ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ለእግዚአብሔር ሥራ ቦታ እንዲሰጡ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ የገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ቀንን ለ28ኛ ጊዜ ባከበረችበት ዓርብ ጥር 24/2016 ዓ. ም. ባስተላለፉት መልዕክት፥ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ሁል ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ በመነሳሳት ከቅዱስ ወንጌል ጋር በተጣጣመ መልኩ እግዚአብሔርን የመናፈቅ መንፈስ እንዲያሳድጉ አደራ ብለዋል።
ዓመታዊ በዓሉ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1997 ዓ. ም. በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የተጀመረ ሲሆን፥ የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ የተወሰደበትን ቀን በምታከብርበት ጥር 24 እንደሆነ ይታወቃል። ለዚህ ዓመት የተመረጠው መሪ ሃሳብም፥ "የተስፋ ነጋዲያን በሰላም ጎዳና ላይ" የሚል እንደሆነ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በቀረበው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ለተገኙት ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ የሐዋርያዊ ሕይወት ማኅበራት አባላት እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2025 ዓ. ም. የሚከበረውን የኢዮቤልዩ በዓል ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ በተዘጋጀ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ለተገኙት አባላት ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ በዓሉን በትዕግስት እና በጸሎት በመጽናት መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበው፥ ውስጣዊ ሕይወትን በመንከባከብ እና ከቅዱስ ወንጌል ጋር በሚስማማ መንገድ የሕይወት ብርሃን እና ተስፋ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን መቀበል እንደሚገባ ጋብዘዋል።
ንቃት እና ጽናት
በትንቢተ ሚልክያስ 3:1 ላይ “እናንተም የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ ቤተ መቅደሱ ይመጣል” የሚለውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የመንፈስ ቅዱስ ብርሃን የበራላቸው ስምዖን እና ሐና፥ በእናቱ ማርያም ታቅፎ ወደ ቤተመቅደስ የገባው ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ መገንዘባቸውን አስታውሰዋል።
በነቢዩ ሚልክያስ በተነገረው የጌታ መምጣት ትንቢታዊነት ላይ በማሰላሰል ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥በትዕግስት፣ በመንፈሳዊ ንቃት እና በጸሎት የሚተጉትን ሁለቱን ማለትም ስምዖንን እና ሐናን ማየት መልካም ነው ብለዋል። “በዕድሜ የገፉ ቢሆኑም ነገር ግን በልባቸው ወጣት ናቸው” ብለዋል።
“ስምዖን እና ሐና በተስፋ ለመጠበቅ መቻላቸው፥ ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮች በሞላበት ዓለም ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች ዓይኖቻቸውን በእግዚአብሔር ላይ እንዲያደርጉ የሚያመልክት ነው” ብለዋል። “በሕይወት ጉዞ ውስጥ መከራ እና ብስጭት አጋጥሟቸዋል፤ ነገር ግን አልተሸነፉም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በሕጻኑ ኢየሱስ ላይ ሲያሰላስሉ ጊዜው እንደ ደረሰ እና ትንቢቱም ፍጻሜውን ያገኘ መሆኑን በማወቅ የአሕዛብ መሲሕ መጥቶአል ብለው ይሹት ነበር” ብለዋል።
የአምላክን የማያቋርጥ ሕልውና ለማወቅ ከመጣር ይልቅ በዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ የተጠመዱ ክርስቲያኖች እንደሚያሳስቧቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ልብ እንዲተኛ ከፈቀዱ መንፈስም እንደሚተኛ ገልጸው፥ ይህም ነፍስን በማደንዘዝ ተስፋን በጨለማ እና በብስጭት ውስጥ እንዲቆልፉ ያደርጋል ብለው፥ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያቱ ልባቸውን ክፍት አድርገው እግዚአብሔርን መጠበቅ እንዳለባቸው አደራ ብለዋል።
በንቃት መጠበቅ የሚገባቸው እንቅፋቶች
የመጠባበቅን ችሎታን የሚያደናቅፉ ሁለት እንቅፋቶችን ለይቶ ማወቅ እንደሚገባ አሳስበው፥ የመጀመሪያው፣ ድካም አድናቆትን የሚተካበት፣ ምሬትም ምስጋናን የሚያሸፍንበት የውስጥ ሕይወት ቸልተኝነት ነው ብለዋል። ሁለተኛው እንቅፋት ከዓለማዊ የአኗኗር ዘይቤ ጋር መላመድ እንደሆነ ገልጸው፥ ይህም ፈጣን እርካታን መፈለግ ነው ብለዋል። እንደ ዛሬው ዓለማዊነት ዘመን ፍጥነትን መቀነስ፣ ፈቃደኝነትን የሚጠይቅ ፈተና እንደሆነ ገልጸው፥ ዝምታ በተወገደበት እና በጠፋበት ዓለም ውስጥ በተስፋ መጠባበቅ ቀላል እንዳልሆነ ገልጸው፥ በዚህ ላለመሸነፍ በውስጣችን ለእግዚአብሔር ሥራ ቦታ መስጠትን እንደሚገባ፥ ይህንንም ለማድረግ የጠፋውን ጸጋ መልሶ ማግኘት እና በውስጣዊ ሕይወት ወደ አስደሳች የትሕትና፣ የዝምታ እና የምስጋና መንፈስ መመለስ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።
የዓለማዊነት መንፈስ ወደ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት የግል ሕይወት እንዲሁም ወደ ቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ እንዳይገባ በማሳሰብ ተስፋን በንቃት የመጠባበቅ መንፈስ ማዳበር እንደሚገባ ጥሪ አቅርበው፥ በጸሎት እና በታማኝነት መጎልመስ ከሁሉም በላይ በእግዚአብሔር መታመንን እንደሚያሳድግ እና እርሱ ሁል ጊዜ በማንገምተው መንገድ የሚመጣ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል።