ካርዲናል አንጄሎ፥ ጳጳሳት በተልዕኮአቸው እንዲበረቱ ከቅዱስነታቸው ምክር መቀበላቸውን ገለጹ

በመካከለኛው ጣሊያን የላዚዮ ክፍለ ሀገር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት፥ በየሦስት ዓመቱ ወደ ቫቲካን የሚደረገውን የብጹዓን ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉብኝት በማካሄድ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ተገናኝተዋል። የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ደ ዶናቲስ ከቅዱስነታቸው ጋር ያደረጉትን ውይይት በማስመልከት በሰጡት አስተያየት፥ ውይይቱ ግልጽ እና ፍሬያማ በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ ብጹዓን ጳጳሳቱ በሐዋርያዊ አገልግሎታቸው እንዲበረቱ ከቅዱስነታቸው የማበረታቻ ምክር መቀበላቸውን ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ውይይቱም በእውነተኛ የሲኖዶሳዊነት መንገድ፥ ብጹዓን ጳጳሳቱ ከካህናት እና ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ሊኖራቸው በሚገባው አንድነት ላይ ያተኮረ እንደ ነበር ታውቋል። ከመጋቢት 9/2016 ዓ. ም. ጀምሮ በቫቲካን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ያካሄዱት የላዚዮ ክፍለ ሀገር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት፥ የጉብኝታቸው ማጠቃለያ ዕለት በነበረው ዓርብ መጋቢት 13/2016 ዓ. ም. ከቅዱስነታቸው ጋር በነበራቸው ቆይታ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ግልጽ እና ፍሬያማ እንደነበር ገልጸው፥ ከሁሉም በላይ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸው የወንጌል ተልዕኮ አቅጣጫን እንዲከተል በማለት ቅዱስነታቸው መጋበዛቸውን አስረድተዋል።

ብጹዓን ጳጳሳቱ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ያደረጉትን ፍሬያማ ውይይት በማስመልከት የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ እና የሮም እና አካባቢው ከተሞች ሀገር ስብከት ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ደ ዶናቲስ በቫቲካን የዜና አገልግሎት በኩል በሰጡት መግለጫ፥ ከቅዱስነታቸው ጋር ያደረጉት ውይይት እርስ በርስ የመቀራረብ አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ እንደ ነበር አስምረውበታል።

“በጸሎት አማካይነት ከእግዚአብሔር ጋር በእውነት መገናኘት መቀራረብ ይቻላል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ደ ዶናቲስ በመግለጫቸው፥ “በብጹዓን ጳጳሳቱ መካከል ያለው ኅብረት ትክክለኛ የሲኖዶሳዊነት አካሄድ እና የአንድነት ጉዞ ምልክት ነው” በማለት ተናግረው፥ “በተጨባጭ እና የእውነተኛ አባትነት ከሁሉም በላይ ከካህናቶቻችን ጋር መቀራረብ እንዲኖር የሚያደርግ ነው” በማለት አስረድተዋል።

ጳጳሳቱ እና ከምዕመናኖቻቸው ጋር ያላቸው አንድነት

“የብጹዓን ጳጳሳት ተግባር በእርግጥ ከቅዱሳን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ጋር መቀራረብ ነው” በማለት የተናገሩት የሮም እና አካባቢው ከተሞች ሀገር ስብከት ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ደ ዶናቲስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “አንድ ጳጳስ ለእግዚአብሔር ሕዝብ እረኛ ሊሆን ይገባል” በማለት የሰጡትን ምክር ጠቅሰው፥ “ጳጳስ በምዕመናን መካከል ቀድሞ የሚሄድ፥ የሚቆም ወይም ወደ ኋላ የሚመለስ ካለ ለመርዳት የተመረጠ ነው” በማለት ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል። 

 

23 March 2024, 16:04