በ82 ዓመት ዕድሜያቸው ያረፉትን የናሚቢያው ፕሬዚደንት ሄግ ጋይንጎብን በ82 ዓመት ዕድሜያቸው ያረፉትን የናሚቢያው ፕሬዚደንት ሄግ ጋይንጎብን   (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በናሚቢያው ፕሬዝደንት ህልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በ82 ዓመት ዕድሜያቸው ያረፉትን የናሚቢያው ፕሬዚደንት ሄግ ጋይንጎብን በማስታወስ የሐዘን መግለጫ መልዕክታቸውን ልከዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የ82 ዓመቱ የናሚቢያ መሪ አቶ ሄግ ጋይንጎብ ባለፈው ሳምንት ማረፋቸውን ተከትሎ በላኩት የቴሌግራም መልዕክት፥ ፕሬዝደንቱ በትጋት ያበረክቷቸውን የአገልግሎት ዓመታት አስታውሰዋል።

ፕሬዚደንት ሄግ ጋይንጎብ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ጥር 26/2016 ዓ. ም. ሲሆን፥ የዕረፍታቸው ዜና የተሰማው ጽሕፈት ቤታቸው የካንሰር ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ካሳወቀ ከሦስት ሳምንታት በኋላ እንደሆነ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጋይንጎብ ተተኪ ለሆኑት ለክቡር አቶ ናንጎሎ ምቡምባ በላኩት የቴሌግራም መልዕክታቸው የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፥ የጋይንጎብ ቤተሰብ፣ የናሚቢያን መንግሥት እና ሕዝቡን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሱት ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቴሌግራም መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ የሟቹን ፕሬዚደንት ነፍስ ልዑል እግዚአብሔር በምሕረቱ እንዲቀበል፥ ለአገሪቱ ሕዝቦችም መለኮታዊ ቡራኬን ከመጽናናት እና ሰላም ጋር በጸሎታቸው ተማጽነዋል።

 

10 February 2024, 16:41