ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ትዕግስት ለኢየሱስ ፍቅር አሳማኝ ምስክርነት የሚሰጥ መሆኑን አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ለተገኙት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ረቡዕ መጋቢት 18/2016 ዓ. ም. አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በሳምንታዊው አስተምህሮአቸው፥ ትዕግስት ለኢየሱስ ፍቅር አሳማኝ ምስክርነት የሚሰጥ መሆኑን አስገንዝበዋል። ክቡራት ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡትን አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን አስቀድመን ለአስተንትኖ እንዲሆናቸው የመረጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ከዚህ ቀጥሎ እናስነብባችኋለን:-

“ፍቅር ይታገሣል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም፥ የራሱንም አይፈልግም፥ አይበሳጭም፥ በደልን አይቆጥርም” (1ኛ ቆሮ. 13 : 4-5፣ 7)

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! ባለፈው እሑድ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት ታሪክ ሰምተናል። ምንም እንኳን ከትውፊቶቹ መካከል የሚመደብ ባይሆንም ኢየሱስ ለታገሳቸው መከራዎቹ ምላሽ የሰጠው በትዕግስት ነበር። ‘ትዕግስት’ እጅግ  አስፈላጊ ነው። ትዕግስት ከስሜታዊነት ጋር አንድ መሆኑ በአጋጣሚ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ በትህትና እና በየዋህነት መታሰርን፣ መገረፍን እና በግፍ መወገዝን በመቀበል ትዕግስቱን የገለጠው በሕማማቱ መካከል ነው። ወደ ጲላጦስ ፊት ሲቀርብ አልተሟገተም፤ በወታደሮች ሲሰደብ፣ ሲተፋበት እና ሲሰድቡት፥ ይህን በሙሉ በትዕግስት ተሸከመ። የመስቀሉን ክብደት ተሸክሟል። በእንጨት ላይ የቸነከሩትን ይቅር ብሏል። በመስቀል ላይ ሳለ የቁጣ ምላሽ አልሰጣቸው። ይልቁንም ምሕረትን አደረገላቸው። ይህ ሁሉ የኢየሱስ ክርስቶስ ትዕግሥት ለደረሰበት ሥቃይ ጠንከር ያለ ተቃውሞ ማሰማት ሳይሆን የፍቅር ፍሬ መሆኑን ያስገነዝባል።

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ‘የቸርነት ሥራ መዝሙር’ ተብሎ በሚጠራው መልዕክቱ፥ (1 ቆሮ 13፡4-7) ፍቅርን እና ትዕግስትን በቅርበት አቆራኝቷቸዋል። በእርግጥም የመጀመሪያውን የቸርነት ሥራ ሲገልጽ፥ ‘ታጋሽ" ወይም ‘ሆደ ሰፊነት’ የሚለውን ቃል ይጠቀማል። ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተደጋግሞ የተጠቀሰውን አስገራሚ ጽንሰ ሃሳብን ይገልፃል። እግዚአብሔር ከእኛ እምነተ ቢስነት ጋር ፊት ለፊት የተጋፈጠበት እና ራሱን ለቍጣ ያዘገየ መሆኑን ያሳያል (ዘፀ. 34፡6 ፤ ዘኁልቅ 14፡18)።

የሰዎችን ክፋት እና ኃጢያት ከመመልከት ይልቅ በታላቅነቱ እና በማያልቅ ትዕግስቱ ሁሉን ነገር በአዲስነት እንደገና ለመጀመር ዘወትር ዝግጁ መሆኑን ገልጧል። ኃጢአትን ይቅር ማለት ለሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የእግዚአብሔር ፍቅር የመጀመሪያ ባህሪ ነው። ነገር ግን ይህ ብቻ አይደለም፤ ለክፋት መልካም ምላሽ መስጠትን የሚያውቅ፣ በቁጣ እና ተስፋን ከመቁረጥ ይልቅ ነገር ግን በጽናት እና ሁሉን በአዲስ እንደገና መሞከር የታላቅ ፍቅር የመጀመሪያ ባህሪ ነው። ስለዚህ የትዕግሥት መነሻ ፍቅር ነው። ቅዱስ አጎስጢኖስ፥ ‘ጻድቃን ያንን መከራ ሁሉ በጽናት የሚሻገሩት የእግዚአብሔር ፍቅር በእነርሱ ላይ ከሁሉም በላይ ኃይለኛ በመሆኑ ነው’ ይላል።

አንድ ሰው የኢየሱስን ፍቅር ከሚመሰክር ከታጋሽ ክርስቲያን የበለጠ ምስክር የለም ሊል ይችላል። ነገር ግን እናቶች እና አባቶች፣ ሠራተኞች፣ ሐኪሞች እና ሕሙማን ችግር የበዛበትን ዓለም የሚያሸንፉት በትዕግሥት ነው። ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያረጋግጡት፥ ‘ለቍጣ የዘገየ ከኃያላን ይሻላል’ (ምሳ 16፡32)። ሆኖም ሐቀኛ መሆን አለብን። ብዙ ጊዜ ትዕግስት ይጎድለናል። ትዕግስት ሊኖረን ይገባል፤ ያስፈልገናልም። ነገር ግን ትዕግስት ማጣት እና ክፉን በክፉ መመለስ ሳይታወቀን ይከሰታል። መረጋጋት፣ ስሜታችንን መቆጣጠር፣ ከመጥፎ ምላሽ መራቅ፣ በቤተሰብ መካከል ፣ በሥራ ቦታ፣ በክርስቲያን ማኅበረሰብ ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን እና ግጭቶችን ማብረድ ከባድ ነው።

ነገር ግን ትዕግስት ለእኛ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ጥሪ መሆኑንም ልናስታውስ ይገባል። ኢየሱስ ክርስቶስ ታጋሽ ከሆነ ክርስቲያንም ታጋሽ እንዲሆን ተጠርቷል። ይህም በችኮላ እና ሁሉንም ነገር በጥድፊያ ለማከናወን የሚፈልገውን የአስተሳሰብ ማዕበል መቃወም እንዳለብን ያሳስባል። በዚህ ውስጥ ሁኔታዎች እንዲረጋጉ ከመጠባበቅ ይልቅ ነገሮች ወዲያውኑ እንደሚለወጡ እናስባለን። መቸኮል እና ትዕግሥት ማጣት የመንፈሳዊ ሕይወት ጠላቶች መሆናቸውን አንዘንጋ። እግዚአብሔር ፍቅር ነው። የሚያፈቅሩ ሰዎች አይታክቱም፤ አይቆጡም፤ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ነው አይሉም፤ በትዕግስት መጠበቅን ያውቃሉ። ከቤት ወጥቶ የሄደውን ልጁን የሚጠብቅ የምሕረት አባት ታሪክ እናስታውስ። በትዕግስት ሲሰቃይ ነበር የቆየው። ትዕግስቱን ያጣው ተመልሶ ባየው ጊዜ ሊያቅፈው ሲሄድ ብቻ ነው (ሉቃ. 15፡21)። ወይም የስንዴውን እና የእንክርዳዱን ምሳሌ ብንመለከት፥ ምንም ነገር እንዳይባክን በማሰብ ክፉ የሆነውን በጊዜ ለመንቀል የማይቸኩል ገበሬን እናስታውስ (ማቴ. 13፡29-30)።

ነበር ግን አንድ ሰው በትዕግስት እንዴት ማደግ ይችላል? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን፥ ትዕግስት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ስለሆነ (ገላ. 5፡22) አንድ ሰው ከኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ እንደሚገኝ መጠየቅ አለበት። እርሱ የዋህ የሆነውን የትዕግስት ጥንካሬን ይሰጠናል። ምክንያቱም ቅዱስ አጎስጢኖስ በስብከቶቹ (46,13)፥ ‘ክርስቲያናዊ በጎነት መልካም ማድረግ ብቻ ሳይሆን ክፋትንም መታገስ ነው’ ይላል። በተለይ በእነዚህ ቀናት ውስጥ በተሰቀለው በየኢየሱስ ክርስቶስ ትዕግስት ላይ ብናስብበት መልካም ነው። ሌላው ጥሩ ልምምድ የሚሆነው የሚያስጨንቁን ሰዎች ወደ እርሱ መውሰድ ነው። ለእነርሱ በጣም የታወቀውን ነገር ግን ችላ የተባሉትን የምሕረት ሥራ እንዲተገበሩ ጸጋውን መጠየቅ፣ ችግር ያለባቸውን ሰዎች በመታገስ፣ በእግዚአብሔር እገዛ አቀራረባቸው ከስህተታቸው እንዴት እንደሚለይ በማወቅ፣ በርህራሄ ዓይን መመልከትን በመጠየቅ ይጀምራል።

በመጨረሻም፥ ትዕግስትን ለማዳበር እና ለሕይወት እስትንፋስ የሚሆነውን በጎነት ለማግኘት አመለካከትን ማስፋት ጥሩ ነው። ለምሳሌ ክርስቶስን መምሰል፤ የሌሎችን መከራ ለማሰብ የራሳችንን ትናንሽ ሸክሞችን በማስታወስ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ስለ እርሱ የተሠቃየ፥ ምንም ያህል ትንሽ ቢሆንም ያለ ዋጋ ሊያልፈው እንደማይችል በማስታወስ፥ ደግሞም ኢዮብ እንደሚያስተምረን፥ በመከራ ውስጥ እንዳለን ሲሰማን፣ የምንጠብቀው ነገር ሊያሳዝነን እንደማይፈቅድ ያለማወላወል በመተማመን፣ ለእግዚአብሔር ራሳችንን ግልጽ ማድረግ መልካም ነው።”

 

27 March 2024, 16:51