ቢያንስ አንድ ሰው የተገደለበት በኢስታንቡል የሚገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን	ቢያንስ አንድ ሰው የተገደለበት በኢስታንቡል የሚገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን   (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ኢስታንቡል ውስጥ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አወገዙ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ጥር 19/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልዓከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት ባሰሙት ንግግር፥ በኢስታንቡል ከተማ በሚገኝ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል። በተጨማሪም በኢስታንቡል የሚገኝ ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት ተወካይ እና የቁንስጥንጥንያ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማሲሚሊያኖ ፓሊኑሮ፥ ከጥቃቱ ጀርባ ያለው እውነትን ተጠንቶ እንዲታወቅ ባለሥልጣናትን ተማጽነው፥ ጥቃቱ በሃይማኖች መካከል ያለውን አለመቻቻል ያመለክታል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ዕለት ለምእመናኑ ባሰሙት ንግግር፥ በቱርክዬ መዲና ኢስታንቡል በሚገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታጣቂዎች የአንድ ሰው ሕይወት በማጥፋት በርካቶች ላይ ያደረሱትን የመቁሰል አደጋን አውግዘዋል።

በኢስታንቡል ከተማ ውስጥ በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በማድረስ ላይ በሚገኙ ምዕመናን ታጣቂዎች ጥቃት በማድረስ አንድ ሰው ገድለው በርካቶችን ማቁሰላቸውን በኢስታንቡል የሚገኝ የሐዋያዊ ጽሕፈት ቤት ተወካይ እና የንቁስጥንጥንያ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ ብጹዕ አቡነ ማሲሚላኖ ፓሊኑሮ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸው፥ የአገሪቱ ባለሥልጣናት በተፈጸመው አሳዛኝ ድርጊት ላይ ተወያይተው ከጀርባው ያለውን እውነት እንዲያገኙ ተማጽነዋል።

ጥቃቱ በሃይማኖቶች አለመቻቻል ምክንያት የተፈጸመ ይመስላል

እሑድ ጥር 19/2016 ዓ. ም. ጠዋት በኢስታንቡል ከተማ ዳርቻ በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምእመናን በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ እንደ ነበሩ ብጹዕ አቡነ ማሲሚላኖ ፓሊኑሮ አስረድተዋል። ብጹዕነታቸው አክለውም፥ ምዕመናኑ ምጽዋዕት በሚያቀርቡበት ሰዓት  ሁለት የታጠቁ ሰዎች ብዙ ጥይቶችን እየተኮሱ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ መግባታቸውን አስታውሰዋል።

በዚያን ጊዜ ከምእመናኑ መካከል የአእምሮ ጤና ችግር ያለበት የሚመስል አንድ ሰው ድርጊቱን በመቃወም ምላሽ ለመስጠት በድፍረት መነሳቱን አብራርተዋል። ታጣቂዎቹ ይህን ሰው በመግደል ምላሽ እንደሰጡ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት በሰጡት መረጃ ገልጸው፥ ለዚህ ድርጊት ተጨባጭ ምክንያት እስካሁን አለመታወቁን እና ሊረጋገጥ አለመቻሉን አስረድተው፥ ነገር ግን እስካሁን የሚቀርቡት አስተያየቶች በሃይማኖቶች መካከል በተፈጠረው አለመቻቻል ምክንያት እንደሆነ ይጠቁማሉ ብለዋል።

"ማኅበረሰቡ በድንጋጤ ውስጥ ይገኛል"

“ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ደንግጧል" ያሉት ብጹዕ አቡነ ማሲሚላኖ ፓሊኑሮ፥ ምንም እንኳን ምዕመናኑ በአደጋው የሞተውን ሰው የቆሰሉ ምዕመናንን በጸሎት በማስታወስ ኅብረታቸውን እየገለጹላቸው ቢገኙም በከፍተኛ ንድጋጤ ውስጥ መውደቃቸውን ገልጸው፥ የአገሪቱ ባለሥልጣናት የዚህን አደጋ እውነተኛ መንስኤ ፈልገው እንዲያገኙ እንጠይቃለን” ብለዋል።

በኢስታንቡል የሚገኝ ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት ተወካይ እና የቁንስጥንጥንያ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማሲሚሊያኖ ፓሊኑሮ በማጠቃለያቸው፥ የተገደለውን ግለ ሰብ በሐዘን በማስታወስ በአገሪቱ ለሚገኝ ክርስቲያን ማኅበረሰብ እና ካቶሊካዊ ምዕመናን በሙሉ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ተማጽነዋል።

 

29 January 2024, 16:33