ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የጣሊያን የሕዝብ ማሠራጫ ኮርፖሬሽን ሠራተኞችን በቫቲካን ሲቀበሉ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የጣሊያን የሕዝብ ማሠራጫ ኮርፖሬሽን ሠራተኞችን በቫቲካን ሲቀበሉ   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የሕዝብ ማሰራጫዎች ለጋራ ጥቅም የቆሙ ሊሆን እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጣሊያን የሕዝብ ማሠራጫ ኮርፖሬሽን “RAI” ሥራ አስኪያጆችን እና ሠራተኞችን በቫቲካን ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የሕዝብ ማሰራጫ ኮርፖሬሽኑ ለጋራ ጥቅም የሚውሉ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ዝግጅቶች እና የማያዳሉ መረጃዎችን ለዜጎች የማቅረብ አገልግሎት ተልዕኮ እንዳለው አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የሕዝብ ማሠራጫዎች ቀዳሚ ተልዕኮ ለዜጎች እውነተኛ እና ትክክለኛ መረጃን መስጠት፣ አስተማሪ እና ጥራት ያለውን የመዝናኛ ዝግጅቶችን ማቅረብ መሆኑን ቅዳሜ መጋቢት 14/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ለተቀበሏቸው የጣሊያን የሕዝብ ማሠራጫ ኮርፖሬሽን ሠራተኞች አስታውቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የሬዲዮ ስርጭት የጀመረበትን 100ኛ ዓመት እና የቴሌቪዥን ስርጭት የጀመረበትን 70ኛ ዓመት የሚያከብሩ የጣሊያን የሕዝብ ማሰራጫ ኮርፖሬሽን የሥራ አስኪያጆችን እና ሠራተኞችን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፥ የጣሊያን የሕዝብ ማሠራጫዎች ታሪክ ባለፉት አሥርት ዓመታት ውስጥ በጣሊያን ማኅበረሰብ ውስጥ ከተከሰቱት ባሕላዊ ለውጦች ጋር በቅርበት የተሳሰረ እንደ ነበር ገልጸው፥  “በእርግጥ ብዙሃን መገናኛዎች በማንነታችን ላይ በጎም ሆነ መጥፎ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል” ብለው፥ የጣሊያን የሕዝብ ማሠራጫ ኮርፖሬሽን “RAI” ተልዕኮ ሁለት ቁልፍ ቃላት ላይ እነርሱም “አገልግሎት” እና “ሕዝብ” በሚሉት ላይ በማትኮር “ማኅበራው ግንኝነት ለህብረተሰቡ የተሰጠ ስጦታ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

እውነተኛ እና ሁሉን የሚያቅፍ መረጃ ማቅረብ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እውነተኛ መረጃ የሚለውን የመጀመሪያ ነጥብ በማስመልከት እንደተናገሩት፥ በመረጃው አገልግሎት ዘርፍ እውነተኛ መረጃን ማቅረብ ማለት አሳሳች የሆኑ የርዕዮተ ዓለም አመለካከቶችን እና የሐሰት ዜና ስርጭትን በመከላከል እውነትን መፈለግ እና ማስተዋወቅ ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው እውነት ምን ጊዜም የሚገኘው የራስን ሃሳብ ብቻ ከማንጸባረቅ ይልቅ የተለያዩ ድምጾችን ማዳመጥን ከመማር እንደሚገኝ በማስታወስ፥ ከማንኛውም አሳሳች መረጃዎች መራቅ እና የዜጎችን መብት ለማስከበር መረጃን ማጣራት እንደሚገባ፥ በሚገኘው መረጃ ላይ ለማሰላሰል እና ለመረዳት ጊዜን መስጠት እንደሚገባ እንዲሁም መረጃ የ 'ሥነ-ምህዳር' ክፍል በመሆኑ የግንዛቤ መዛባትን መዋጋት ይገባል” በማለት አሳስበዋል።

የውይይት ባሕልን ማዳበር

“እውነትን መፈለግ ማለት ብዝሃነትን ማረጋገጥ ማለት ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቀደም ሲል እንደተናገሩት፥  ‘እውነት ከተገኘ በኋላም ቢሆን በተወሰነ መልኩ ዘወትር እንደሚሆነው ፈጽሞ ሊጫን አይገባም” ብለዋል።በመሆኑም የጣሊያን የሕዝብ ማሰራጫዎች ኮርፖሬሽን የሥራ አስኪያጆች እና ሠራተኞች በሥራቸው መካከል አንድነትን በመፍጠር የውይይት ባሕል እንዲያዳብሩ አሳስበዋል። የውይይት ባሕልን ለማዳበር ሌሎችን ማዳመጥ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ “የሌሎችን አቋም ሳይረዱ የራስን አቋም ብቻ ማንጸባረቅ እውነተኛ መደማመጥ አይደለም” ሲሉ አስረድተዋል።

በጣሊያን የሕዝብ ማሠራጫዎች “RAI” በኩል የሚቀርቡ ሌሎች ዝግጅቶች፥ ሲኒማ፣ ልብ ወለድ ታሪኮች እና ተከታታይ የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች፣ የባሕል እና የመዝናኛ ፕሮግራሞች፣ ስፖርታዊ ዝግጅቶች እና የልጆች ፕሮግራሞች፣ ውበትን በመፈለግ፣ የአብሮነት እሴቶችን ማስተዋወቅ፣ ነፃነትን ለማስጠበቅ መትጋት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው፥ እያንዳንዱ ጥበባዊ አገላለጽ የሁሉንም ተመልካች ሕይወት እንደሚያከብር ማረጋገጥ ያስፈልጋል በማለት አሳስበዋል።

የሰው ሠራሽ ቴክኖሎጂዎች አንድምታ

ቅዱስነታቸው አዲሶቹ የመረጃ ቴክኖሎጂዎችን በማስመልከት እንደተናገሩትም፥ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን አላግባብ መጠቀም ሊያስከትል የሚችለው ጎጂ፣ አድሎአዊ እና ማኅበራዊ ኢ-ፍትሃዊነት ተፅእኖዎችን ለመከላከል እና ለመቀነስ የሚያግዙ የመከላከያ እርምጃዎች እና የቁጥጥር መሣሪያዎች ሊኖሩ እንደሚገባ በድጋሚ ተናግረው፥ ብዝሃነትን ለመቀነስ፣ በሕዝብ አስተያየቶች ላይ ቅራኔን ወይም የቡድን አስተሳሰብን ማራመድን መዋጋት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም፥ የጣሊያን የሕዝብ ማሠራጫዎች ባላቸው የሕዝባዊነት ባህሪ ላይ በማሰላሰል፥ ይህ ባህሪው አገልግሎቱ ከጋራ ጥቅም ጋር የተገናኘ መሆኑን የሚገልጽ እንደሆነ አስምረውበት፥ ይህም በቅድሚያ የተናቁትን፣ የደኸዩትን እና የተዘነጉትን በማስታወስ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ የመሆን ቁርጠኝነትን እንደሚያካትት፥ እንዲሁም እውቀትን ለማጎልበት፣ የሰዎችን አድማስ ለመክፈት እና ወጣቶች ትልቅ ህልም እንዲኖራቸው ለማስተማር መሣሪያ የመሆን ጥሪ ያለበት መሆኑን ያመለክታል ብለዋል።

የታዳሚው ድርሻ ከዝግጅት ጥራት አስፈላጊነት ያነሰ ነው

በታዳሚዎች ቁጥር ብዛት ላይ ከማተኮር ይልቅ በሚቀርቡ ዝግጅቶች ጥራት ላይ ማትኮር እንደሚገባ ጥሪ ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ማኅበራዊ ግንኙነት በዘመናችን ውስጥ ማኅበረሰባዊ ጠቀሜታ ያላቸውን እንደ የዜግነት እና የተሳትፎ እሴቶችን በማደስ ረገድ መሠረታዊ ሚናን ሊጫወት እንደሚችል ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ የጣሊያን የሕዝብ ማሰራጫ ኮርፖሬሽን በቤተሰብ እና በኅብረተሰብ መካከል አንድነትን እና እርቅን፣ ማሳወቅን እና ማዳመጥን፥ ከአክብሮት እና ትህትና ጋር የመደማመጥ እና የውይይት ባሕልን እንዲያበረታታ አደራ ብለዋል።  

 

 

 

 

25 March 2024, 17:24