ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ የወንጌል ተልዕኮ ሳይታክቱ የሚወጡት አገልግሎት እንደሆነ አስገነዘቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው የተልዕኮ ቀንን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ በተጠቀሰው የሠርግ ግብዣ ምሳሌ ላይ በማስተንተን፥ ንጉሡ ለአገልጋዮቹን "ስለዚህ ወደ ጎዳናዎች ሂዱ እና ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሠርጉ ግብዣ ጥሩ” ማለቱን አስታውሰዋል።
“ሂዱና ጋብዟቸው!”
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንጉሡ ለአገልጋዮቹ የሰጠው ትዕዛዝ መሠረት በማድረግ፥ የተልዕኮውን ምንነት የሚገልጹ ሁለት ቃላትን በመጥቀስ፥ እርሱም ለተልዕኮ መነሳት እና ሌሎችንም መጋበዝ የሚሉት እንደሆኑ አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በእያንዳንዱን ቃል በማስተንተን ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ተልዕኮ
ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ግብዣን የሚያቀርቡበት፥ የጠፋውን በግ ለመፈለግ የእግዚአብሔር አብ መልዕክተኛ እና መልካሙ እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሄደ፥ ሕዝቦች ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኙ እና አንድነት እንዲኖራቸው ለመጋበዝ መውጣት ነው” ብለዋል።
የንጉሡን ግብዣ በማስመልከት ሲናገሩ፥ “እግዚአብሔር ከሰጠው ተልዕኮ ያላነሰ ሌላ አስፈላጊ ነገር መኖሩን ማየት እንችላለን” ብለዋል። “መገመት እንደምንችለው አገልጋዮቹ የንጉሡን ግብዣ በጥድፊያ ሳይሆን በታላቅ አክብሮት እና ደግነት መፈጸማቸውን በማስታወስ፥ በዘመናች ያሉ ክርስቲያኖችም እንዲሁ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበው፥ “በውስጣቸው ባለው የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ በሆነው በደስታ፣ በታላቅ ክብርና በበጎነት ወንጌልን ለመስበክ መጠራታቸውን ገልጸዋል።
የጋብቻ ድግስ
የጋብቻ ድግስን በማስመልከት የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሌሎች ሁለት የተልዕኮ ገጽታዎች መኖራቸውን አስታውሰው፥ እነዚህም ከመጨረሻው ዘመን እና ቅዱስ ቁርባን ጋር የተያያዙ እንደሆኑ፥ የንጉሡ ግብዣ ከሰማያዊው ግብዣ ጋር የተያያዘ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የመጨረሻው የመዳን ምሳሌ ነው ብለዋል።
ብዙ የጥንት ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስ በቅርብ ዳግም እንደሚመጣ የማመናቸውን እውነታን በመጥቀስ፥ የሚሲዮናዊነት ቅንዓት ለእነርሱ ኃይለኛ የፍጻሜ ዘመን ገጽታ እንደ ነበር ገልጸው፥ በዚህም ወንጌልን የመስበክ አጣዳፊነት መገንዘባቸውን አስረድተዋል። “ዛሬም ቢሆን ይህንን አመለካከት መጠበቅ አስፈላጊ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በተመሳሳይ መንገድም ቀጣዩ ሕይወት አሁንም በቅዱስ ቁርባን ግብዣ ላይ አስቀድሞ የተገለጸ ነው በማለት” ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተናግረዋል። ስለዚህም በወንጌል ተልዕኮአችን በኩል ለሰዎች ሁሉ የምናቀርበው የፍጻሜ ግብዣ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃሉ፣ በሥጋው እና በደሙ ከሚመግበን ግብዣ ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል።
'ሁላችንም ወደ ግብዣው ተጠርተናል'
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተልዕኮን ቀን በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት የመጨረሻ ክፍል፥ ንጉሡ ሁሉም ሰው ወደ ሠርጉ ግብዣ እንዲመጣ ባቀረበው ጥሪ ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ “ማንም ሳይቀር ሁሉም ወደ ሠርጉ ግብዣ ይምጣ” ያለው የተልዕኮው ዋና ልብ ነው ብለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርትም ሰዎች ምንም ዓይነት ማኅበራዊም ሆነ ሥነ-ምግባራዊ ደረጃ ይኑራቸው ለሁሉም ከልብ ይጨነቁ እንደ ነበር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል።
በምሳሌው ላይ ንጉሡ አገልጋዮቹ ያገኙትን ሰው ሁሉ፥ መልካሞችም ሆኑ ክፉዎች፣ ድሆችን፣ አካለ ጎደሎዎችን ዓይነ ስውራንን እና አንካሶችንም እንዲሰበስቡ ማታዘዛቸውን ጠቁመው፥ “ለሁሉም ሰው የሚሆን ተልዕኮ የሁሉንም ሰው ቁርጠኝነት ይፈልጋል” ብለዋል። ይህም ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ሚስዮናዊ ለመሆን የበለጠ ሲኖዶሳዊት መሆን እንዳለባት የሚያመለክት መሆኑን ገልጸው፥ “ሲኖዶሳዊነት በመሠረቱ ሚስዮናዊ እንደሆነ፥ የወንጌል ተልዕኮም ዘወትር ሲኖዶሳዊ እንደሆነ በመግለጽ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድሮ የተልዕኮ ቀንን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉትን መልዕክት ደምድመዋል።