ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሮም ውስጥ በቅዱስ ሄንሪ ቁምስና ተገኝተው ካህናትን ጎብኝተዋል
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሮም ሀገረ ስብከት ውስጥ በየጊዜው የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ዓርብ መጋቢት 27/2016 ዓ. ም. አካሂደዋል። ቅዱስነታቸው በሮም ሰበካ ሰሜን ምሥራቅ በሚገኝ 11ኛ ሐዋርያዊ ክልል ውስጥ የሚያገለግሉ ካኅናትን ዓርብ መጋቢት 27/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ሄንሪ ቁምስና ውስጥ መጎብኘታቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል አስታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሀገረ ስብከታቸው በተከታታይ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት አቋርጠው ቆይተው ዘንድሮ በመስከረም ወር መጀመራቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በሮም ዳርቻዎች የሚያደርጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2015 ዓ. ም. ባወጁት የምሕረት ኢዮቤልዩ ዓመት የጀመሯቸው “የምሕረት ዓርብ” ጉብኝቶች ቀጣዮች እንደሆኑ ታውቋል።
አስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ የሚታይበት ሠፈር
ቅዱስነታቸው በቅርብ ወራት ውስጥ ከጎበኟቸው አራት ቁምስናዎች መካከል አንዱ የሆነው የቅዱስ ሄንሪ ቁምስና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1997 እና 1998 መካከል በዘመናዊ ዘዴ በእንጨት መዋቅር የተገነባ፣ መናፈሻ እና መጫወቻ ሥፍራዎች ያሉት ቢሆንም ነገር ግን የአካባቢው ነዋሪዎች የኑሮ ችግር ያለባቸው እና ችላ የተባሉ እንደሆኑ ተመልክቷል።
ከካህናቱ ጋር የተደረገ ውይይት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ቁምስናው ሲደርሱ የአካባቢው ጳጳስ አቡነ ዳንኤል ሳሌራ፣ የቁምስናው መሪ ካኅን አባ ማሲሚሊያኖ ሜማ እና 35 የሐዋርያዊ ክልሉ ካህናት አቀባበል አድርገውላቸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጥለው በአካባቢው ያሉ የሐዋርያዊ አገልግሎት ጉዳዮችን በማስመልከት ከካህናቱ ጋር ተወያይተዋል።
ከካህናቱ ጋር ተወያይተው ሲወጡ ወደ 50 የሚጠጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሰላምታ ያቀረቡላቸው ሲሆን፥ በዋነኛነትም አረጋውያን፣ ሴቶች፣ የትምህርት ቤት ሕጻናት እና በቁምስናው ውስጥ የሚሠሩ በርካታ መነኮሳት እንደነበሩ ተመልክቷል።
የማረሚያ ቤት ውስጥ ችግር
ሮም ውስጥ ከሚገኝ የረቢቢያ ማረሚያ ቤት የመጡ በርካታ ካህናት በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በተመለከተ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባደረጉት ገለጻ፥ በማረሚያ ቤቶቹ ውስጥ ራስን በራስ የማጥፋት አደጋ እንዳለ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን ለታራሚዎች የምታበረክታቸውን አገልግሎቶች በማስመልከት ገለጻ አድርገውላቸዋል።
የአካባቢው ጳጳስ አቡነ ዳንኤል ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፥ አንዳንድ ቆሞሳት አገልግሎታቸው እና ትምህርታቸው ብዙውን ጊዜ መንገዳቸውን ለማቃናት እና ወደ አዲስ ሕይወት ለመግባት ዕድሎችን እንደሚያመቻቹላቸው ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መግለጻቸውን ጠቅሰው፥ “የረቢቢያ ማረሚያ ቤት ካኅናት በሥፍራው መገኘታቸው ውይይቱ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ላይ እንዲያተኩር አድርጎታል” ሲሉ ተናግረዋል።
የምሕረት ዓመት፣ ወጣቶች እና የኢዮቤልዩ ክብረ በዓል
የአካባቢው ረዳት ጳጳስ አቡነ ዳንኤል እንደተናገሩት፥ ከቅዱስነታቸው ጋር በተደረገው ውይይት ሁሉም ካኅናት እና ዲያቆናት መደሰታቸውን ገልጸው፥ ከውይይቱ ርዕሠ ጉዳዮች መካከለ አንዱ “ምሕረት” የሚል እንደ ነበር ገልጸው፣ ይህም ከቤተ ክርስቲያን እንደ ራቁ የሚሰማቸውን ጨምሮ የክኅነት አገልግሎታቸውን ያቋረጡትንም የሚያካትት እንደ ነበር ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “በመጪው የኢዮቤልዩ ክብረ በዓል፣ የሮም ሀገረ ስብከት በሚያካሂደው ሲኖዶሳዊ ሂደት እና ወደ ቅዱስ ዓመት በሚያደርገው ጉዞ ደስተኛ ነኝ” ማለታቸውን ገልጸዋል። አቡነ ዳንኤል በመጨረሻም “በካህናት ዝግጅት ላይ ሴቶችን ማካተት” በሚለው ርዕሥ ላይም ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል።
ር. ሊ. ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ወደ ሥፍራው ያደረጉት ጉብኝት
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በየካቲት ወር 2002 ዓ. ም. የቅዱስ ሄንሪ ቁምስናን ከጎበኙት በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አካባቢውን የጎበኙ ሁለተኛው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እንደሆኑ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በውቅቱ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የቁምስናው ምዕመናን በአብዛኛው ወጣት ማኅበረሰብ እንደሆኑ ገልጸው፥ በጊዜው የመጀመሪያ እና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እጥረት ቢኖርም በጊዜ ሂደት የተገነቡት ትምህርት ቤቶች እንዳሉ መናገራቸው ይታወሳል።