ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙርነት ደስታ እንደገና ሊሰማን ይገባል!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ጥር 5/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጸሎት ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በዕለቱ የቅዱስ ወንጌል ምንባብ ላይ በማስተንተን ቃለ ምዕዳናቸውን አቅርበዋል። በጣሊያን ከሚገኙ የተለያዩ ሀገረ ስብከቶች የመጡ ምዕመናንን ጨምሮ ከልዩ ልዩ አገራት ለመጡ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር የመሆን ደስታ እንደገና ሊሰማን ይገባል ብለዋል። ክቡራት ክቡራን፥ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እሑድ ጥር 5/2016 ዓ. ም. በዕለቱ የቅዱስ ወንጌል ምንባብ ላይ በማስተንተን ያሰሙት ቃለ ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን:-

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፥ መልካም ሰንበት ይሁንላችሁ! የዛሬው የቅዱስ ወንጌል ምንባብ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ጋር መገናኘቱን ይገልጻል። (ዮሐ. 1፡35-42)። ይህ ትዕይንት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እኛም ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘንበት ቀን እንድናስታውስ ይጋብዘናል። እያንዳንዳችን ከኢየሱስ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነው በልጅነት፣ በጉርምስና፣ በወጣትነት ወይም በጎልማሳነት ዕድሜ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ክርስቶስን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘሁት መቼ ነው? ይህን በትንሹም ቢሆን ለማስታወስ ሞክሩ። ይህን ካስታወሳችሁ በኋላ እርሱን በመከተል ያገኛችሁትን ደስታ እንደገና በማደስ እራሳችሁን ጠይቁ። ኢየሱስን መከተል ማለት የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን ማለት ነው። የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን ምን ማለት ነው? በዛሬ የቅዱስ ወንጌል ምንባብ መሠረት ሦስት ቃላትን ልንወስድ እንችላለን። እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስን መፈለግ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መሆን እና ኢየሱስ ክርስቶስን ለሌሎች መስበክ የሚሉት ናቸው።

በቅድሚያ መፈለግ የሚለውን ቃል እንመለከት። ለአጥማቂው ምስክርነት ምስጋና ይግባውና ሁለት ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል ጀመሩ። ኢየሱስን ሲከተሉት አየና፥ ‘ምን ትፈልጋላችሁ?’ ሲል ጠየቃቸው። (ቁ. 38) ይህ ጥያቄ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያቀርብላቸው የመጀመሪያው ጥያቄ ነበር። ከሁሉ አስቀድመው ውስጣቸውን በሚገባ ተመልክተው በልባቸው ውስጥ ስለሚገኙ ፍላጎቶች እራሳቸውን እንዲጠይቁ ይጋብዟቸዋል። "ምን ፈልገህ ነው?" ብሎ ይጠይቃቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን በማሳት ወደ ራሱ መጥራት አይፈልግም። ከአንገት በላይ ተከታዮችንም አይፈልግም። ኢየሱስ ክርስቶስ የሚፈልገው እራሳቸውን የሚጠይቁ እና በቃሉ እንዲፈተኑ የሚፈቅዱ ሰዎችን ነው። ስለዚህ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን በመጀመሪያ ኢየሱስን መፈለግ ያስፈልጋል። ከዚያም የተከፈተ ልብ ሊኖራችሁ ይገባል። ኢየሱስን የሚፈልጉ ሰዎች የጠገበ ወይም የተደላደለ ልብ ሊኖራችሁ አይገባም።

የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት በሁለተኛው ቃል መሠረት የሚፈልጉት ምን ነበር? ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መሆንን ነው። የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ስለ እግዚአብሔር የሚነገር ዜናን ወይም መረጃን፣ ምልክቶችን ወይም ተአምራት መመልከት አልፈለጉም። ነገር ግን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘትን፣ መሲሑን ለማግኘት፣ ከእርሱ ጋር ለመነጋገር፣ ከእርሱ ጋር ለመቆየት እና እሱን ለመስማት ይፈልጉ ነበር። ስለዚህ የመጀመሪያው ጥያቄያቸው የሚሆነው ምንድነው? ‘የት ነው የምትኖረው?’ የሚል ነው (ዮሐ. 1:38)። ኢየሱስ ክርስቶስም ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ ጋር እንዲቆዩ ጋበዛቸው። ‘ኑና እዩ’ አላቸው (ዮሐ. 1:39)። ከእርሱ ጋር መቆየት፣ ከእርሱ ጋር መኖር ለኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በጣም አስፈላጊው ነገር ነው። ባጭሩ እምነት መላምት ወይም ንድፈ ሐሳብ ሳይሆን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘት ነው። እምነት ኢየሱስ ክርስቶስ የሚኖርበትን ቦታ ለማየት መሄድ እና ከእርሱ ጋር መኖር ማለት ነው። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘት እና ከእርሱ ጋር መሆን ማለት ነው።

ኢየሱስን መፈለግ፣ ከእርሱ ጋር መሆን እና ሦስተኛው እና የመጨረሻው ኢየሱስ ክርስቶስን ለሌሎች መመስከር የሚል ነው። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን ፈልገውት ከእርሱ ጋር በመጓዝ ምሽቱን በሙሉ ከእርሱ ጋር አሳለፉ። ከዚያም ተመልሰው ስለ እርሱ ለሌሎች መናገር ጀመሩ። ኢየሱስን መፈለግ፣ ከእርሱ ጋር መቆየት እና ስለ እርሱ ለሌሎች ማወጅ። በሕይወቴ ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስን እፈልገዋለሁ? ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እቆያለሁ? ኢየሱስ ክርስቶስን ለሌሎች ለመስበክስ ድፍረት አለኝ? ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበት አጋጣሚ በጣም ኃይለኛ ተሞክሮ ነበር። ስለዚህም ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ያንን ጊዜ ዘወትር ያስታውሱታል። ጊዜውም ወደ አሥር ሰዓት ገደማ ነበር’ (ዮሐ. 1:39)። ይህም የዚህን ገጠመኝ ኃይል እንድንመለከት ያስችለናል። ደቀ መዛሙርቱም ልባቸው በደስታ ተሞልቶ ስለ ነበር የተቀበሉትን ስጦታ ቶሎ መግለፅ እንደሚያስፈልግ ተሰማቸው። በእርግጥም ከሁለቱ መካከል አንዱ የሆነው እንድሪያስ የሆነውን ነገር ለወንድሙ ለማካፈል ቸኮለ።

ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሆይ! እኛም ዛሬ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘንበትን ዕለት እናስታውስ። እያንዳንዳችን በቤተሰባችን ውስጥ ሆነ በውጭ ከሰዎች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘንባቸው አጋጣሚዎች ይኖሩናል። ኢየሱስ ክርስቶስን ያገኘሁት መቼ ነው? መቼ ነው ጌታ ልቤን የነካው? እኛም ዛሬ ኢየሱስ ክርስቶስን የምንወድ፣ እርሱን ዘወትር የምንፈልግ ደቀ መዛሙርቱ ነን ወይንስ የልማድ እምነት ያለን ሰዎች ነን? ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዴት በጸሎት መቆየት እንዳለብን፣ ከእርሱ ጋር እንዴት በጸጥታ መቆየት እንዳለብን እናውቃለን? በኋላም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የመገናኘትን ውበት ለሌሎች የማወጅ ፍላጎት አለን?

ኢየሱስ ክርስቶስን ዘወትር እንድንፈልግ፣ ከእርሱ ጋር እንድንሆን እና እርሱን ለሌሎች የምንሰብክበትን ፍላጎት የኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ ደቀ መዝሙር የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትስጠን።”

 

15 January 2024, 15:05