ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ክርስቲያኖች ከሞት በተነሳው ኢየሱስ ላይ እምነት ሊኖራቸው ይገባል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የጎርጎርሳውያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ካቶሊክ ምዕመናን ዘንድ ተከብሮ ባለፈው የብርሃነ ትንሳኤ በዓል ሁለተኛ እሑድ መጋቢት 29/2016 ዓ. ም. የተነበበውን የቅዱስ ወንጌል ክፍል መሠረት በማድረግ ስብከታቸውን አቅርበዋል። ከሮም እና አካባቢዋ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ሀገረ ስብከቶች እና አገራት ለመጡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ ከሞት በተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ክርስቲያኖች እምነት እንዲኖራቸው አሳስበዋል።

ክቡራትን እና ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ፥ መጋቢት 29/2016 ዓ. ም. በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል በማስተንተን ለምዕመናን ያሰሙትን ስብከት ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ መልካም እሑድን እመኝላችኋለሁ! ዛሬ የፋሲካ በዓል በተከበረ በሁለተኛው እሑድ ላይ እንገኛለን። የዛሬው እሑድ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፥ ስለ መለኮታዊ ምሕረት እንድናስታውስ ያሳሰቡን ዕለት ነው። ከዮሐ. 20፡ 19-30 ተወስዶ የተነበበው የወንጌል ክፍልም፥ የእግዚአብሔር ልጅ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ እና በስሙም በማመን የዘላለምን ሕይወት እንደምናገኝ ይነግረናል (ቁ. 31)። ‘የዘላለም ሕይወት ማግኘት’ ማለት ምን ማለት ነው?

ሁላችንም ሕይወት እንዲኖረን እንፈልጋለን፤ ነገር ግን ሕይወትን የምናገኝባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ሕልውናን ወደሚቀንሱ በርካታ ነገሮች ዘንድ መሮጥ፥ ሥጋዊ ደስታ ለማግኘት፥ ለመብላት እና ለመጠጣት፣ ለመደሰት፣ ገንዘብን እና ሃብትን ለመሰብሰብ፣ ጠንካራ እና አዲስ ስሜትን ለመፍጠር መጣር፣ መጀመሪያ ሲያዩት ደስታን የሚሰጥ የሚመስል፥ ነገር ግን ልብን የማያረካ መንገድ ወዘተ። አንድ ሰው ሕይወት ሊኖረው የሚችለው በዚህ መንገድ አይደለም። ምክንያቱም ደስታን እና ስልጣንን በመሻት ደስታ አይገኝም። በእርግጥ ፍቅር፣ ህመም፣ አቅመ ደካማነት እና ሞት የመሳሰሉ ብዙ የህልውና ገጽታዎች መልስ አያገኙም። የሁላችን የጋራ ሕልሞች፣ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እና ያለ ገደብ መወደድ ፍጻሜን ሳያገኝ ይቀራል። እያንዳንዳችን ልናገኘው የተጠራንለት ይህ የሕይወት ሙላት በኢየሱስ ክርስቶስ እውን መሆኑን ዛሬ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል ይነግረናል። የሕይወት ሙላት የሚሰጠን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ይናገራል። ነገር ግን አንድ ሰው ወደዚህ እንዴት ሊደርስበት ይችላል? እንዴትስ ሊለማመደው ይችላል?

በቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንደተጠቀሰው በደቀ መዛሙርቱ ላይ የደረሰውን እንመልከት። ደቀ መዛሙርቱን በሕይወታቸው ውስጥ እጅግ አሳዛኝ ጊዜ አጋጥሞአቸዋል። ከኢየሱስ ክርስቶስ የሕማማት ቀናት በኋላ ተስፋን በመቁረጥ በፍርሃት ውስጥ ይገኙ ነበር። ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እነርሱ መጥቶ የቆሰሉ እጆቹን እና ጎኑን አሳያቸው (ዮሐ. 20:20)። እነዚህ ቁስሎች የመከራ እና የሕመም ምልክቶች ነበሩ። የበደለኛነትን ስሜት ሊቀሰቅሱ ይችሉ ነበር። ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የምህረት እና የይቅርታ መንገዶች ሆኑ። በዚህ መንገድ ደቀ መዛሙርቱ ቁስሎቹን አይተው በእጃቸው በመዳሰስ፥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሲሆኑ ሕይወትን እንደሚያገኙ እና ዘወትር አሸናፊዎች እንደሚሆኑ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከሆኑ ሞት እና ኃጢአት የሚሸነፍ መሆኑን ተገነዘቡ። ተወዳጅ ልጆቹ ሆነው በደስታ፣ በፍቅር እና በተስፋ የተሞላ አዲስ ሕይወት የሚሰጣቸውን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ተቀበሉ። አንድ ነገር ልጠይቃችሁ! ተስፋ አላችሁ? እያንዳንዳችሁ “ተስፋዬ ምንድነው?” በማለት እስቲ ራሳችሁን ጠይቁ።

በየዕለቱ ሕይወትን ማግኘት የምንችለው በዚህ መንገድ ነው። ለእኛ ሲል የተሰቀለውን እና ከሞት የተነሳውን ኢየሱስ ክርስቶስን መመልከቱ በቂ ነው። በምስጢረ ቁርባን እና በጸሎት አማክይነት ከእርሱ ጋር በመገናኘት፣ በእርሱ በማመን፣ ራሳችንን በጸጋው እንድንነካ በማድረግ፣ በእርሱ ምሳሌ በመመራት እንደ እርሱ የመውደድ ደስታን ልናጣጥመው እንችላለን። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የምናደርገው እያንዳንዱ ሕያው ግንኝነት ብዙ ሕይወት እንዲኖረን ያስችለናል። ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን የሚፈልገን በመሆኑ፥ እኛም እርሱን መፈለግ፣ ራሳችንን ለእርሱ ማቅረብ እና ልባችንን ልንከፍትለት ይገባል።

በኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ ኃይል አምናለሁ? ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት እንደ ተነሣ አምናለሁ? ኃጢአትን፣ ፍርሃትን እና ሞትን ድል ባደረገው በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ? ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ግንኙነት እንዲኖረኝ ራሴን ዝግጁ አደርጋለሁ? ወንድሞቼን እና እህቶቼን እወዳቸዋለሁ? በየቀኑ በተስፋ ለመኖር ጥረት አደርጋለሁ? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ። እስቲ እያንዳንዳችሁ በዚህ ጉዳይ ላይ አስቡበት።

ሕይወትን በሚሰጠን እና ከሞት በተነሳው በኢየሱስ ላይ የበለጠ እምነት እንዲኖረን እና የብርሃነ እንሳኤውን ደስታ ለሌሎች ማድረስ እንድንችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን።”

 

08 April 2024, 17:15