ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ከእግዚአብሔር ጋር የማይለዋወጥ ጽኑ ግንኝነት መመሥረት ይገባል!”
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! በዮሐ. 2: 13-25 ድረስ የተነበበው የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል ምንባብ ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም በቤተመቅደስ ውስጥ ሆነው ይገበያዩ የነበሩ ነጋዴዎችን ከቤተመቅደስ እንዲወጡ ያደረገበትን ትዕይንት ያሳየናል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ሻጮችን ከቤተ መቅደሱ ውስጥ በማስወጣት፣ ገንዘባቸውንም በመበተን እና ገበታዎቻቸውንም በመገለባበጥ እንዲህ ሲል ገሰጻቸው፥ ‘የአባቴን ቤት የንግድ ቤተ አታድርጉት’ አላቸው (ዮሐ. 2:16) ። በቤት እና በገበያ መካከል ባለው ልዩነት ላይ እናተኩር። በእርግጥ እነዚህ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብባቸው ሁለት የተለያዩ መንገዶች ናቸው።
ቤተ መቅደስን እንደ ገበያ ሥፍራነት ስንመለከተው አንድ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ትክክል ለመሆን በቤተ መቅደስ ውስጥ የበግ ጠቦትን ገዝቶ በመሠዊያው እሳት ከጠበሰው በኋላ መብላት ነበረበት። ከዚያም በኋላ ሁሉም ሰው ወደ ቤቱ ይሄዳል። በዚህ ሁኔታ ቤተመቅደስ እንደ ቤት ይቆጠራል። በሌላ በኩል በተቃራኒው ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት፣ ወደ እሱ፣ ወደ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ለመቅረብ፣ ደስታን እና ሐዘንን ለመካፈል ወደ ቤተመቅደስ እንሄዳለን። ከዚህም በላይ ሁሉም ሰው ወደ ገበያ ሲሄድ ስለሚገዛው ነገር ዋጋ ይደራደራል። በቤት ውስጥ ግን ለሚደረግለት መስተንግዶ ምን ያህል ልክፈል ብሎ ማንም አያስብም። ነገር ግን አንድ ሰው ወደ ገበያ ሲሄድ የራሱን ፍላጎት ወይም ትርፍ ይፈልጋል። በቤት ውስጥ ግን ሁሉንም ነገር በነጻ ያገኛል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ሻጮችን ከቤተ መቅደሱ እንዲወጥ ያደረገበት፣ ገበታዎቻቸውን ገለባብጦ ገንዘባቸውን የበተነባቸው፥ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የሚቀርቡበት ቤተ መቅደስ ወደ ገበያ ማዕከልነት እንዲለወጥ ባለመፈለጉ ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት እንዲበላሽ ወይም እንዲቋረጥ አይፈልግልም። የጠበቀ እና እምነት የተጣለበት እንጂ የራቀ እና ከንግድ ጋር የተያያዘ እንዲሆን ኢየሱስ አይፈልግም። የቤተሰብ ገበታን የዕቃ መሸጫ ቦታ እንዲሁን፣ የዋጋ ድርድሮች የወዳጅነት ስሜትን፣ ሳንቲሞችም የሰዎችን መቀራረብ እንዲተኩ ኢየሱስ አፈልግም። ኢየሱስ ይህን የማይፈልገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር እና በሰዎች መካከል ኅብረትን፣ ምሕረትን እና መቀራረብን ለማምጣት የመጣ በመሆኑ በወንድሞች መካከል ልዩነትን እንዲፈጠር አይፈልግም።
የዛሬው ቅዱስ ወንጌል የዐብይ ፆም ወቅትን ጨምሮ በራሳችን እና በአካባቢያችን ውስጥ ከገበያ ሥፍራነት ይልቅ የላቀ የቤተሰብነት ስሜት መገንባት እንደሚገባን ከሁሉ አስቀድሞ እንደ ስግብግቦች እና እምነት እንደሌላቸው ነጋዴዎች ሳንሆን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ አብዝተን እንድንጸልይ፣ ወደ ደጁ በልበ ሙሉነት ቀርበን ሳንሰለች በሩን እንድናንኳኳ ይጋብዘናል። ስለዚህ በቅድሚያ በጸሎት ከዚያም ወንድማማችነት ከምን ጊዜውም የበለጠ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ወንድማማችነትን ማስፋፋት ይኖርብናል።
ስለዚህ በቅድሚያ ጸሎታችን ምን ይመስላል? ብለን እራሳችንን እንጠይቅ። ጸሎታችን እንደ አንድ ዕቃ ዋጋ የተተመነነው ወይስ ጊዜን ሳንሰጥ በብቸንነት ወቅት የእግዚአብሔርን ዕገዛ የምንለምንበት ነው? ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት ምን ይመስላል? ከሰዎች ምንም ሳልጠብቅ መልካም ነገርን ላደርግላቸው እችላለሁን? ዝምታን እና ልዩነትን ለማስወገድ በቅድሚያ እርምጃን መውሰድ እችላለሁ? እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን እራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።
በመካከላችን እና በዙሪያችን ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የምንሆንበትን መሠረት ለመገንባት የሚያስችለንን ኃይል በመስጠት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን።”