ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የጣሊያን ቀይ መስቀል ማኅበር አባላትን በቫቲካን ተቀበሉ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የጣሊያን ቀይ መስቀል ማኅበር አባላትን በቫቲካን ተቀበሉ  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

የቀይ መስቀል ማኅበር የሰብዓዊነት ተግባር ወንድማማችነትን ማረጋገጥ እንደሚያስችል ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጣሊያን ቀይ መስቀል ማኅበር አባላትን በቫቲካን ተቀብለዋል። ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባሰሙት ንግግር፥ ማኅበሩ የጦርነት እና የሌሎች አደጋዎች ሰለባ ለሆኑ ሰዎች የሚሰጠውን መተኪያ የሌለው ሰብዓዊ ጥበቃ እና ድጋፍ አወድሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተመሠረተበትን 160ኛ ዓመት ከሚያከብሩት የጣሊያን ቀይ መስቀል አባላት ጋር ቅዳሜ መጋቢት 28/2016 ዓ. ም.  ተገናኝተዋል። ማኅበሩ በወቅቱ በጄኔቭ ስዊዘርላንድ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1863 ዓ. ም. የተመሠረተውን የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማኅበር ተከትሎ በሰሜን ጣሊያን ሚላን ከተማ ውስጥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1864 ዓ. ም የተቋቋመ ሲሆን ዓላማውም በጦርነት ለተጎዱ እና ለታመሙት ዕርዳታን ለማቅረብ እንደ ነበር ይታወሳል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ ጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ለተሰበሰቡት 6,000 ለሚሆኑ የጣሊያን ቀይ መስቀል ማኅበር በጎ ፈቃደኞች እና ሠራተኞች ባሰሙት ንግግር፥ በዓለም ዙሪያ በጦርነት እና በሌሎች አደጋዎች ለሚሰቃዩት ሰዎች ለሚያደርጉት ሰብዓዊ ዕርዳታ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ተጨባጭ የወንድማማችነት ምልክት

ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባሰሙት ንግግር፥ የበጎ ፈቃደኞቹ ቁርጠኝነት በሰብዓዊነት፣ በገለልተኝነት፣ በነጻነት፣ በበጎ ፈቃደኝነት፣ በአንድነት እና በሁለንተናዊነት መርሆዎች በመነሳሳት ወንድማማችነትን በተጨባጭ ማሳየት የሚቻልበት ምልክት ነው” ሲሉ ገልጸውታል።

“የሰውን ልጅ ማዕከል ካደረጉ እርስ በርስ መወያየት እና ለጋራ ጥቅም በኅብረት መሥራት ይቻላል፤ ከመለያየት ይልቅ የጠላትነት ግድግዳን በማፍረስ የግል ጥቅም ፍለጋን እና ሌላውን እንደ ጠላት የመመልከት አመክንዎን ድል ማድረግ ይቻላል” ብለዋል።

ሕጻናት ለጦርነት አደጋ በጣም የተጋለጡ ናቸው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በግጭት ዞኖች እና በተፈጥሮ አደጋዎች ለተጎዱ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን ለስደተኞች እና ለተጋላጭ ሰዎች ለሚሰጠው ድጋፍ እና የማይተካ አገልግሎት የጣሊያን ቀይ መስቀል ማኅበርን በማመስገን፥ በተለይም ለጦርነት አደጋ ለተጋለጡት ሕፃናት በሚያበረክቱት ታላቅ የበጎ አድራጎት ሥራ እንዲቀጥሉ በማበረታታት፥ “ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ምን ጊዜም ቢሆን ድንበር ሳያግደው ባሕላዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ሃይማኖታዊ የወንድማማች ፍቅር ምልክት ሆኖ እንዲቆይ” በማለት መልካምን ተመኝተውለታል።

በሚፈለግበት ቦታ ሁሉ መገኘት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠል፥ “በሁሉም ቦታ ለማንኛውም ሰው መድረስ” የሚለውን የበዓሉን መሪ ሃሳብ መሠረት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፥ መሪ ሃሳቡ በተለይ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቱ ዘይቤ እና አስፈላጊነት የሚገልጽ ነው” በማለት አስረድተዋል።

“በሁሉም ቦታ” የሚለው፥ ከመከራ የፀዳ ቦታ አለመኖሩን የሚገልጽ፥ አንድነትን ዓለም አቀፋዊ ማድረግ እንደሚገባ እና እንዲሁም በሁሉም ቦታ ሰብዓዊ መብቶችን የሚያረጋግጡ ሕጎች እንደሚያስፈልጉ፣ ባሕልን የሚያዳብሩ ልማዶችን እና ዓለምን በስፋት መመልከት የሚችሉ ሰዎችን ማግኘት የሚገልጽ መሆኑን አስረድተዋል።

የሚሰቃዩትን ለመድረስ ዝግጁ መሆን

“ሁሉንም ሰው” የሚለው ቃል በሌላ በኩል እያንዳንዱ ሰው ክብር እና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን እና በኑሮ ሁኔታው፣ በደረሰበት የአካል ጉዳት እና ችግር ወይም በማኅበራዊ የኑሮ ደረጃ ምክንያት ወደ ጎን ሊባል ወይም ሊዘነጋ እንደማይገባ የሚያስታውስ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም በተለይም ዘረኝነት እና ንቀት እንደ እንክርዳድ በሚያድግበት በዚህ ወቅት፥ የጣሊያን ቀይ መስቀል ማኅበር ከተቸገሩት ሰዎች ጎን መቆሙን እንዲቀጥል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አደራ ብለዋል።

የምሥረታውን በዓል መሪ ቃል በማስታወስ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው የመጀመሪያ መልዕክቱ ምዕ. 9:22 ላይ “ደካሞችን እጠቅም ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንኩኝ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፥ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንኩኝ” ያለውን በማስታወስ፥ የወንጌልን ደስታ ለሁሉ የማድረስ ተልዕኮው እና ይህም ወንድማማችነትን ባሳዩ ቁጥር ቢያንስ ስቃይን ለማቃለል የሚጠቀሙበት ስልት እንደሆነ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጣሊያን ቀይ መስቀል ማኅበር አባላት የወንድማማችነት እና የሰላም መሣሪያዎች በመሆን፣ የበጎ አድራጎት ተዋናዮች፣ በዓለም ውስጥ የወንድማማችነት ግንባታ አጋዦች እንዲሆኑ የእግዚአብሔርን ጸጋ በመማጸን ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።

 

08 April 2024, 17:01