ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ ለካቶሊኬንታግ ቡድን አባላት በጸሎት እና በውይይት ለሰላም ሥሩ ማለታቸው ተገለጸ
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
ካቶሊኬንታግ ካቶሊክ ከተሰኘው የእንግሊዘኛው ቃል የተተረጎመ እና የተወሰደ ሲሆን በጀርመንኛ ቋንቋ ተናጋሪ አገሮች በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን የተዘጋጀ ፌስቲቫል መሰል ስብሰባ ነው። የካቶሊኬንታግ በዓላት በየ2-4 ዓመቱ በጀርመን፣ ስዊዘርላንድ እና ኦስትሪያ ይካሄዳሉ።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ግንቦት 21/2016 ዓ.ም አመሻሽ ላይ በኤርፈርት ከተማ በተከፈተው የጀርመን ካቶሊኮች ብሔራዊ ስብሰባ 103ኛው የካቶሊኬንታግ (የካቶሊክ ቀን) ተሳታፊ ለሆኑ ሰዎች መልእክት ልከዋል።
የሰላም ሰው መጻይ ጊዜ አለው
በየአመቱ በተለያዩ ከተሞች የሚከበረው የአምስት ቀን በዓል በጀርመን እ.አ.አ በ1848 ዓ.ም የጀመረውን ልዩ ባህል ያሳያል። በሀገሪቱ ውስጥ ካቶሊኮችን በመሰብሰብ ትልቅ እና አስፈላጊ ከሆኑት ማህበራዊ ዝግጅቶች መካከል አንዱ ነው ፣ ነገር ግን ከጀርመን የመጡ የፖለቲካ እና የሃይማኖት መሪዎችም እንዲሁ የሚሳተፉበት ዝግጅት ሲሆን እናም ከውጭ አገር የመጡ ሰዎችም ጭምር የሚሳተፉበት እምነትን ለማክበር እና በጀርመን ማህበረሰብ ላይ ተጽእኖ ያላቸውን ርዕሰ ጉዳዮች ለመወያየት ታስቦ የተመሰረተ ቀን ነው፥ ለዘንድሮው ስብሰባ የተመረጠው መሪ ቃል "የሰላም ሰው የወደፊት ዕጣ ፈንታ አለው" የተሰኘ እንደሆነም ተዘግቧል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልእክታቸው በመዝሙር 37 ላይ የሚገኙት እነዚህ ቃላት የሚነግሩን ጻድቃን ለሆኑት፣ ጌታን ደስ የሚያሰኙ እና በእርሱ ለሚታመኑት ሰላም ተስፋ እንደሚሰጥ ነው ያሉ ሲሆን ሆኖም የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ላይ ያለው ታሪካዊ አለመተማመን፣ አለመስማማት እና መከራ አስከትሏል ሲሉ ገልጸዋል።
“የሰው ልጅ ፍጥረታትን እንደ ፈጣሪ ሐሳብ አይጠቀምም፣ ነገር ግን ለሥልጣንና ለጥቅም ባለው የራስ ወዳድነት ምኞቱ አበላሸው። ስለዚህ መከራና ሞት ወደ ዓለም መጡ” ሲሉ ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች በተለይም ወጣቶች በዓለም ላይ አንድ ስህተት እንዳለ በመገንዘብ የአቅጣጫ ለውጥ እንደሚያስፈልጋቸው ይሰማቸዋል ብለዋል። ይህንንም ተናግሯል። በትክክል የኢየሱስ ተልእኮ ነበር፡ ሰውን ወደ እግዚአብሔር ማቅናት እና ከዚህም ጋር “ከወንድሞቹ ጋር ያለውን ግንኙነት፣ ከፍጥረታት እና በመጨረሻ ግን ከራሱ ጋር ያለውን ግንኙነት” ማደስ እና መፈወስ ፈልጎ ነበር ብለዋል።
ፍትህ ከሌለ ሰላም ሊኖር አይችልም።
ኢየሱስ በተራራ ባደረገው ስብከት እንደሚታየው ተስፋ በመስጠትና ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን በማውገዝ ብዙውን ጊዜ የሰዎችን የሥነ ምግባር እሴቶች በመሻር ላይ ያሉ ነገሮችን በመተው ሰላምን እንዳመጣ ተናግሯል። ከፍቅርና ከውዳሴ የተወለደ ሰላሙ በመስቀሉና በትንሳኤው የተመሰከረለት ሲሆን “የሰላም ሰው የወደፊት ዕጣ ፈንታ አለው” በማለት ተናግረዋል።
“ክርስቶስ የሚያመጣው ሰላም ለሰዎች አዲስ ተስፋ ሲሰጥ፣ በአስቸጋሪ ጊዜያት የወደፊት ተስፋን ሲሰጥ ይታያል፡- ለተገለሉት፣ ለታማሚዎች፣ በኃጢአት ለተጠመዱ ሁሉ ሰላም እና ምሕረት እንደሚያመጥ ገልጸዋል።
ስለዚህ ክርስቲያኖች የተገለሉትን በመርዳት እና በሕዝብ ሕይወት ውስጥ የኑሮ ሁኔታቸውን እንዲያሻሽሉ በማድረግ የኢየሱስን ተልእኮ እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
የተጠላለፉ ቀውሶች የጋራ መፍትሄዎች እና ውይይት ያስፈልጋቸዋል
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ፀረ ሴማዊነት፣ ዘረኝነት እና ሌሎች ጽንፈኛ እና ሁከት አስተሳሰቦች በአውሮፓ እና ከዚያም አልፎ መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶችን አደጋ ላይ የሚጥሉ አስተሳሰቦችን አውግዘዋል። በአሁን ሰዓት አለም እየተጋፈጠ ያለው የሞራል፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ትስስር ምን ያህል እንደተሳሳተ እና በዚህም በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ሰፊ ውይይት በማድረግ የጋራ መፍትሄዎችን እንደሚያስፈልግ በድጋሚ አስምረውበታል። ካቶሊኬንታግ ለእንደዚህ ዓይነት ውይይቶች መድረክ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
"የተፈጥሮ ስጋት ለድሆች ፍትህ፣ ለህብረተሰቡ ቁርጠኝነት፣ የህይወት እና የቤተሰብ ጥበቃ፣ የእያንዳንዱ ሰው ህይወት ክብር ጥበቃ እንዲሁም ውጫዊ እና ውስጣዊ ሰላም አብረው የሚሄዱ ችግሮች ናቸው" ብለዋል።
ሃይማኖታዊ እና ሕብረትን የሚፈጥሩ ውይይቶችን ማዳበር
መልዕክቱ በተለይ ለወደፊት ሰላማዊ ህይወት ግንባታ አስፈላጊ የሆኑትን ማኅበረሰባዊ እና ሃይማኖታዊ ውይይቶችን ለማበረታታት መድረኩን አመስግኗል።
የዝግጅቱ መሪ ቃል ይህንን መንገድ ለመከተል የሚያበረታታ መሆኑን በመጥቀስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማጠቃለያው ተሳታፊዎች ስለ ሰላም እና አንዳቸው ለሌላው እንዲጸልዩ በመጋበዝ ስብሰባው “ታላቅ የመንፈሳዊ ብልጽግና” እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል።