ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ምስጢረ ንስሐ የእግዚአብሔርን ጸጋ እና ምሕረት የሚያስገኝ ልዩ ጊዜ ነው!"
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“የኢዮቤልዩን በዓል ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ዓመት የእግዚአብሔር ምሕረት በብዙዎች ልብ እና ሥፍራ ሲያብብ እያየን ስለሆነ እግዚአብሔር ይበልጥ የተወደደ፣ የታወቀ እና የተመሰገነ ይሁን” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን የገለጹት፥ ሐዋርያዊ የምስጢረ ንስሐ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ያዘጋጀውን የአንድ ሳምንት ስልጠና የተከታተሉ የዘርዓ-ክህነት ተማሪዎችን ዓርብ የካቲት 29/2016 ዓ. ም. በቫቲካን በተቀበሏቸው ጊዜ ነው።
በሮም በሚገኙ ልዩ ልዩ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙት ካኅናት እና የዘርዓ-ክህነት ተማሪዎች ሲሰጥ የቆየው የዚህ ዓመታዊ ስልጠና ዋና ዓላማ ሰልጣኞቹ የምስጢረ ንስሐ አገልግሎት የሚሰጡበትን መንገድ ለማሳየት ያለመ እንደ ሆነ ታውቋል።
የእግዚአብሔርን ፍቅር ማጣጣም
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለስልጠናው ተሳታፊዎች ባሰሙት ንግግር፥ ተግባራቸው ለምስጢረ ንስሐ የሚቀርቡ ምዕመናን የእግዚአብሔር ፍቅር ጣፋጭነት እንዲያቁ ማገዝ እንደሆነ ተናግረዋል። “እያንዳንዱ የኑዛዜ ጊዜ ልዩ እና የማይደገም የጸጋ ጊዜ መሆኑን በመገንዘብ የእግዚአብሔርን ምሕረት በልግስና፣ በአባታዊነት እንዲሁም በእናትነት ርኅራሄ እንዲሰጡ” በማለት ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።
በሦስት የመጸጸት መንገዶች ላይ ትኩረት ያደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እነርሱም፥ ምዕመናን ንስሐ ገብተው የኃጢአትን ይቅርታ ከማግኘታቸው በፊት የሚደግሟቸው ጸሎቶች እንደሆኑ ገልጸዋል።
በኃጢአተኝነታችን ራስን መኮነን ሳይሆን በኃጢአታችን ንስሐ መግባት
ንስሐ ስለመግባት በቅድሚያ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ንስሐ መግባት ከሥነ-ልቦናዊ የጥፋተኝነት ስሜት በእጅጉ እንደሚለይ ገልጸው፥ ንስሐ መግባት በእግዚአብሔር ወሰን በሌለው ፍቅር እና ምሕረት ፊት ስቃያችንን ከመገንዘብ የሚመነጨ ነው” ብለው፥ ክርስቲያን ንስሐ የሚገባው ራሱን ለመጉዳት ሳይሆን በእግዚአብሔር ይቅር ባይነት እና አባትነት ላይ ለመተማመን እንደሆነ አስረድተዋል።
“በኃጢአታችን ምክንያት የሚሰማን ስሜት የእግዚአብሔር ወሰን የለሽ ፍቅርን ከመገንዘብ ጋር ተመጣጣኝ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “የእግዚአብሔር ርኅራሄ በተሰማን ቁጥር ከእርሱ ጋር በሙላት ለመገናኘት እንፈልጋለን፣ የክፋት አስከፊነት በሕይወታችን ውስጥ ይበልጥ ግልፅ ይሆናል” ብለዋል።
በእግዚአብሔር ቸርነት መታመን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም፥ በእግዚአብሔር ቸርነት መታመን የጸጸት ሥራ እንደሆነ ገልጸው፥ እግዚአብሔር አምላክ በሁሉም መልካም እና ፍቅራችንም የሚገባው እንደሆነ ይገልጻል” ብለው፥ ከሁሉ አብልጦ እግዚአብሔርን መውደድ ማለት እርሱን የሕይወታችን ማዕከል አድርገን ሁሉንም ነገር ለእርሱ መስጠት ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።
“ለእግዚአብሔር ቅድሚያን መስጠት ለሰዎች እና ለፍጥረታቱ የምንጣቸውን ሌሎች የፍቅር ዓይነቶችን ሕያው ያደርጋል፤ እግዚአብሔርን የሚወድ ወንድሙን ስለሚወድ መልካምነቱን ዘወትር ፍትሃዊ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመግለጽ ይፈልጋል” ብለዋል።
በእግዚአብሔር ዕርዳታ ዳግመኛ ወደ ኃጢአት አለመመለስ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው መደምደሚያ ስለ ኃጢአት ስርየት ሲናገሩ፥ ይህም ክርስቲያን በፈጸመው ኃጢአት ውስጥ እንደገና አለመውደቅን የሚገልጽ እንደሆነ ተናግረው፥ ይህ ቁርጠኝነት ክርስቲያንን ከውድቀት ወደ ፀፀት፣ ከስሕተት ወደ ፍጹም ሐዘን እንዲሸጋገር ያስችለዋል” ብለዋል።
“ከእንግዲህ ወዲህ በጸጋህ ብርታት ኃጢአትን ላለመሥራት እና ከኃጢአትም ለመራቅ በጽኑ ቆርጬአለሁ” የሚሉት ቃላት ውሳኔ ማድረግን እንጂ ቃል መግባትን የሚገልጹ አይደሉም” በማለት አስረድተዋል። “ማናችንም ብንሆን ‘ዳግመኛ ኃጢአት አንሠራም’ ብለን ለእግዚአብሔር ቃል መግባት አንችልም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አክለውም፥ ይቅርታን ለማግኘት የሚያስፈልገን፥ ወደ ፊት እንከን የለሽ ስለመሆናችን ዋስትናን መስጠት ሳይሆን፥ ኑዛዜአችን ለትክክለኛው ዓላማ የተደረገ መሆኑ ነው” ብለዋል። ዳግመኛ ኃጢአት ላለመፈጸም ያለን ቁርጠኝነት የእግዚአብሔርን ዕርዳታ ለማግኘት ከምናቀርበው ጸሎት ጋር አብሮ የሚሄድ እና ያለ እግዚአብሔር ዕርዳታ መለወጥ የማይቻል መሆኑንም አስረድተዋል።
እግዚአብሔር ርኅራሄውን በማሳየት ብርሃን ይሆናል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የእግዚአብሔር ርኅራሄ ከፀፀታችን ጋር ጠቃሚ የሆኑ መለኮታዊ ባሕርይን እንደሚገልጽ በማስረዳት፥ "ጌታ ሆይ ራራልኝ፣ ጌታ ሆይ ይቅር በለኝ" የሚሉት የጸሎታችን የመጨረሻ ቃላት እንደሆኑ አስታውሰዋል።
"እግዚአብሔር መሐሪ እና መልኩም የምሕረት እንደሆነ ዘወትር ማስታወሱ መልካም እንደሆነ፣ በእያንዳንዱ የምሕረት እና የፍቅር ሥራው ፊቱ እንደሚያበራ፥ ሐዋርያዊ የምስጢረ ንስሐ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ያዘጋጀውን የአንድ ሳምንት ስልጠናን ለተከታተሉት ካኅናት እና የዘርዓ-ክህነት ተማሪዎች በማስረዳት ንግግራቸውን ደምድመዋል።