በደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ በካን ዮኒስ ጦርነት ያደረሰው ጥፋት በደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ በካን ዮኒስ ጦርነት ያደረሰው ጥፋት  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጦርነት ለሁሉም ወገን ሽንፈት በመሆኑ ቶሎ ሊቆም ይገባል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች ተወካዮችን ሐሙስ ሰኔ 20/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ለተወካዮቹ ባስተላለፉት መልዕክት ለሰላም ያላቸውን ጽኑ አቋም እንዲያድሱ ጠይቀው በአካባቢው አገራት በጦርነት ምክንያት ለሚሰደዱት እና መከራ ውስጥ ለወደቁት የምሥራቅ አብያት ክርስቲያናት ምዕመናን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው ከምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች ተወካዮች ጋር በቫቲካን ተገናኝተው ባሰሙት ንግግር ለዓለም ሰላም በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ እና በዩክሬን ሰላም እንዲሰፍን ያላቸውን ልባዊ ምኞት በድጋሚ ገልጸዋል።

“ጦርነትን የሚያቀጣጥሉ እና ከጦርነት እናተርፋለን የሚሉት በሙሉ ከዚህ የተሳሳተ ዓላማ እንዲመለሱ አሳስበው፥ ከሁከት እና ከግጭት ሰላም ሊገኝ እንደማችል በሮም የድርጅቱን 97ኛ ምልአተ ጉባኤን ላካሄዱት የቤተ ክርስቲያን የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች ተወካዮች አስገንዝበዋል።

ለመካከለኛው ምሥራቅ እና ለዩክሬን ትኩረትን መስጠት
በሮም በሚገኘው የኢየሱሳውያን ማኅበር ጠቅላይ ቤት ውስጥ ለአራት ቀናት የተካሄደው ስብሰባ በቅድስት አገር፣ በዩክሬን እና እንዲሁም በኢትዮጵያ ያለውን አስከፊ ሁኔታ ላይ ከማትኮሩ በተጨማሪ የስብሰባው ተሳታፊዎች ከግዛቶቻቸው ውጭ በስደት ለሚገኙ በርካታ የምሥራቅ ካቶሊክ ምዕመናን በሚደረግላቸው የሐዋርያዊ እረኝነት እንክብካቤ ላይም ተወያይተዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች ተወካዮችን ጋር በተገናኙበት ወቅት
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች ተወካዮችን ጋር በተገናኙበት ወቅት

ሰማዕትነትን የተቀበሉ አብያተ ክርስቲያናት
ብዙ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የሰማዕትነትን ጽዋ መጎንጨታቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ በምስማርና በጦር እንደተወጋ ሁሉ ብዙ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ማኅበረሰቦችም ባጋጠሟቸው ግጭቶችና ብጥብጦች ምክንያት እየተሰቃዩ እና እየደሙ ናቸው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ቅድስት ሀገር እና ዩክሬንን፣ ሶርያን፣ ሊባኖስን፣ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትን፣ በአውሮፓ እና በእስያ መካከል የሚገኙ አገራትን፣ እንዲሁም ትግራይን ጨምሮ ግጭቶች የሚታዩባቸውን የኢትዮጵያ ክፍሎችን አስታውሰው፥ ጦርነት በካሄድባቸው በእነዚህ አገራት ውስጥ እጅግ በርካታ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ካቶሊካዊ ምዕመናን እንደሚገኙባቸው ጠቅሰዋል።

“በርካታ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ከባድ መስቀል ተሸክመው የሰማዕትነት ዋጋ ከፍለዋል” በማለት ለእነዚህ ምዕመናን ያላቸውን አብሮነት በማደስ፥ “ለስቃያቸው ግድ የለሾች መሆን አንችልም” ብለዋል።

የቤተ ክርስቲያኒቱ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች ተወካዮች ለምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲቀጥሉ አበረታትተው፥ በእነዚህ አስጨናቂ ጊዜያት ወንጌልን መሠረት በማድረግ እገዛ መስጠትን እንዲቀጥሉ አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ቀሳውስት እና ገዳማውያን የመንጋቸውን ጩኸት በትኩረት እንዲከታተሉ፣ በእምነትም አርአያዎች እንዲሆኑ፣ ከማንኛውም ዓይነት አለመግባባት ወይም ጥቅም ይልቅ ወንጌልን በማስቀደም እና አንድነትን በማገልገል ለጋራ ጥቅም እንዲተባበሩ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያኒቱን የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች ተወካዮች ለሰጡት ክርስቲያናዊ የአገልግሎት ምላሽ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። “በጥላቻ እና በጦርነት በተመረዙት እርሻዎች ላይ የምትዘሯቸው ዘሮች፣ በሰላም ኃይል ላይ በመሆኑ የማያምን ደንዳና ልብ ላለው ዓለም ትንቢት ይሆናል” ብለዋል። “ቅዱስ ወንጌል እንደሚነግረን እናንተ በደግነትና በማስተዋል ለሥራ የተጠራችሁ የተስፋ ዘሪዎች እና ምስክሮች ናችሁ” በማለት አመስግነዋል።

በቅድስት ሀገር ተኩስ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችኮስስ በተለይ በቅድስት ሀገር ያለውን አስጨናቂ ሁኔታን በመጥቀስ፥ በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚገኙ ክርስቲያኖች “በግጭት የተመሰቃቀለውን መሬታቸውን ጥለው እንዲወጡ ከሚያደርጋቸው ፈተና እንዲወጡ በማበረታታት፥ በመላው ዓለም የሚገኙ ምእመናን በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ያላቸውን ቅርበት በተጨባጭ መንገድ እንዲያሳዩ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።

በቅድስት ሀገር በአስቸኳይ ተኩስ ቆሞ ለሰላም ውይይት እንዲደረግ፣ በእነዚያ አገሮች ውስጥ ያሉ ልዩ ልዩ ሕዝቦች በሰላም አብረው እንዲኖሩም አሳስበዋል። “ወደ ተረጋጋ ሕይወት ለመድረስ የሚያስችል ብቸኛው አማራጭ ይህ ነው” ብለው፥ “ጦርነት ከመጀመሪያው ጀምሮ ዘወትር ሽንፈትን የሚያከናንብ፣ ሁሉም ወገን የሚሸነፍበት ትርጉም የሌለው እንደሆነም አስረድተዋል።

“ጦርነት ባስከተለው መዘዝ የሚሰቃዩትን፣ የተጎዱትን እና ቤት ንብረታቸውን ያጡትን በሙሉ እናዳምጥ። ጦርነትን የሚቀሰቅሱ ንግግሮች፣ ሌሎችን ጥፋተኛ የሚያደርጉ ባዶ መፈክሮች፣ ዓለምን በክፋት የሚከፋፍሉ፣ ጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበው ሰላምን በውይይት ማምጣት የከበዳቸው መሪዎች ያሳዘናቸውን የአቅመ ደካማ ወጣቶች፣ የግለሰቦች እና የሕዝቦች ጩኸት ልንሰማ ይገባል” ብለዋል።

በዩክሬን ሰላም እንዲወርድ እና እስረኞች እንዲፈቱ መጸለይ
በጦርነት ውስጥ የምትገኘውን ዩክሬንን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ለሕዝቦቿ የሰላም መንገዶች እንዲከፈቱ፣ የጦር እስረኞች እንዲፈቱ እና የዩክሬን ሕጻናት ከሩስያ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ” በጸሎት እንድናግዛቸው በድጋሚ ጠይቀዋል። ለመላዋ የአርመንያ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያር ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ካሬኪን ዳግማዊ እና ግጭት ውስጥ ለወደቀው የአርመንያ ሕዝብ ወንድማዊ ሰላምታቸውን አስተላልፈዋል።

የፈንጂዎች ምልክቶች ያሉባቸው የዩክሬን አካባቢዎች
የፈንጂዎች ምልክቶች ያሉባቸው የዩክሬን አካባቢዎች

በውጭ አገራት የሚኖሩ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንን መደገፍ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ በርካታ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናን ግጭቶችን በመሸሽ ወይም ሥራ ፍለጋ እና ሰላም የሰፈነበት የተሻለ ሕይወት ፍለጋ መሰደዳቸውን ጠቅሰዋል።

በወጭ አገራት የሚኖሩ እነዚህ ማኅበረሰቦች ሃይማኖታዊ ማንነታቸውን የማጣት እና ውድ የሆኑ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ቅርሶች በመዳከም አደጋ ላይ እንደሚገኙ አስታውሰው፥ የተሰደዱትን የምሥራቅ አብያት ክርስቲያናት ምዕመናን በእንግድነት ለሚቀበሉት ለላቲን ሥርዓተ አምልኮ ሀገረ ስብከቶች ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች ተወካዮችን በመንበራቸው ሲቀበሉ
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች ተወካዮችን በመንበራቸው ሲቀበሉ
28 June 2024, 16:19