ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ሥራ አጥነት ሰብዓዊ ክብርን የሚጎዳ መሆኑን አስገነዘቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሥራው ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጨናነቀ የመጣውን የግንባታ መስክ በማስታወስ፥ ይህም የዕድገት እና የለውጥ እምቅ አቅም የሆነውን ወጣቱን ትውልድ የሚያጋጥም ተግዳሮት እንደሆነ አስረድተዋል።
ቅዱስነታቸው በሮም በሚገኝ የማህበራቱ ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀውን አውደ ጥናት ለተሳተፉት አባላት ባስተላለፉት መልዕክት፥ አውደ ጥናቱ ስኬትን የመፈለግ ስሜትን እንደሚያበረታታ ገልጸው፥ በሌላ ወገንም ከሥራ አጥነት ወይም ቋሚ ሥራን ካለማግኘት ሊመጣ የሚችለውን ባዶነት የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከሥራ አጥነት የሚመጣ ባዶነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሥራ አጥነት የሚመጣው ባዶነት የብዙዎችን በተለይም የወጣቶችን ሕይወት እንደሚያቃውስ ገልጸው፣ ሥራ አጥነት የሰው ልጅ ክብር እንደሚጎዳም አስረድተዋል።ቅዱስነታቸው በተጨማሪም፥ ግለሰቦች ቋሚ ያልሆነ እና ያልተረጋጋ የሥራ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው በሥራ ልምድ፣ በጊዜያዊ ሥራ እና በትርፍ ጊዜ ሥራ መካከል ሚዛኑን ያልጠበቀ የሥራ ስምሪትን በመፍጠር ሊያስከትል በሚችለው ያልተረጋጋ ውጤት ላይም አሰላስለዋል።
ሥራ አጥነት ብዙ ወጣቶችን ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርግ ወይም ሌሎች ዕድሎችን እንዳይፈልጉ የሚያስገደድ ጎጂ ተጽዕኖ መሆኑን ህብረተሰቡ እንዲገነዘብ ቅዱስነታቸው ጋብዘው፥ “ሥራ ልዩ እና የማይተካ የተስፋ ጥሪ ነው” በማለት አስገንዝበዋል።
ሰብዓዊ ክብር እና መረጋጋት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፥ ወጣቶች ወደ ሥራው ዓለም ከመግባታቸው በፊት መብታቸውን ለማስጠበቅ የሚያደርጉትን ትግሎች ጠቅሰው፥ “ጥራት ያለውን ትምህርት ለመቅሰም እና ወደ ሙያዊ ብቃት ለመድረስ የሚያግዙ መሠረታዊ ነገሮችን ለማሟላት የሚደረግ ጉዞ የማያቋርጥ ትግል የሚጠይቅ ከሆነ በግንባታው ዘርፍ ወደሚገኝ የሥራ ዕድል እንዴት መድረስ ይቻላል?” በማለት ጠይቀዋል።
ብዙዎች ህልማቸውን እውን እንዳያደርጉ እንቅፋት የሚሆንባቸው የባዶነት ስሜት መኖሩን የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በሥራው ዓለም ውስጥ የሚታዩ አስተማማኝ ያልሆኑ ጉዳዮችን ለመዳሰስ የሚያግዝ የድጋፍ መመሪያ ሊኖር እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተዋል።
“ወጣቶች፥ ጭንቀትን እና የባዶነት ስሜትን እንዲያሸንፉ የሚያግዝ ክፍል ሊኖር ይገባል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ይህም ከሚደርስባቸው አደጋ ሊያድናቸው እንደሚችል በመግለጽ፥ በጣሊያን የክርስቲያን ሠራተኞች ማኅበራት አንድነት ለሚያራምደው "LaborDì" ለተሰኘ ተነሳሽነት ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
ከመጠን ያለፈ ሥራ
የሥራውን ዓለም በሚመለከት ሌላ አስቸጋሪ ሁኔታ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከዛሬው ፈጣን የሥራ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ከፍተኛ ጫና እና ጭንቀት አስታውሰው፥ ማንኛውንም መስዋዕትነት ክፍሎ ትርፍን ለማሳደድ የሚደረግ ጥረት፣ በሥራው መስክ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን አደጋ እና እንደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ሮቦት ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የሚፈጥሩትን አደጋዎች አስታውሰዋል።
የትብብር አስፈላጊነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የ"LaborDì" አውደ ጥናት ተሳታፊዎች በሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ተስፋ እንዳይቆርጡ በማበረታታት፥ በተግባር ዕቅዳቸው መካከል የትውልድ ራዕይን በማጎልበት ወጣቶች የሥራ ገበያውን እንዲገነዘቡ በማድረግ፣ ልዩ ልዩ ዕድሎችን እና አስፈላጊ ክህሎቶችን እንዲያገኙ የሚያስችሉ ተጨባጭ ድጋፎችን በማድረጋቸው አመስግነዋል።
ቤተ ክርስቲያን ከትምህርት ተቋማት፣ ከመንግሥት አካላት፣ ከሥራ ማኅበራት፣ ከሥራ ፈጣሪዎች እና ከኩባንያዎች ጋር የተረጋጋ እና ዘላቂ ግንኙነቶችን በመመሥረት ለምትጫወተው ሚና አጽንኦት ሰጥተው፥ ማኅበራቱ በግንባታው ዘርፍ የሥራ ዕድልን በመክፈት ለብዙ ወጣቶች ተስፋን በመስጠት እና የሥራ ውበትን እንዲገነዘቡ ማድረግ እንደሚገባ በማሳሰብ መልዕክታቸው ደምድመዋል።