ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል ባቀረቡበት ወቅት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል ባቀረቡበት ወቅት  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በዓለም ላይ ጦርነት እንዲቆም የቅዱስ ዮሴፍን አማላጅነት ተማጸኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ማክሰኞ መጋቢት 10/2016 ዓ. ም. የተከበረውን የቅዱስ ዮሴፍ ዓመታዊ በዓል በማስታወስ፥ በዩክሬን እና በቅድስት አገር የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም ሁሉም ወገኖች የተቻለውን ሁሉ እንዲያደርጉ አሳስበው፥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እጮኛ የቅዱስ ዮሴፍ አማላጅነት በመለመን የሰላም ጥሪ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ረቡዕ መጋቢት 11/2016 ዓ. ም. ያቀረቡትን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ለመከታተል በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ቃለ ምዕዳን ባሰሙበት ወቅት፥ “በጦርነት የተጎዱትን የዩክሬን፣ የፍልስጤም እና የእስራኤል ሕዝቦች የሰላም አማላጅነት አደራን ለቅዱስ ዮሴፍ እንሰጣለን” ብለዋል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዓለም ላይ በጦርነት ምክንያት እየደረሰ ያለው ስቃይ እንዲያበቃ ያቀረቡት የቅርብ ጊዜ ጥሪ፥ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በመጋቢት 10/2016 ዓ. ም. የቅዱስ ዮሴፍን ዓመታዊ በዓል ባከበረች ቀን ማግስት ነው።

ቅዱስ አባታችን በተለይ በርዕሠ ሊቃነ ጵጵስና ዓመታት በልባቸው ለቅዱስ ዮሴፍ ልዩ ቦታ ያላቸው ሲሆን፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከጥር 1/2020 እስከ ታኅሣሥ 8/2021 ያለው ጊዜ የቅዱስ ዮሴፍ ልዩ ዓመት እንዲሆን ማወጃቸውም ይታወሳል።

ጦርነቱን ለማስቆም መደራደር

“ጦርነት ዘወትር ሽንፈት መሆኑን መቼም መዘንጋት የለብንም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ማንም ሰው ለጦርነት መነሳት እንደሌለበት፣ ጦርነትን ለማስቆም ድርድር ሊደረግ እንደሚገባ እና ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እንደሚያስፈልግ አጥብቀው ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ ሁሉም ምዕመናን ለሰላም በጸሎት እንዲተጉ ጠይቀው ቡራኤያቸውን ከሰጡ በኋላ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

20 March 2024, 13:08