የእስራኤል እና የፍልስጤም ጦርነት በንብረት እና በሰው ነፍስ ያስከተለው ጥፋት የእስራኤል እና የፍልስጤም ጦርነት በንብረት እና በሰው ነፍስ ያስከተለው ጥፋት  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው ጦርነት ይብቃ ልንል ይገባል!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ የካቲት 24/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባደረጉት ንግግር በመካከለኛው ምሥራቅ በሃማስ ታጣቂዎች እና በእስራኤል ጦር ሠራዊት መካከል የሚካሄደው ጦርነት እንዲያበቃ ተናጽነዋል። ቅዱስነታቸው በንግግራቸው በሁለቱም ወገኖች ተኩስ ቆሞ የእስራኤል ታጋቾች እንዲፈቱ እና ለፍልስጤም ሕዝብ አስቸኳይ ዕርዳታ እንዲደረግለት ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካቲት 24/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጸሎት ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባደረጉት ንግግር፥ ቀጣይነት ባለው ጦርነት ምክንያት በፍልስጤም እና በእስራኤል ሕዝቦች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ በየቀኑ በልባቸው እንደሚሸከሙት ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “በሺዎች ለሚቆጠሩት ሞትን፣ መቁሰልን፣ መፈናቀልን እና ያስከተለው ጦርነት ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ሰዎች ላይ ስቃይን እና ታላቅ ውድመትን ማስከተሉን በመግለጽ፥ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በሙሉ ለሰላም ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ጠይቀዋል።

በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ለተሰበሰቡት ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን ባሰሙት ንግግርም፥ “በእርግጥ በዚህ መንገድ የተሻለ ዓለምን እየገነባን ነው ብለን እናስባለን ወይ?” ሲሉ ጠይቀው፥ “ሁላችንም ጦርነት ይቁም! በማለት ድምጻችንን እናሰማ” ብለዋል።

ተኩሱ ባስቸኳይ ይቁም!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጋዛ እና በአከባቢው ፈጣን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ድርድር እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበው፥ ታጋቾችም ነፃ ወጥተው በጉጉት ወደሚጠብቃቸው ዘመዶቻቸው እንዲመለሱ፣ የሲቪሉ ማኅበረሰብ ደህንነት ተጠብቆ አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደርሰው አሳስበዋል።

“በድርድር የተጀመረው ጥረት ቀጥሎ በጋዛ እና በአከባቢው ፈጣን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ አበረታታለሁ” ብለዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር በማያያዝ በየቀኑ ብዙ ሰዎች የሚሰቃዩባትን እና የሚሞቱባትን ዩክሬንን ምዕመናን በጸሎታቸው እንዲያስታውሷት አደራ ብለው፥ ቦታው ታላቅ ሐዘን የነገሠበት እንደሆነ ገልጸዋል።

በመስከረም 26/2016 ዓ. ም. የተጀመረ ጦርነት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጎርጎሮሳውያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ካቶሊክ ምዕመን ዘንድ በተያዘው በሦስተኛ እሑድ የዐብይ ጾም ወቅት ያቀረቡት ጥሪ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ጦርነቱ ከጀመረበት ማለትም ከመስከረም 26/2016 ዓ. ም. አንስቶ ካቀረቧቸው በርካታ የሰላም ጥሪያቸው መካከል አንዱ እንደ ሆነ ታውቋል። እሳካሁን በሃማስ ታግተው የቆዩ 130 እስራኤላውያን እንደሚገኙ እና ከ30 በላይ የሚሆኑት ሳይገደሉ እንዳልቀረ ይገመታል።

እስራኤላውያን በጋዛ ሰርጥ ባደረሱት ጥቃት የተገደሉት ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ30,000 በላይ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ የደረሱበት አይታወቅም። በተመሳሳይም በዚህ ጦርነት ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ለአሰቃቂ ሰብዓዊ ዕርዳታ መጋለጣቸው ታውቋል። ከእነዚህ ውስጥ 2/3ኛው ሴቶች እና ህጻናት እንደሆኑ ተነግሯል።

በሰሜን ጋዛ የታየው የረሃብ ስጋት

በቅርቡ ከጋዛ የተመለሱት የኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤት ኃላፊ በግዛቲቱ ሰሜናዊ ክፍል ረሃብ እንዳለ ማመናቸውን ተናግረዋል። የምክር ቤቱ ኃላፊ አቶ ያን ኤገርላኡንድ ለብሪታኒያው ብዙሃን መገናኛ ኮርፖሬሽን “ቢቢሲ” እንደተናገሩት በአካባቢው የተመለከቱት ነገር ከጠበቁ እጅግ የከፋ እንደሆነ ገልጸው፥ ይህ የሆነበት ምክንያት እስራኤል በአቅራቢያዋ ያሉ የድንበር ማቋረጫዎችን እየከፈተች ባለመሆኗ ዕርዳታ ወደ ጋዛ መድረስ ባለመቻሉ እንደሆነ አስረድተው፥ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ጀርመን እና እንግሊዝ ለእስራኤል የጦር መሣሪያ በመሸጥ ላይ መሆናቸውንም አውግዘዋል።

በሳምንቱ መጨረሻ የዮርዳኖስ እና የአሜሪካ የዕርዳታ ድርጅቶች በጋራ ለጋዛ ሕዝብ የዕርዳታ ምግቦችን ከአውሮፕላን ላይ ሲወረውሩ ታይተዋል። የአሜሪካ አየር ሃይል እንዳስታወቀው ወደ 38,000 የሚጠጉ የታሸጉ ምግቦችን የያዙ ሦስት አውሮፕላኖች ወደ ጋዛ መላካቸውን ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ሸምጋዮች በግብጽ መዲና ካይሮ ላይ መሰብሰባቸው ተነግሯል። በመስከረም 26/2016 ዓ. ም. ሐማስ በእስራኤል ላይ ከባድ ድንገተኛ ጥቃት ካደረሰ በኋላ እስራኤል በጋዛ ላይ በከፈተችው መጠነ ሰፊ ጦርነት እስከ ዛሬ ድረስ በጋዛ 30,320 ፍልስጤማውያን መገደላቸው እና 71,533 መቁሰላቸው ተነግሯል። 

04 March 2024, 16:58