ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ስደተኞችን ለመርዳት ለተደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት ምስጋናቸውን አቀረቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከታህሳስ 3-5/2016 ዓ. ም. ድረስ በጄኔቫ ስዊዘርላንድ ለተካሄደው ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የስደተኞች መድረክ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “የስደተኞችን ችግር በጋራ ኃላፊነት ለመፍታት ያለንን ግልጽ ቁርጠኝነት የሚያሳይ የተስፋ ምልክት ነው” ብለዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት ለስብሰባው ተሳታፊዎች ታኅሳስ 3/2016 ዓ. ም. ያስተላለፉት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ናቸው።
መድረኩ በየአራት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን፥ በስደተኞች ጉዳይ ላይ የሚመክር በዓለም ትልቁ ስብሰባ እንደሆነ ይታወቃል። መድረኩ በዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉዳይ ላይ የተቀመጡትን ዓላማዎች ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ሲሆን፥ እነዚህም በተቀባይ ሀገራት ላይ ያለውን ጫና ማቃለል፣ የስደተኞችን በራስ መተማመን ማሳደግ፣ የሦስተኛ ሀገር መፍትሄዎች ተደራሽነትን ማሳደግ እና በትውልድ አገራት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል የሚሉትን ያካትታል። ስብሰባውን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ጋር በመተባበር በጂኔቭ ስዊዘርላንድ ያዘጋጁት የኮሎምቢያ፣ የፈረንሳይ፣ የጃፓን፣ የዮርዳኖስ እና የኡጋንዳ መንግሥታት እንደሆኑ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለማችን ውስጥ ብዙ አዎንታዊ ምልክቶች እንደሚታዩ ተናግረዋል, አገሮች እና የአካባቢ ማኅበረሰቦች ድንበራቸውን እና ልባቸውን ለስደተኞች ክፍት በማድረግ፥ በባሕር ላይ የሚጠፋውን ሕይወት ከሞት ማትረፍ እና መልካም አቀባበል እንዲደረግላቸው አሳስበዋል። "መተባበር ለዓለም አቀፍ ችግሮች ቁልፍ መፍትሄ ነው" ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ስደተኞችን መርዳት ሕይወታቸውን ለመለወጥ ብለው ለሚሄዱበት አገር ያለውን ጥቅም አስታውሰዋል።
በቤታቸው የመቆየት ነጻነት ወይም ስደት
ዜጎች በአገራቸው መቆየት ወይም ወደ ሌላ አገር መሄድን መምረጥ እውቅና ያለው ነፃነት ሊሆን ይገባል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሁሉም ሰው በትውልድ አገሩ ውስጥ የተከበረ ሕይወት የመምራት ዕድል ሊኖረው ይገባል ብለዋል።
ዛሬ ወደ 114 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች በግጭት፣ በአመጽ፣ በስደት፣ ሃይማኖትን በሚያጋጥ መከራ እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በግዳጅ በመፈናቀል ላይ እንደሚገኙ በምሬት የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የእኛ ምላሽ እነዚህን ውስብስብ እና አንገብጋቢ የሆኑ ድንገተኛ አደጋዎችን በበቂ ሁኔታ ለመፍታት ዕድል አላገኘንም፤ በሚያሳዝን ሁኔታ፣ “ከለላን በመፈለግ ወይም መልካም የወደፊት ተስፋን በመፈለግ ላይ ሳሉ በየብስና በባሕር ላይ ለሚጠፋው ሥፍር ቁጥር ለሌለው ሕይወት ማዘናችንን እንቀጥላለን” ሲሉ ተናግረዋል።
ሕይወትን ለማዳን ቅድሚያ መስጠት
ቅድሚያ የሚሰጠው ዋናው ጉዳይ የሰውን ሕይወት ከሞት አደጋ መጠበቅ እና ማዳን ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ብዛትን ከሚጠቁሙ ከእነዚ ቁጥሮች በስተጀርባ የራሳቸው ታሪክ እና ስቃይ ያላቸው የሰው ልጆች እንደሚገኙ ማየት አለብን” ብለዋል።
ስደተኞች ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ በሚደረግበት ጊዜም ደህንነታቸው የተጠበቀ እና ማንም ሰው ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊደርስበት፥ አልፎ ተርፎም የሞት አደጋ ሊያጋጥመው ወደሚችልበት አካባቢ እንዲመለስ መገደድ የለበትም ብለዋል። በተመሳሳይም ስደተኞችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ አገራት በራቸውን የሚያንኳኩትን ተቀብሎ ማስተናገድ፣ አገልግሎቱን ማስተዋወቅ እና ከማኅበርሰቡ ጋር ለማዋሃድ መጣር አለባቸው ብለዋል።
የስደተኞች መብቶች እና ግዴታዎች
አንገብጋቢ የምግብና የመጠለያ ፍላጎቶችን ከማሟላት በተጨማሪ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚኖሩበትን ማኅበረሰብ ለመርዳት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አሳስበው፥ አክለውም “ስደተኞች ዕርዳታን የሚፈልጉ ብቻ ሳይሆኑ መብት እና ግዴታ ያለባቸው ሰዎች ናቸው” ሲሉ አስታውሰዋል።
ተሰጥኦአቸው እና ክህሎታቸው ለተቀባይ ማኅበረሰቦች ጠቃሚ እና የተመሰገነ ግብዓት ሊሆን እንደሚች እና ስደተኞችን የመፍትሄው አካል በማድረግ በሚኖሩበት አካባቢ እንደ ሰው ማደግ እና አስተዋጽኦዋቸውን ማበርከት ይችላሉ" ብለዋል።
የወንድማማችነት ባህልን መምረጥ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ “እንደ ሰው ልጅ የወንድማማችነት ባህልን ወይም የግዴለሽነት ባህልን” መምረጥ በምንችልበት የመጀመሪያ ደረጃ ላይ እንገኛለን ብለው፥ አክለውም “ታሪክ የሥልጣኔ መቋረጥ አደጋን ለመከላከል ሕሊናን በማለፍ ፈተና ውስጥ ይገኛል” ብለዋል።
በዓለም አቀፍ የስደተኞች ፎረም ላይ ሁሉም ተሳታፊዎች በማኅበረሰቦች እና በአገሮች መካከል የወንድማማችነት እና የአብሮነት መርሆዎችን እንደገና የማረጋገጥ ዕድሉን እንዲጠቀሙ አደራ ብለዋል።