ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ልብን እየተንከባከብን ክፋትን መቃወም ይገባል!” አሉ
“ደግሞም ኢየሱስ ሕዝቡን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ ‘ስሙኝ፤ ሁላችሁም አስተውሉ፤ ከውጭ ወደ ውስጥ ገብቶ ሰውን የሚያረክሰው አንዳች ነገር የለም፤ ይልቁን ሰውን የሚያረክሰው ከራሱ ወደ ውጭ የሚወጣው ነገር ነው፤ ከውስጥ፥ ከሰው ልብ የሚወጡት ክፉ ሃሳብ፣ ምንዝር፣ ስርቆት፣ ሰው መግደል፣ ዝሙት ናቸው፤’” (ማር. 7:14-15፣ 21)
ክቡራት እና ክቡራን አድማጮቻችን፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ታኅሳስ 17/2016 ዓ. ም. ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! እንደምን አረፈዳችሁ! “በዛሬው የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እኩይ ምግባር እና በጎ ምግባር የሚሉ ርዕሦችን በአዲስ ም ዕራፍ መጀመር እፈልጋለሁ። ይህንንም በመጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ላይ በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የቀድሞ አያቶቻቸን ክፋትን እና ፈተናን በማስመልከት ካቀረቡት መጀመር እንችላለን። እንደ መልካም ሥፍራነቱ በተመሰለው በኤደን ገነት ውስጥ እባብ የፈተና ምልክት ሆኖ እንደ ገጸ ባሕርይ ታየ። እባብ ተንኮለኛ እንስሳ ነው፤ በዝግታ ይንቀሳቀሳል። አንዳንድ ጊዜ መኖሩንም ማወቅ እንኳን ይዳግታል። ምክንያቱም እራሱን አካባቢውን አስመስሎ ማቅረብ ስለሚችል ነው። በዚህ ምክንያት እጅግ አደገኛ ነው።
ከአዳምና ከሔዋን ጋር ንግግር ሲጀምር የጠራ እና ግልጽ የንግግር ችሎታ ያለው መሆኑንም ያሳያል። አንድ ሰው በሐሜት እንደሚናገር እንዲህ በማለት ይጀምራል፡- ሴቲቱን ወይም ሔዋንን፥ ‘በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ አንዳች እንዳትበሉ አዝዞአልን?’ በማለት ተንኮለኛ ጥያቄ አቀረበላት (ዘፍ 3፡1)። ጥያቄው ሐሰት ነው። እግዚአብሔር መልካምን እና ክፉን ለይተው ለማወቅ ከሚያስችል ከተወሰነ የዛፍ ፍሬ በቀር ወንድ እና ሴት በአትክልቱ ሥፍራው የሚገኙትን ፍሬዎች በሙሉ እንዲበሉ አዘጋጅቶላቸዋል ወይም አቅርቦላቸዋል። ይህ ክልከላ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ እንደሚተረጉሙት፥ የሰው ልጅ ምክንያታዊነትን እንዳይጠቀም ለመከልከል የታሰበ ሳይሆን የጥበብ መለኪያ ነው። ‘ገደብህን እወቅ! የሁሉ ነገር ጌታ እንደሆንክ አይሰማህ! ምክንያቱም ኩራት የክፋት ሁሉ መጀመሪያ ነው!’ እንደ ማለት ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር የቀድሞ አያቶችን የፍጥረት ጌቶች እና ጠባቂዎች አድርጎ ከማጽናታቸው በተጨማሪ ራሳቸውን የመልካም እና የክፉ ነገሮች ሁሉ ጌቶች እና ሁሉን ቻይ ነን ከሚለው ትምክህት ሊጠብቃቸው ይፈልጋል። ትምክህተኝነት ለሰው ልጅ ልብ በጣም አደገኛው ወጥመድ ስለሆነ በየቀኑ ልንጠነቀቀው ይገባል።
እንደምናውቀው አዳምና ሔዋን የእባቡን ፈተና መቋቋም አልቻሉም። እግዚአብሔር ያን ያህል ጥሩ አምላክ እንዳልሆነ እና እንዲገዙለት የሚፈልግ፣ ለእርሱ ተገዝተው እንዲቆዩ የሚፈልግ አምላክ የሚለው ሐሳብ ወደ አእምሮአቸው ውስጥ እንዲገባ አደረገ። ከዚህ የተነሳ የሁሉም ነገር ውድቀት ሆነ። ብዙም ሳይቆይ የቀድሞ አያቶቻችን ፍቅር ራሱን እንደሚሸልም እና ክፋትም በራሱ ላይ ቅጣት እንደሚያመጣ ተገነዘቡ። ስህተት እንደሠሩ ለመገንዘብ የእግዚአብሔር ቅጣት አያስፈልጋቸውም። እስካሁን ድረስ ሊኖሩ የሚችሉበትን መልካም እና ያማረ ዓለም እንዲፈርስ ያደረገው የራሳቸው ድርጊት ነው። አማልክት እየሆኑ እንደሆነ ይሰማቸው ወይም ያምኑ ነበር። ነገር ግን በምትኩ ራቁታቸውን እንደሆኑ ተገነዘቡ። በጣም መፍራት ጀመሩ። ምክንያቱም የሰው ልጅ ትዕቢት ወደ ልቡ ውስጥ ዘልቆ ከገባ፥ ክፋት መፀነስ ከሚችለው ብቸኛው ምድራዊ ፍጡር እራሱን መጠበቅ አይችልምና።
በእነዚህ ሃሳቦች መሠረት፥ መጽሐፍ ቅዱስ ክፋት በሰው ውስጥ በአስደናቂ ሁኔታ የሚጀምር ሳይሆን ነገር ግን አንድ ድርጊት በልቡ ውስጥ አስቀድሞ እንደ ተጀመረ፣ ስለዚህ ጉዳዩ ማሰብ ሲጀምር እና በምናባዊ ሃሳብ እና በማታለያዎቹ ተጠምዶ እንደሚያልቅ ያስረዳል። የአቤል ግድያ የጀመረው በቅድሚያ ድንጋይ በመወርወር ሳይሆን ቃኤል በልቡ ውስጥ የያዘው ቂም ወደ ተንኮል በመቀየሩ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እግዚአብሔርም፥ ‘መልካም ነገር አድርገህ ቢሆን ኖሮ ተቀባይነት አይኖርህም ነበርን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፥ ፍላጎቷም ወደ አንተ ነው፥ አንተ ግን በእርስዋ ልትሰለጥንባት ይገባል’ በማለት የሰጣቸው ምክሮች ከንቱ ሆኑ። (ዘፍ 4፡7)
አንድ ሰው ከዲያብሎስ ጋር ፈጽሞ መደራደር የለበትም። እርሱ ብልጥ እና አስተዋይ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስን ለመፈተን እንኳን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶችን ተጠቅሟል! በማይታይ የጥሩነት ጭንብል ውስጥ ክፋትን መደበቅ ይችላል። አንድ ሰው ክፉ መንፈስ ወደ ልቡ ውስጥ ሊገባ በሚሞክርበት ጊዜ ዘወትር ንቁ ሆኖ ቀዳዳዎችን ወዲያው መዝጋት ያለበት ለዚህ ነው። ሊደርስባቸው የሚችለውን አደጋ በቀላል ስለሚመለከቱት እና ማሸነፍ ስለማይችሉ ብቻ አንዳንድ ሰዎች በአደንዛዥ ዕጽ፣ በአልኮል እና በቁማር ሱሰኝነት ይወድቃሉ። በጥቃቅን ጦርነቶች የጠነከሩ መስሎ ይታያቸዋል። ይልቁንም መጨረሻቸው ለኃያሉ ጠላት ሰለባ መሆን ነው። ክፋት ሥሩን በውስጣችን ሲሰድ እና እኩይ ተገባሩ ስም ሲያገኝ ለማጥፋት የማይቻል አስቸጋሪ አረም ይሆናል። አንድ ሰው ከዚህ ሁሉ ነጻ የሚሆነው መራራ ትግል በማካሄድ ብቻ ነው።
ስለዚህ የዛሬውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮን ይህን በማለት እንደመድማለን፥ አንድ ሰው ልቡን መጠብቅ አለበት። ዓለምን ትተው በጸሎት እና በወንድማዊ በጎነት ለመኖር ወደ በረሃ ከወረዱ በርካታ አባቶች የምናገኘው ምክር ይህ ነው። እነርሱ እንደሚሉት በረሃው ብዙ ጦርነቶችን የምናሸንፍበት ቦታ ነው። በርሃ በዓይን የምናያቸውን፣ በምላስ የምንናገራችውን እና በጆሮአችን የምንሰማቸውን ክፉ ነገሮች የምናሸንፍበት ቦታ ሲሆን፥ የመጨረሻ እና ከሁሉም በጣም ከባድ የሆነው ከልብ ጋር የምንደርገው ጦርነት ነው። ክርስቲያን በአእምሮ እና በልብ ውስጥ የሚመጡ ሃሳቦችን እና ፍላጎቶችን እየተጋፈጠ እራሱን በጥበብ ይጠብቃል። እነዚያ ሃሳቦች እና ፍላጎቶች ከየት እንደሚመጡ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወይስ ከጠላት እንደሚመጡ ለማወቅ እራሱን ይጠይቃል። ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚመጡ ከሆነ ሊቀበለው ይገባል። ምክንያቱም የደስታ ምንጮች ናቸው። ነገር ግን ከጠላት ዘንድ የመጡ ከሆነ እንክርዳድ እና በካይ ናቸው። ዘሮቹ ትንሽ መስለው ቢታዩንም አንድ ጊዜ ውስጣችን ከገቡ በኋላ አድገው ትላልቅ የክፉት እና የሐዘን ቅርንጫፎች ሆነው እናገኛቸዋለን። መንፈሳዊ ስኬት የሚገኘው ውጊያውን አስቀድመን ስንጀምር እና ሁል ጊዜ ልባችንን ከክፉ ነገር ስንጠብቅ ነው።”