በሱዳን ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት ያስከተለው ቀውስ በሱዳን ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት ያስከተለው ቀውስ   (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጦርነት የሚሰቃዩ የሱዳን እና የሰሜን ሞዛምቢክ ሕዝቦችን በጸሎት አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ የካቲት 10/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባሰሙት ንግግር በሱዳን እና በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተቋም ላይ የእሳት ቃጠሎ አደጋ በተፈጸመበት ሰሜናዊ ሞዛምቢክ ውስጥ ሰላምን ለማስፈን የዓለም መሪዎች ግፊት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ጦርነት ሞትን እና ጥፋትን ብቻ የሚያስከትል ትርጉም የለሽ በመሆኑ ሰዎች ጦርነት እንደ ሰለቻቸው እና ጦርነት ምን ጊዜም ቢሆን ችግርን ሊፈታ በፍፁም አይችልም” ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል። እሑድ የካቲት 10/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው ካቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ ባሰሙት ንግግር ሱዳን ውስጥ ግጭት ከተቀሰቀሰ 10 ወራትን እንዳስቆጠረ አስታውሰው፥ የዓለም መሪዎች ግጭቶች እና ጦርነቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ሰላምን ለማስፈን የበኩላቸውን ግፊት እንዲያደርጉ በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

"በሕዝብ እና በአገር የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትለውን ጦርነት የሚያካሂዱ ተዋጊ ወገኖች ጦርነትን እንዲያቆሙ በድጋሚ ጥሪ አቀርባለሁ" ብለው፥ የወደፊቷ ሱዳንን ለመገንባት የሰላም መንገዶች በፍጥነት እንዲገኙ እንጸልይ" ብለዋል።

በሰሜናዊ ሞዛምቢክ ውስጥ የተቀሰቀሰው ሁከት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞዛምቢክ ሰሜናዊ የካቦ ዴልጋዶ ክልል መከላከያ በሌላቸው ሰዎች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት፣ በመሠረተ ልማት ላይ የሚደርሰውን ውድመት እና የጸጥታ ችግርን በቁጭት ተናግረው፥ ማዜዜ በተባለ አካባቢ የሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ካቶሊክ ሚሲዮን በእሳት መጋየቱንም ጠቁመዋል። በሞዛምቢክ የቺዩር አውራጃ አስተዳዳሪ አቶ ኦሊቬራ አሚሞ፥ ታጣቂዎች በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን እና የበርካታ ሰዎች ቤቶችን ማውደማቸውን ገልጸዋል።

“በጦነት ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች ሰላም እንዲወርድ እንጸልይ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአፍሪካ አህጉር በሚገኙ ሌሎች አካባቢዎች እና እንዲሁም በዩክሬን እና በቅድስት አገር በጦርነት የሚሰቃዩ ሰዎችን በጸሎት በማስታወስ፥ “ጦርነት ዘወትር የሽንፈት ምልክት ነው” ሲሉ አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በመጨረሻም፥ “ጸሎት ውጤት ያለው በመሆኑ በተጨባጭ ለሰላም የቆመ አዕምሮ እና ልብ እንዲሰጠን እግዚአብሔርን እንለምነው” ሲሉ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

በሱዳን ሰቆቃው ቀጥሏል

በሱዳን ውስጥ የሚካሄደውን አረመኔያዊ ግጭት ለማስቆም ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በሀገሪቱ ውስጥ ውጊያው እንደቀጠለ ነው። ሱዳን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከሚያዝያ ወር 2023 ዓ. ም. ጀምሮ በሱዳን ጦር ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች መካከል አሰቃቂ የትጥቅ ግጭቶችን እያካሄደች ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሁለቱም ወገኖች ግጭቱን አነሳስተዋል ሲሉ እርስ በርሳቸው ሲወነጅሉ ቆይተዋል።

የሱዳን ጦር ከፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኦምዱርማን ግዛት ዘልቆ መግባቱ ታውቋል። ኦምዱርማን በናይል ወንዝ ማዶ ለምትገኝ የሱዳን ዋና ከተማ የካርቱም መንትያ ከተማ ተደርጋ ትቆጠራለች።

እሁድ ዕለት ከአገሪቱ የወጡ ዘገባዎች እንዳመለከቱት፥ የሱዳን ጦር በከተማው ደቡባዊ ክፍል ከሚገኙ  ኃይሎቹ ጋር መቀላቀሉን ገልጸው ይህ ኃይል ላለፉት አሥር ወራት በፈጥኖ ደራሽ ኃይል ተከብቦ የቆየ መሆኑን ገልጸዋል። በሱዳን በተቀሰቀሰው ግጭት ከ25 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ጠያቂ እንዲሆኑ  እና ወደ ሌሎች አገሮች የተሰደዱትን 1.6 ሚሊዮን ሰዎችን ጨምሮ ስምንት ሚሊዮን ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓቸዋል።

የሰላም ጥረቶች

ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ግጭቱን ለማስቆም እንደገና ውይይት መጀመራቸው ታውቋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው፥ የሱዳን ልዩ መልዕክተኛው አቶ ራምታኔ ላምራ በፖለቲካ እና በሽምግልና ጥረቶች ዙሪያ ለሰላም የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር ከአፍሪካ እና ከሌሎች አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በቅርብ ለመሥራት እየሞከረ እንደሚገኙ ገልጿል።

ዲፕሎማቱ የፖለቲካ ሂደቱን እንደገና ለማስጀመር በአፍሪካ ቀንድ፣ በአውሮፓ እና በባህረ ሰላጤው ዋና ዋና ከተሞች ሰፋ ያለ ጉብኝት ማድረግ ጀምረዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከዚህ ቀደም፥ እየተባባሰ የመጣው የሱዳን የእርስ በርስ ግጭት በአጎራባች አገራት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጾ ብዙዎቹም የራሳቸውን ችግሮች ለመቋቋም ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ማሳወቁ ይታወሳል።

 

 

19 February 2024, 16:36