በጋዛ በእስራኤል ወታደሮች እየተፈጸ የሚገኘው ውድመት በጋዛ በእስራኤል ወታደሮች እየተፈጸ የሚገኘው ውድመት   (AFP or licensors)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በጋዛ በሲቪሎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን አውግዘዋል: 'ጦርነት ነው፣ ሽብርተኝነትም ጭምር ነው አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጦርነት "ሽብርተኝነት" እንዲቆም ልባዊ ጥሪ አቅርበዋል እና የእስራኤል ወታደራዊ ጥቃት በጋዛ ቅዱስ ቤተሰብ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ላይ ያደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል፣ ይህም ሁለት ክርስቲያን ሴቶችን የገደለ እና የበጎ አድራጎት ሚሲዮናውያን ገዳም ያወደመ ተግባር በመሆኑ ቅዱስነታቸው ጥቃቱን አውግዘዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅድስት አገረን እያመሰ ያለው ጦርነት እንዲያበቃ እሁድ ዕለት ታኅሳስ 07/2016 ዓ.ም ተማጽነዋል ፣በተለይ በጋዛ በሚገኘው የቅዱስ ቤተሰብ ካቶሊካዊ ሰበካ ውስጥ ላሉ ክርስቲያኖች ጸሎት አቅርበዋል።

እሁድ እለት ቅዱስነታቸው በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ አስተንትኖ አድርገው ካበቁ በኋላ የመልአከ ሰላም ፀሎት ከደገሙ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ባስተላለፉት ሣማንታዊ መልእክት  “ያልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች የቦምብ ጥቃቶች እና የጥይት ዒላማዎች በሆኑበት” ከጋዛ አሳሳቢ ዜና ማግኘታቸውን ቀጥለዋል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በካቶሊክ ሰበካ ቅጥር ግቢ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት “ቤተሰቦች፣ ሕፃናት፣ ሕመምተኞች እና አካል ጉዳተኞች እና መነኮሳት እንጂ አሸባሪዎች በሌሉበት” የተፈጸመ ጥቃት በመሆኑ አውግዘዋል።

"የልጆች እናት የነበሩ ወይዘሮ ናሂዳ ካሊል አንቶን እና ልጃቸው ሳማር ካማል አንቶን ተገድለዋል እና ሌሎች ደግሞ ወደ መታጠቢያ ቤት ሲሄዱ በተኳሾች ቆስለዋል" ብለዋል።

“አንዳንዶች ‘ይህ ሽብርተኝነት ነው። ይህ ጦርነት ነው’ ይላሉ፣ አዎ ጦርነት ነው። ሽብርተኝነት ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው "ለዚህ ነው ቅዱሳት መጻሕፍት "እግዚአብሔር ጦርነትን  ሁሉ ያስቆማል ... ቀስትን ይሰብራል ጦርነትንም ያደቅቃል" (መዝሙር 46: 10) ይላል ስለዚህ ጦርነትን ያስቆም ዘንድ ስለ ሰላም ወደ እግዚአብሔር እንጸልይ” ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በጦርነት ምክንያት እየተሰቃዩ ያሉትን ሰዎች አስታውሰዋል።

“በጦርነት፣ በዩክሬን፣ በፍልስጤም እና በእስራኤል እንዲሁም በሌሎች የግጭት አካባቢዎች የሚሰቃዩ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን አንርሳ፥ የገና በዓል መቀራረብን የሰላም መንገዶችን ለመክፈት ያለውን ቁርጠኝነት ያጠናክርልን" ሲሉ ተማጽነዋል።

በጥቃቱ የተገደለችው ሳማር ካማል አንቶን
በጥቃቱ የተገደለችው ሳማር ካማል አንቶን

የእስራኤል ጦር በካቶሊክ ደብር ላይ ጥቃት ሰነዘረ

ቅዳሜ ዕለት የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ብቸኛ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ላይ ከባድ የቦምብ ድብደባ ፈጽመዋል።

የእየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ በሰጠው መረጃ መሰረት የእስራኤል ብሔራዊ የጦር ሰራዊት ታንክ ሮኬት በመተኮሱ የበጎ አድራጎት ሚሲዮናውያን ገዳም (የማዘር ትሬዛ ሲስተሮች ገዳም) በመምታቱ የሕንፃውን ጀነሬተር በማውደም እና በቤቱ ላይ ጉዳት ያደረሰውን ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ ተከትሎ  መግለጫ አውጥቷል።

ተጨማሪ ሁለት ሮኬቶች የማዘር ቴሬዛ እህቶች እንክብካቤ ሲያደርጉላቸው ለነበሩት 54 አካል ጉዳተኞች ገዳሙን መኖሪያ አልባ አድርጓቸዋል ተብሏል።

"ገዳሙ ከ54 በላይ አካል ጉዳተኞች የሚገኙበት ሲሆን ከጦርነቱ መጀመሪያ ጀምሮ የአምልኮ ስፍራ ተብሎ የተገለፀው የቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ አካል ነው" ብለዋል ፓትርያርኩ።

በጥቃቱ የተገድደሉት እናት ወይዘሮ ናሂዳ ካሊል አንቶን
በጥቃቱ የተገድደሉት እናት ወይዘሮ ናሂዳ ካሊል አንቶን

ሁለት ክርስቲያን ሴቶች ተገደሉ።

በዕለቱ አንድ እስራኤላዊ ተኳሽ በቅዱስ ቤተሰብ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የተጠለሉ ሁለት ክርስቲያን ሴቶችን ገደለ።

ነሂዳ ካሊል አንቶን አንድ በእድሜ ገፋ ያሉ የእድሜ ባለጸጋ ሴት እና ልጃቸው ሳማር ካማል አንቶን ከቤተክርስቲያኑ ህንፃ ወጥተው ወደ እህቶች ገዳም እየሄዱ እንደነበር ተዘግቧል። “አንደኛዋ ሌላዋን ደኅንነቱ ወደ ተጠበቀ ሥፍራ ለመውሰድ ስትሞክር ተገድላለች” ሲል መግለጫው ገልጿል።

ተኳሹ በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያሉትን እና ሌሎች ሰዎችን ለመከላከል የሞከሩ 7 ሰዎችን ተኩሶ ማቁሰሉ ተነግሯል። "ምንም ማስጠንቀቂያ አልተሰጠም፣ ምንም ማሳወቂያ አልተሰጠም” ብለዋል ፓትርያርኩ። "በቀዝቃዛ ደም የተገደሉት በቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ምንም አይነት ተዋጊዎች በሌሉበት የተፈጸመ አሳፋሪ ተግባር ነው" ሲል መግለጫው አክሎ ገልጿል።

 

18 December 2023, 12:06