ቅዱስነታቸው በቅድስት ማርያም ባዚሊካ ውስጥ የብርሃነ ልደቱን ትዕይንት ያቀረቡ ሰዎችን በቫቲካ ሲቀበሉ ቅዱስነታቸው በቅድስት ማርያም ባዚሊካ ውስጥ የብርሃነ ልደቱን ትዕይንት ያቀረቡ ሰዎችን በቫቲካ ሲቀበሉ   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በብርሃነ ልደቱ ወቅት ስቃይ ላጋጠማት ቅድስት አገር ቅርብ መሆናቸውን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሮም በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ የብርሃነ ልደቱን ትዕይንት ያቀረቡት አባላትን በቫቲካን ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባሰሙት ንግግር፥ አባላቱ ያቀረቡት ትዕይንት ዋጋ ያለውና የሕጻኑ እግዚአብሔር የመገለጽ ምስጢር ልብን በማንቃት መደነቅን የሚፈጥ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዛሬዋ ቤተልሔም እና ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት የነበረችውን ቤተልሔምን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እነዚህ ሁለት ሃሳቦች በቦምብ ብርሃን መካከል የሚከበር የብርሃነ ልደቱ በዓል እና ለሰው ልጆች በሙሉ አዲስ የተስፋ ብርሃንን ያመጣ የብርሃነ ልደቱ በዓል በማለት ገልጸዋቸዋል።

ቅዱስነታቸው ቅዳሜ ታኅሳስ 6/2016 ዓ. ም. ረፋዱ ላይ፥ በሮም በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ የብርሃነ ልደቱን ትዕይንት ያቀረቡት አባላትን በቫቲካን በሚገኘው ጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ተቀብለው ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

"ብቻችሁን ልንተዋችሁ አንፈልግም!"

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዛሬይቱ ቤተልሔም እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደባት፣ በኖረባት፣ በሞተባት እና ከሞት በተነሳባት ምድር ለሚገኙ ነዋሪዎች በሙሉ የአብሮነት ሰላምታቸውን ልከዋል። ለአሥርተ ዓመታት ለቆሰለች እና ጭካኔ በተመላበት ጦርነት ውስጥ የምትገኝ ቅድስት አገርን በጸሎታቸው በማስታወስ ተጨባጭ ዕርዳታን በማድረግ አንድነታቸውን በመግለጽ ላይ እንደሚገኙ ለአባላቱ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ አባላቱ ከብርሃነ ልደቱ ትዕይንት ጋር በስቃይ ወደሚገኝ ወደ ቅድስት አገር ሕዝብ እንዲቀርቡ ጠይቀው፥ የቤተልሔም ስቃይ ለመካከለኛው ምሥራቅ እና ለመላው ዓለም ክፍት ቁስል እንደሆነ አስታውሰዋል።

በብዙ መከራ ውስጥ ከሚገኙ ከእነዚህ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር አብሮ መሆን ይገባል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ የብርሃነ ልደቱ ሰሞን ለእነርሱ የሕመም፣ የሐዘን፣ ያለ መነፈሳዊ ነጋዲያን የቀሩበት እና የብርሃነ ልደቱ በዓል የማይከበርበት ወቅት በመሆኑ ብቻቸውን ልንተዋቸው አንፈልግም በማለት ተናግረዋል።

ርህራሄ የሚገለጽበት

ከ 800 ዓመታት በፊት በቤተልሔም የሆነውን የብርሃነ ልደቱን ክስተት የሚገልጽ የብርሃነ ልደቱን ትዕይንት የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችኮስ ጣሊያን ውስጥ ግሬቾ በተባለ አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ ማዘጋጀቱ ይታወሳል። የቅዱሱን የፈጠራ ሥራ በባሕላዊ እይታ መመልከት እንደማይገባ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ በሕይወት በሚገኙ ሰዎች አማካይነት ማዘጋጀት የፈለገው ለምን እንደሆነ መጠየቅ እና እስከ ዛሬ ድረስ የቆየበትን ምክንያት ማስመር አስፈላጊ ነው ብለዋል።

“ቅዱስ ፍራንችስኮስ ይህን ያደረገው የክስተቱን ተጨባጭነት ለማሳየት ፈልጎ እንደ ነበር፣ በምስል ወይም በሐውልት ሳይሆን በእውነተኛ ሰዎች አማካይነት የኢየሱስ ክርስቶስ የመገለጡ እውነታ ጎልቶ እንዲታይ ስለፈለገ ነው” ብለዋል። የብርሃነ ልደቱን ትዕይንት በተጨባጭ ላቀረቡት አባላት የምተወው የመጀመሪያው ሃሳብ ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ሕያው የብርሃነ ልደቱ ትዕይንት ዋና ዓላማ፥ “ሕጻን ሆኖ የታየውን የእግዚአብሔር ምሥጢር ማድነቅ እና በልባችን ውስጥ ማንቃት ነው” በማለት አስረድተዋል።

 

16 December 2023, 15:30