ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ለቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አባላት ንግግር ሲያደርጉ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ለቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አባላት ንግግር ሲያደርጉ  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ "የኢዮቤልዩ በዓል የእግዚአብሔር ሕዝብ በተስፋ እንዲኖር ያግዛል" አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጎርጎሮሳውያኑ 2025 ዓ. ም. የሚከበረውን የኢዮቤልዩ ዓመት በማስመልክት ለቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አባላት ንግግር አድርገዋል። መጪው ዓመት የተስፋ ዓመት እንደ ሆነ በማስገንዘብ፥ አዲስ የስብከተ ወንጌል አገለግሎት አቀራረብ እና ዓለማዊነትን ለማሸነፍ የሚያግዝ መንፈሳዊ ምሕረት የሚጎለብትበት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በጸጋ ሙላት እና በምሕረት መንገድ ሲቀርብ የበለጠ ተሰሚነት ሊኖረው እንደሚችል እና ልብም ለለውጥ ፈቃደኛ ይሆናል” ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህንን ያሳሰቡት በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አባላትን ዓርብ መጋቢት 6/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው።

የወንጌል አገልግሎት በዓለማዊት ውስጥ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአባላቱ ያሰሙትን ንግግራቸውን የጀመሩት፥ ዓለማዊነት እና ግለኝነት በበዛበት ዓለማችን ውስጥ አዲስ የወንጌል አገልግሎት የማስተዋወቅ አስፈላጊነትን በማስመልከት ያዘጋጁት ጽሑፍ በንባብ ከቀረበ በኋላ እንደ ነበር ታውቋል።

ባለፉት አሥርተ ዓመታት ዓለማዊነት የክርስቲያንነት ስሜት ከመቀነስ ጀምሮ ለእምነት እና ለይዘቱ ግድየለሽነትን እንዲኖር በማድረግ ትልቅ ችግር እንዳስከተለ አስረድተው፥ ከአዲሱ የዲጂታል ባሕል መስፋፋት ጋር በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ካለው የእውነት እና የነጻነት ፍላጎት እንዲሁም ከሰው ልጅ ራዕይ ጋር በግል እና በማኅበራዊ ግንኙነቶች የነጻነት ፍላጎት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳላቸው ገልጸዋል።

“ስለዚህም ዓብይ ጉዳይ የሚሆነው በእምነት ስርጭት ላይ የተከሰተውን ስብራት እንዴት ማሸነፍ እንደምንችል መረዳት እና ከቤተሰብ እና ከወንጌል አገልግሎት ማሰልጠኛ ማዕከላት ጋር ያለውን ውጤታማ ግንኙነት መልሶ ማግኘት ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል።

“ለወንጌል ስርጭት እምብርት የሆነው የትንሳኤው እምነት፣ በቤተሰብ እና በክርስቲያን ማኅበረሰብ ውስጥ ጉልህ ልምድ ሊኖር እንደሚገባ እና ሕይወትን ከሚለውጥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ግንኙነት ሊኖር እንደሚገባ ጠይቀዋል። ያለዚህ ግንኙነት ሕልውናችን እምነትን የሕይወት ምስክርነት ከማድረግ ይልቅ ንድፈ ሐሳብ በማድረግ ፈተና ውስጥ ይወድቃል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2020 ዓ. ም. በጳጳሳዊ ምክር ቤት የተዘጋጀውን አዲሱን የትምህርተ ክርስቶስ ማስተማሪያን እንደ ትክክለኛ እና ውጤታማ መሣሪያ አድርገው በመቀበል፥ አዲስ የወንጌል ስርጭት ለማስተዋወቅ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ማስተማሪያን ማደስ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ መላው የክርስቲያን ማኅበረሰብ እንዲሳተፍበት ማድረግ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ወሳኝ ሚና

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ ትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ሚና ሲናገሩ፥ ብጹዓን ጳጳሳት ለዚህ አገልግሎት የተጠሩትን ማበረታታት እና መከታተል እንደሚገባ፥ በተለይም በወጣት ትውልድ መካከል ያለው ልዩነት እንዲጠብ እና እምነትን ለሌሎች የማስተላለፍ ተልዕኮ እና ሃላፊነት ለአረጋውያን ብቻ በአደራ የተሰጠ መሆን የለበትም ብለዋል።

"የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ለቀረቡት አዳዲስ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ፣ በጥንቃቄ የሚጠና እና ዋጋ የሚሰጠው እንዲሆን ለማድረግ መንገዶችን እንዲፈልጉ በማለት ለአገልግሎቱ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አባላት ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

የምሕረት መንፈሳዊነትን ማሳደግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መቀጠም፥ የምሕረት መንፈሳዊነት ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት መሠረታዊ እንደሆነ ገልጸው፥ “የእግዚአብሔር ምሕረት መቼም ቢሆን የማይጎድል በመሆኑ፥ ለእርሱ ለመመስከር፣ ለመናገር እና በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ለማሰራጨት ተጠርተናል” ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2015 ዓ. ም. በወጣው “የምሕረት ዓይን” በሚል መመሪያ መሠረት የተከናወነውን ጥልቅ ሐዋርያዊ ተግባር በመጥቀስ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2016 ዓ. ም. ያወጁትን ልዩ የምሕረት ኢዮቤልዩ ዓመትን አስታውሰዋል። "ካኅናት ለጋስ በሆነው አገልግሎታቸው የመሃሪው እግዚአብሔር ታማኝ አገልጋዮች የመሆንን ጸጋ እና ደስታን በድጋሚ የሚገነዘቡ እና የምሕረት ጸጋን ዘወትር ያለ ገደብ የሚመሰክሩ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

ለተስፋ ኢዮቤልዩ በዓል በመዘጋጀት ጸሎት ያስፈልጋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመጨረሻም፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. በሚከበረው የተስፋ ኢዮቤልዩ ዓመት ላይ በማሰላሰል በመጪዎቹ ሳምንታት ውስጥ ሐዋርያዊ መልዕክቶች ይፋ እንደሚደረጉም ተናግረዋል። “መልዕክቶቹ በርካታ ሰዎች ከሁሉም በላይ ተስፋን በተጨባጭ መንገድ ለመለማመድ እንደሚያግዟቸው ተስፋ አድርገው፥ የእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ተስፋን እጅግ ይፈልገዋል!” ሲሉ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሚቀጥለው ዓመት ለኢዮቤልዩ በዓል ወደ ሮም የሚመጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናንን ለመቀበል ላደረገው ጥረት የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አባላትን እያመሰገኑ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2024 ዓ. ም. የጸሎት ዓመት ተብሎ የተሰየመውም ለበዓሉ ዝግጅት ጸሎት አስፈላጊ በመሆኑ ነው ብለዋል። 

"ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር የመሆን ልምድን የምንረዳበት፣ እርሱ እንደተቀበልን እና በእርሱ እንደተወደድን የመሰማት ልምድ አድርገን ልንወስድ ይገባናል" ሲል ተናግረው፥ “ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና በቅዱሳን ቤት ውስጥ አብዝተን ይበልጥ መጸለይ እንጀምር” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

 

 

 

16 March 2024, 16:40