ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የእሑዱን የእኩለ ቀን ጸሎት ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት እንደሚመሩት ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ዘወትር እሑድ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከሚሰበሰቡት ምዕምመናን ጋር የሚያደርሱትን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ሆነው እንደሚመሩት እና በጤናቸውም መሻሻል መታየቱን የቫቲካን መግለጫ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ማትዮ ብሩኒ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው እሑድ ኅዳር 23/2016 ዓ. ም. ከምዕመናን ጋር በቫቲካን የሚያደርሱትን ጸሎት ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት እንደሚመሩት እና ሥነ-ሥርዓቱም በቫቲካን መገናኛዎች በኩል በቀጥታ እንደሚሰራጭ አቶ ማትዮ ብሩኒ ገልጸው፥ ምዕመናኑም በአደባባዩ በተዘጋጁላቸው ግዙፉ “ስክሪኖች” አማካይነት እንደሚከታተሉት አክለው ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ላጋጠማቸው የጉንፋን ሕመም አስፈላጊውን የሕክምና ዕርዳታ በማግኘታቸው አሁን ምንም ዓይነት የትኩሳት ምልክት እንደማይታይባቸው እና ጤናቸውም መሻሻሉን የቫቲካን መግለጫ ጽ/ቤት ዳይሬክተር አቶ ማትዮ ብሩኒ ቅዳሜ ኅዳር 22/2016 ዓ. ም. ከቀኑ ሰባት ሰዓት ተኩል ላይ በሰጡት መግለጫ አሳውቀውዋል። ቅዱስነታቸው ባጋጠማቸው የጉንፋን ሕመም ምክንያት  የመተንፈስ እክል አጋጥሟቸው እንደ ነበር ይታወሳል።

በዚህም ምክንያት በሳምንቱ ውስጥ የሚያከናውኗቸውን ሐዋርያዊ ተግባራት ጨምሮ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዱባይ ከተማ በተዘጋጀው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ለመካፈል የነበራቸውን እቅድ መሰረዛቸው ሲታወስ፥ እርሳቸውን ወክለው ጉባኤውን በመካፈል ላይ የሚገኙት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ዛሬ ለጉባኤው ተካፋዮች ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል።

በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ የሚያቀርቡት ጸሎት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሮም በተከሰተው ድንገተኛ ብርድ ምክንያት፥ እሑድ ኅዳር 23/2016 ዓ. ም. ረፋዱ ላይ የሚያቀርቡትን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ሆነው እንደሚመሩት የቫቲካን መግለጫ ጽ/ቤት ዳይሬክተር አቶ ማትዮ ብሩኒ አስታውቀዋል።

ቅዱስነታቸው ያለፈው እሑድ  ያዘጋጁትን የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ለምዕመናኑ በንባብ ያቀርቡት የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ብራይዳ እንደነበሩ ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ በነበረው ሥነ-ሥርዓት መጀመሪያ እና መደምደሚያ ላይ ለምዕመናኑ አጭር ሰላምታ አቅርበው የእመቤታችን ጸሎት መድገማቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እሑድ ኅዳር 23/2016 ዓ. ም. ረፋዱ ላይ ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ሆነው የሚመሩት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በቫቲካን መገናኛዎች አማካይነት በቀጥታ እንደሚተላለፍ እና በአደባባዩ የሚሰበሰቡ ምዕመናንም በተዘጋጁት ግዙፉ “ስክሪኖች” አማካይነት የሚከታተሉ መሆኑን የቫቲካን መግለጫ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ማትዮ ብሩኒ ገልጸዋል።

 

 

 

02 December 2023, 18:02