የእስራኤል እና የፍልስጤም ጦርነት ያስከተለው ጥፋት የእስራኤል እና የፍልስጤም ጦርነት ያስከተለው ጥፋት  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከጦርነት ዘወትር ሽንፈት እንጂ ጥቅም የለውም በማለት አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ካቀረቡት ሳምንታዊው የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጥለው ባቀረቡት የሰላም ጸሎት ዩክሬንን፣ እስራኤልን እና ፍልስጤምን አስታውሰዋል። በአዳራሹ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባሰሙት አጭር ንግግርም፥ ጦርነት ዘወትር ሽንፈትን እንደሚያስከትል አስገንዘበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የሚሰቃዩትን ሰዎች በድጋሚ በማስታወስ ባሰሙት ንግግር፥ ጦርነት ዘወትር ሽንፈት እንጂ ጥቅም እንደሌለው ገልጸው፥ ከጦርነት የሚያተርፉት የጦር መሣሪያ አምራቾች ብቻ ናቸው በማለት አስረድተው፥ የማግለል እና የንቀት ባሕል ልንዋጋው ይገባል በማለት በሜክሲኮ ለሚገኘው የቴሌቶን ፋውንዴሽን ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቅርብ ቀናት ወዲህ ባጋጠማቸው የመተንፈሻ አካል ሕመም ምክንያት በእነዚህ ቀናት ከመላው ዓለም ለሚመጡ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና ለአገር ጎብኚዎች የሚያቀርቡትን ሐዋርያዊ አስተምህሮ እና ስላምታ የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ተወካይ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፊሊፖ ቻምፓኔሊ እንዲያቀርቡ መጠየቃቸው ሲታወስ፥ ቅዱስነታቸው በዓለም ዙሪያ ሰላምን ለተጠሙት ሰዎች በሙሉ ያላቸውን ቅርበት በገለጹበት መልዕክታቸው፥

በጦርነት ምክንያት የሚሰቃዩትን በተለይም የዩክሬን፣ የእስራኤል እና የፍልስጤም ሕዝቦችን በጸሎት እናስታውስ ብለው፥ ጦርነት ማንም አሸናፊ የማይሆንበት ሁሌም ሽንፈትን የሚያስከትል እና የጦር መሣሪያ አምራቾች ብቻ የሚያተርፉበት ነው በማለት አስረድተዋል።

በጋዛ ውስጥ የደረሰው ጥፋት
በጋዛ ውስጥ የደረሰው ጥፋት

በተለይም ዩክሬንን በማስመልከት ለፖላንድ ቋንቋ ተናጋሪ ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፥ በኡልማ ቤተሰብ የብጽዕና አዋጅ ላይ ለመገኘት ወደ ሮም የመጡ ነጋዲያን፥ መጭው እሁድ ለምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን በተለይም በስቃይ ውስጥ ለምትገኝ ዩክሬን በሚደረግ የጸሎት እና የዕርዳታ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ላይ ለሚሳተፉት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በዩክሬን ካርኪቭ አቅራቢያ በሩሲያ ሚሳኤል ለተገደሉት ሰዎች የተከናወነ የመቃብር ቁፋሮ ሥራ
በዩክሬን ካርኪቭ አቅራቢያ በሩሲያ ሚሳኤል ለተገደሉት ሰዎች የተከናወነ የመቃብር ቁፋሮ ሥራ

የአካፑልኮ ተጎጂዎች ለማገዝ የቀረበ ጥሪ

በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ የተገኙትን እና ከሜክሲኮ የመጡ የቴሌቶን ፋውንዴሽን አባላት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ሜክሲኮ ውስጥ በአካፑልኮ ግዛት ከአንድ ወር በፊት በአውሎ ነፋስ አደጋ ክፉኛ የተጎዱትን እና የአካል ጉዳተኞችን ማገዝ እንደሚገባ አደራ ብለው፥ የማግለል እና የንቀት ባሕል በመዋጋት የእያንዳንዱን ሰው ክብር እንጠብቅ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በሜክሲኮ፥ አካፑልኮ ውስጥ አውሎ ነፋስ ያስከተለው ውድመት
በሜክሲኮ፥ አካፑልኮ ውስጥ አውሎ ነፋስ ያስከተለው ውድመት

ለእግዚአብሔር የሚሰጠውን ሙሉ መታመን ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንማር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ ዘንድሮ ዓርብ ኅዳር 28/2016 ዓ. ም. የሚከበረውን የጽንሰታ ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፥  እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ፍቅር በመታመን የአዎንታ ምላሽ መስጠቷን በማስታወስ፥ በሁሉም ሥፍራ መልካምን ለማድረግ እና ወንጌላዊ ፍቅርን ለመመስከር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ላይ ካላት ሙሉ እምነት መማር ይገባል ብለዋል።

 

 

06 December 2023, 16:11