ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ የወደቁትን ወደ መልካም ሕይወት መመለስ እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ባቅረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው በአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛነት የወደቁትን ወደ ሕይወት መመለስ እንደሚገባ አሳሰበዋል። የቅዱስነታቸውን አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘት ከማቅረባችን አስቀድመን ለአስተንትኖ እንዲሆናቸው የመረጡትን የቅዱስ መጽሐፍ ክፍል እናቀርብላችኋለን።

“ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን አይጠቅምም። ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሠለጥንብኝም። ምግብ ለሆድ ነው፥ ሆድም ለምግብ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሰውነት ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሰውነት ነው፤
እግዚአብሔርም ጌታን ከሞት አስነሣ፥ እኛንም በኃይሉ ያስነሣናል” (1ኛ ቆሮንቶስ 6፣ 12-14)።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
ዛሬ እ. ኤ. አ. በ1987 በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ድንጋጌ መሠረት አደንዛዥ ዕፅን አላግባብ መጠቀምን እና ሕገወጥ ዝውውሩን ለመከላከል የተውሰነበት ዓለም አቀፍ ቀን የሚከበርበት ዕለት ነው።የዘንድሮው ጭብጥም፥ የአደንዛዥ ዕፅ አላግባብ መጠቀምን እና ሕገወጥ ዝውውሩን በመከላከል ላይ መሥራት እንደሚገባ ያሳስባል።

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንዲህ ሲሉ ተናግረው ነበር። “አደንዛዥ ዕፅን አላግባብ መጠቀም እያንዳንዱን ማኅበረሰብ ያደኸያል። የሰውን ልጅ ጥንካሬን እና የግብረ ገብ ደረጃን ይቀንሳል። የተከበሩ እሴቶችን ያዳክማል። መልካም ሕይወት ለመኖር እና የተሻለ ማኅበረሰብን ለመገንባት የሚያግዝ አስተዋፅዖ ለማድረግ ያለንን ፍላጎት ያበላሻል። እንደዚሁም እያንዳንዱ የአደንዛዥ ዕጽ ሱሰኛ እንደ እግዚአብሔር ልጅ ልዩ የግል ታሪክ ያለው በመሆኑ ሊደመጥ፣ ሊታግዝ፣ ሊወደድ እና በተቻለ መጠን ሊፈወስ እንደሚገባ እናስታውስ…

ይሁን እንጂ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ክፉ ዓላማ እና ድርጊታቸውን ችላ ልንል አንችልም። የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ የሕክምና ማኅበረሰብን በጎበኙበት ወቅት ጠንከር ያሉ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል:- ‘የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ስፍር ቁጥር በሌላቸው ወጣቶች እና ከየትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በተውጣጡ ጎልማሶች ላይ እያደረሱ ያለውን ከባድ ጉዳት እንዲያስቡበት አሳስባለሁ፤ እግዚአብሔር ለሥራችሁ ተጠያቂ ያደርጋችኋል። በዚህ መንገድ የሰው ልጅ ክብር ሊረገጥ አይችልም’ ብለዋል።

በአንዳንድ አገሮች እንደታቀደው ወይም ቀደም ሲል በተተገበረው ሕግ መሠረት የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነትን መቀነስ የሚቻለው የአደንዛዥ ዕፅ አጠቃቀምን ነፃ በማድረግ አይደለም። የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኞች እና ቤተሰቦቻቸው ብዙ አሳዛኝ ታሪኮች ስለሚታወቅ እነዚህን አደገኛ ንጥረ ነገሮች ማምረት እና ማዘዋወርን ማቆም የሞራል ግዴታ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ። በኃይል እና በገንዘብ አመክንዮ የሚነዱ ስንት የሞት አዘዋዋሪዎች አሉ! ይህን ዓመፅን የሚያመጣ እና መከራን እና ሞትን የሚዘራ መቅሰፍት ለማስወገድ የጠቅላላው ማህበረሰብ ድፍረትን ይጠይቃል።

የአደንዛዥ ዕፅ ምርት እና ዝውውሩ በጋራ መኖሪያ ምድራችን ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል። ይህም በአማዞን ተፋሰስ አገራት ውስጥ ይበልጥ ግልጽ ሆኗል።

ሌላው የአደገኛ ዕፆች አላግባብ መጠቀም እና ሕገወጥ ዝውውራቸውን መከላከል ሲሆን ይህም የላቀ ፍትህን በማስፈን ወጣቶችን የግል እና የማህበረሰብ ህይወትን በሚገነቡ እሴቶች በማስተማር፣ ችግሩ ያለባቸውን በመደገፍ እና የወደፊት ተስፋን በመስጠት ነው።

በተለያዩ ሐዋርያዊ ጉብኝቶቼ ወቅት በቅዱስ ወንጌል አነሳሽነት ከዚህ ከባድ አደጋ በማገገም ላይ የሚገኙ ማኅበረሰቦችን መጎብኘት ችያለሁ። ካህናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም ምእመናን የደጉ ሳምራዊ ምሳሌን በተግባር ላይ ለማዋል ያላቸው ቁርጠኝነት ጠንካራ እና ተስፋ ሰጪ ምስክርነት ነው። እንደዚሁም የተለያዩ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ ለሆኑ ሰዎች በሚያደርጉት እንክብካቤ እና ይህን መቅሰፍት ለመከላከል የሚያግዙ ፍትሃዊ ሕጎችን እና ፖሊሲዎችን ለማበረታታት በሚያደረጉት ጥረት ተጽናንቻለሁ።

በላቲን አሜሪካ ውስጥ የተዘረጋው አውታረ መረብ ለአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኞች ከሚያደረገው ሐዋርያዊ እንክብካቤ በተጨማሪ አደጋውን ለመከላከል በማድረግ ላይ ያለውን ጥረት እና የተወሰዱ ውሳኔዎችን እንደ ምሳሌ መጠቆም እችላለሁ። የዚህ አውታረ መረብ ሠነድ ‘የአልኮል ሱሰኝነት፣ ስነ-ልቦናን የሚጎዱ ንጥረ ነገሮች፣ ሌሎች ሱሶችም ለምሳሌ እንደ ወሲብ ቀስቃሽ ፅሑፎች እና ምስሎች፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና ወዘተ ከመልክአ ምድራዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና የዕድሜ ደረጃዎችን እንኳ ሳይለይ ያለ ልዩነት የሚጎዱን ችግሮች መሆናቸውን ያስገነዘባል። ሠነዱ በማከልም፥ ‘ልዩነቶች ቢኖሩም እንደ አንድ ማህበረሰብ በመደራጀት ልምዶችን፣ ምኞቶቻችንን፣ ችግሮቻችንንም በጋራ ለመካፈል እንፈልጋለን’ በማለት ያስገነዝባል።

የደቡብ አፍሪካ ብጹዓን ጳጳሳትንም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በኅዳር ወር 2023 ዓ. ም. ‘ወጣቶችን የሰላም እና የተስፋ ወኪሎች እንዲሆኑ ማብቃት’ በሚል መሪ ርዕሥ ላይ የጠሩትን ስብሰባ እጠቅሳለሁ። በስብሰባው ላይ የተገኙት የወጣት ማኅበራት ተወካዮች ስብሰባው ‘በመላው ክልል ጤናማ እና ንቁ ወጣቶች ላይ ያተኮረ ትልቅ ምዕራፍ’ መሆኑን ተገንዝበዋል። ተወካዮቹ በተጨማሪም ‘አደንዛዥ ዕጽ መጠቀምን ለመዋጋት አምባሳደሮች እና ተሟጋቾች የመሆንን ሚና እንቀበላለን። ወጣቶች በሙሉ ዘወትር እርስ በርስ እንዲተሳሰቡ እና እንዲረዳዱ እንለምናለን” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት አሳዛኝ ሁኔታ፣ በሕገወጥ ምርት እና አዘዋዋሪነት ያጋጠማቸውን ቅሌት ቸል ልንል አንችልም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰው ልጅ ቀርቦ ቁስሎችን ፈውሷል። የእርሱ የቅርበት ዘይቤን በመከተል እኛም ደግሞ የእርሱን ምሳሌ እንድንከተል ተጠርተናል። ከችግር እና ከህመም ሁኔታዎች ፊት ቆመን የብቸኝነት እና የጭንቀት ጩኸትን እንዴት ማድመት እንደሚገባ ለማወቅ፣ በአደንዛዥ ዕፅ ባርነት የወደቁትን ጎንበስ ብለን እንድናነሳ እና ወደ ሕይወት እንድንመልስ ተጠርተናል።

በዚህ ዓለም አቀፍ የአደንዛዥ ዕፅ ቀን፣ እንደ ክርስቲያኖች እና የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች፣ ዓላማው እንዲሳካ በመጸለይ ቃል ኪዳናችንን እናድስ፤ አመሰግናለሁ!”

 

26 June 2024, 17:15