፋ ሐዘንን እና ሞትን መካድ አይደለም። እርሱ ከእኛ የራቀ በሚመስልበት ጊዜም ዘወትር ከጎናችን የሆነው እና ከሞት የተነሣው የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር በዓል ነው። "ክርስቶስ ራሱ ታላቁ የተስፋ ብርሃን እና የሌሊት መሪያችን ነው። ምክንያቱም እርሱ 'የሚያበራ የንጋት ኮከብ' ነው" (ክርስቶስ ሕያው ነው፥ ቁ. 33)።

ተስፋን መንከባከብ

የተስፋ ነበልባል በውስጣችን ከተቀጣጠለ በኋላ በዕለት ተዕለት ኑሮአችን ጭንቀት፣ ፍርሃትና ጫና ሊጠፋ የሚችልበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። ነበልባል ወደ ታላቅ የተስፋ እሳት ለማደግ እየነደደ እንዲሄድ ‘ኦክስጅን’ ያስፈልገዋል። የዋህ የሆነው የመንፈስ ቅዱስ ንፋስ ተስፋችንን ያሳድገዋል። በዚህ የምንተባበርባቸው በርካታ መንገዶች አሉ።

ተስፋን መንከባከብ ይምንችለው በጸሎት ነው። ጸሎት ተስፋን ይጠብቃል፣ ያድሳልም። የተስፋ ጭላንጭል ወደ ነበልባልነት እንዲያድግ ያግዛል። "ጸሎት የተስፋ የመጀመሪያው ኃይል ነው። ስትጸልዩ ተስፋ ያድጋል፥ ወደፊት ይጓዛል” (የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፥ ግንቦት 20/2020 እ.አ.አ.)። መጸለይ ወደ ተራራ ጫፍ እንደ መውጣት ነው። መሬት ላይ ስንሆን ፀሐይ በደመና ልትሸፈን ትችላለች። ነገር ግን ደመናን ካለፍን በኋላ ብርሃኗ እና ሙቀቷ ይሸፍኑናል። በዙሪያችን ያሉ ነገሮች ሁሉ ጨለማ እና አስፈሪ በሚሆኑበት ጊዜ እንኳን ፀሐይ ግን ሁል ጊዜ ባለችበት ቦታ ሆና እናገኛታለን።

ውድ ወጣቶች ሆይ! በፍርሃት፣ በጥርጣሬ እና በጭንቀት ደመና እንደተከበባችሁ ሲሰማችሁ እና ፀሐይን ማየት ሳትችሉ ስትቀሩ ጸልዩ። የቀድሞው ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ፥ “በተስፋ በዳን” ባሉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ቁ. 32 ላይ፥ “ከእንግዲህ ማንም በማይሰማኝ ጊዜ እግዚአብሔር ዘወትር ይሰማኛል” በማለት ተናግረዋል። በተለይ በችግር ወቅት ውስጣችን ሲጨነቅ በየቀኑ ለጥቂት ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር እንሁን፡- “ነገር ግን ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን በጸጥታ ጠብቂ፥ ተስፋዬ ከእርሱ ዘንድ ናትና” (መዝ 62፡6)።

ተስፋ መንከባከብ የምንችለው በዕለት ተዕለት ውሳኔያችን ነው። በተስፋ እንድንደሰት ቅዱስ ጳውሎስ ያቀረበልን ግብዣ (ሮሜ 12፡12) በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ተጨባጭ ምርጫዎችን እንድናደርግ ይጠይቃል። ሁላችሁም በተስፋ ላይ የተመሠረተ የሕይወት ዘይቤ እንድትመርጡ አሳስባለሁ። አንድ ምሳሌ ብቻ ልስጥ፥ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተስፋን ከሚሰጡ ነገሮች ይልቅ አሉታዊ ነገሮችን ማካፈል ዘወትር ቀላል ይመስላል። ስለዚህ የእኔ ተጨባጭ ሃሳብ ይህ ነው፥ በእያንዳንዷ ቀን የተስፋ ቃልን ለሌሎች ለማካፈል ሞክሩ። በጓደኞቻችሁ እና በአካባቢያችሁ ባሉ ሰዎች መካከል የተስፋ ዘርን ለመዝራት ሞክር። “ተስፋ ትሑት በመሆኑ ከቀን ወደ ቀን የሚታነጽ በጎነት ነው…። በትንንሽ ሥራዎች አማካይነት በእኛ ውስጥ የሚሠራ የመንፈስ ቅዱስ የመጀመሪያ ፍሬ በውስጣችን መኖሩን በየቀኑ እናስተውል። (የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የማለዳ አስተንትኖ ጥቅምት 29/2019 እ.አ.አ.)

የተስፋ ችቦን ማብራት

አንዳንድ ጊዜ ከጓደኞቻችሁ ጋር በምሽት ስትወጡ ስልኮቻችሁን ለብርሃን ትጠቀሙታላችሁ። በትልልቅ ኮንሰርቶች ላይም በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች እነዚህን ዘመናዊ ሻማዎች ከሙዚቃው ጋር በማስማማት ሲያንቀሳቅሱ ማየት አስደናቂ ዕይታን ይፈጥራል። በሌሊት የሚበራ ብርሃን ነገሮችን በአዲስ መንገድ እንድናይ ያደርገናል። በጨለማ ውስጥም የተወሰነ ውበት ያበራል። በተስፋ ብርሃን ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲሁ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ሕይወታችን ይበራል። ከእርሱ ጋር ስንሆን ሁሉንም ነገር በአዲስ ብርሃን እናየዋለን።

ሰዎች ችግራቸውን ለማውራት ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሲመጡ የመጀመሪያ ጥያቄያቸው፥  “ይህን ችግር ከእምነት አንጻር እንዴት ትመለከተዋለህ?” ይሉ እንደ ነበር እንሰማለን። ነገሮችን በተስፋ ብርሃን ስናያቸው የተለዩ ሆነው እናገኛቸዋለን። እናንተም ነገሮችን በእምነት መንገድ መመልከት እንድትጀምሩ አበረታታችኋለሁ። ተስፋ ለሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰውና ክርስቲያኖች ከውስጥ በሚፈልቅ አዲስ ደስታ ተሞልተናል። ተግዳሮቶች እና ችግሮች ሁልጊዜም ይኖራሉ። ነገር ግን “በእምነት የተሞላ” ተስፋ ካለን፥ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሌላቸው ስለምናውቅ ልንጋፈጣቸው እንችላለን። በዚህ እኛም ለሌሎች ትንሽ የተስፋ ብርሃን ልንሆን እንችላለን።

እያንዳንዳችሁ እምነታችሁ ተጨባጭ፣ በእውነታ ላይ የተመሠረተ እና የወንድሞቻችን እና የእህቶቻችን ፍላጎት የሚሰማችሁ እስከሆነ ድረስ፥ ለሌሎች ብርሃን ልትሆኑ ትችላላችሁ። አንድ ቀን ከፍ ባለ ተራራ ላይ በክብር ብርሃን ሲለወጥ የተመለከቱትን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እስቲ እናስብ። እዚያው ቢቀሩ ኖሮ ለራሳቸው ብቻ ጥሩ ገጠመኝ ሆኖ ይቀርላቸው ነበር። ያዩትንም ለሌሎች ማካፈል አይችሉም ነበር። ነገር ግን ከተራራው ላይ መውረድ ነበረባቸው። እኛም እንደዚሁ ነን። ያለ ምክንያት በመሆኑ እግዚአብሔር ያዘጋጀልንን ጊዜ መውደድ እንጂ ከዚህ ዓለም መሸሽ የለብንም። ደስታን የምናገኝበት ብቸኛው መንገድ፥ እግዚአብሔር የሚሰጠንን ጸጋ ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ጋር በየቀኑ ስንካፈል ነው።

ውድ ወጣቶች ሆይ! ከሞት የተነሳውን የኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋ እና ደስታ ለሌሎች ለማካፈል ወደ ኋላ አትበሉ! በእናንተ ውስጥ የተቀጣጠለውን የብርሃን ጭላንጭል አሳድጉ፤ ለሌሎችም አካፍሉት። ለሌሎች ስታካፍሉት የበለጠ እንደሚያድግ ትገነዘባላችሁ! ክርስቲያናዊ ተስፋችንን እንደ ውስጣችን ስሜት ለራሳችን ብቻ ማድረግ አንችልም። ምክንያቱም ይህ ተስፋ ለሁሉም ነውና። በተለይ ከውጪ ፈገግታን አሳይተው ነገር ግን ተስፋን ከማጣት የተነሳ ውስጣቸው ቆስሎ የሚያለቅሱ ብዙ ሰዎች ስላሉ ወደ እነርሱ መቅረብ ያስፈልጋል። በግዴለሽነት እና በራስ ወዳድነት ባሕል እራሳችሁን መበከል የለባችሁም። በምትኖሩበት አካባቢ የኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋ የሚፈስበት እና የሚሰራጭበት ክፍት መንገድ ሆናችሁ ጠብቁ።

"ክርስቶስ ሕያው ነው! እርሱ ተስፋችን ነው፤ የእርሱ ተስፋ ወጣቶችን ወደ ዓለም ውስጥ በሚያስደንቅ ሁኔታ ያመጣቸዋል!” (ክርስቶስ ሕያው ነው፤ ቁ. 1)። እነዚህን ቃላት የተናገርኳችሁ የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ የወጣቶች ሲኖዶስ ከተካሄደ በኋላ ነበር። ሁላችሁም በተለይ በወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ የተሰማራችሁ በሙሉ፥ እ.አ.አ. በ2018 ዓ. ም. ይፋ የተደረገውን “ክርስቶስ ሕያው ነው” የሚለውን ሐዋርያዊ ምክር በድጋሚ እንድታነቡት አደራ እላለሁ። ሁኔታውን መርምረን ለዚያ ለማይረሳው የሲኖዶስ ጉባኤ ሙሉ ተግባራዊነት በተስፋ የምንሠራበት ጊዜ ደርሷል።

ሕይወታችንን በሙሉ የተስፋ እናት ለሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አሳልፈን እንስጥ። ደስታችን እና ተስፋችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በልባችን ይዘን ከሌሎች ጋር እንድንካፈል ታስተምረናለች። ውድ ጓደኞቼ! በምታደርጉት ጉዞ በእያንዳንዷ እርምጃ ትደሰቱ ዘንድ እባርካችኋለሁ! በጸሎቴም አብሬአችሁ ነኝ። እናንተም ለእኔ እንድትጸልዩልኝ አደራ እላለሁ።

ቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ባዚሊካ - ሮም፤  ኅዳር ጥቅምት 29/2016 ዓ. ም.

ትርጉም በዮሐንስ መኰንን

 

02 December 2023, 15:47