ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የካቶሊክ እና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት ለኅብረት እንዲጸልዩ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የጋራ ምክር ቤቱ የተመሠረተበትን 20ኛ ዓመት በማስመልከት በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በምስራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ዓለም አቀፍ የነገረ መለኮት የጋራ ውይይት ያካሄዱትን አባላትን ዓርብ ጥር 17/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለዋል።
በዓለም ዙሪያ ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጉ አባላት ያሉት የምስራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጥንታዊ የክርስትና ባሕል እንዳሏቸው ሲታወቅ፥ ለመጀመሪያዎቹ ሦስት የአንድነት ጉባኤዎች እውቅና በመስጠት በክርስቶሳዊ ምርምር ቀጣይነት ባለው የጋራ ርዕሠ ጉዳይ ላይ ውይይት በማካሄድ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓርብ ጥር 17/2016 ዓ. ም. ለምክር ቤቱ አባላት ባደረጉት ንግግር፥ ለኅብረት አገልግሎት እና በብዙ የዓለማችን ክፍሎች እየተስፋፋ የመጣውን የሰላም እጦት ለመቋቋም ያለመታከት እንዲጸልዩ እና በርትተው እንዲሠሩ አደራ ብለዋል።
የበጎነት፣ የእውነት እና የሕይወት ውይይት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም፥ ምክር ቤቱ ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ የአንድነት ጉዞን ለማካሄድ የተራመዷቸውን ሦስት የማይነጣጠሉ መንገዶችን አስታውሰው፥ እነርሱም የበጎነት፣ የእውነት እና የሕይወት ውይይቶች መሆናቸውን አስታውሰዋል።
የበጎነት ውይይቱ በምክር ቤቱ ከተካሄደው የእውነት ውይይት ጋር አብሮ እንደሚሄድ ገልጸው፥ በተለምዶ እርስ በርስ የመገናኛ እና የአንድነት መንገድ የነበሩትን የጉብኝት እና የመልዕክት ልውውጥን የሚያጠቃልል መሆኑን አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለይ ባለፉት ዓመታት የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ የማላንካራ ሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና የሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ያደረጓቸውን የወንድማማችነት ጎብኝቶችን አስታውሰዋል።
በልዩነት መካከል አንድነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም፥ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ውስጥ ከምስራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በማሰላሰል፥ በብዝሃነት ውስጥ ያለው አንድነት ያስገኘውን ትልቅ ሃብት ጠቁመዋል።
በተለይም ወጣት ካህናትና መነኮሳት በየዓመቱ በመካከላቸው የእርስ በእርስ ጉብኝቶችን በማካሄድ ለትምህርት ወደ ተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እንደሚሄዱ ጠቁመው፥ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን በማደስ በስምምነት እንድትጓዝ እንደሚያደርጋት፣ የሕብረት ጎዳናን በማሳየት ለወጣቶች ጥበብን፣ ለአባቶች ትንቢትን የመናገር ችሎታን እንደሚሰጣቸው ተናግረው፥ የሕይወት ውይይት በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ በመታገዝ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ወደ ሙሉ አንድነት መድረስ ይቻላል
የጋራ ምክር ቤቱ በ20ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ለእግዚአብሔር ምስጋና የሚያቀርብበት ጊዜ እንደሆነ፣ አብያተ ክርስቲያናት ወደ ሙሉ አንድነት መድረስ ብቻ ሳይሆን አስቸኳይ እና አስፈላጊም እንደሆነ እና ዓለም በዚህ እንደሚያምን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፥ ምክር ቤቱ በአሁኑ ጊዜ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ባላት ሚና ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፥ የምክር ቤቱ አባላት ሥራቸውን ለእመቤታችን ቅድስት ማርያም አደራ በማቅረብ ወደ እርሷ ይቀርብ የነበረውን የሚከተለውን ጥንታዊ ጸሎት አብረው እንዲደግሙ ጋብዘዋል፥
የእግዚአብሔር እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ! ወደ ጥበቃሽ ሥር እንቀርባለን። በችግር ጊዜ ልመናችንን አትናቂ፥ የተባረክሽ ድንግል ሆይ! ዘወትር ከአደጋ ሰውሪን፤ አሜን!