ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮን ባቀረቡበት ዕለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮን ባቀረቡበት ዕለት  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጦርነት ለሚሰቃዩት የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ የሰላም አማላጅነት ለመኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬ ዕለት ካቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ አስተምህሮአቸው ክፍል በመቀጠል መጭው ቅዳሜ ሰኔ 22/2016 ዓ. ም. ቤተ ክርስቲያን በድምቀት የምታከብረውን እና የሮም ከተማ ባልደረባ የሆኑት የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ዓመታዊ በዓል በማስታወስ፥ በጦርነት ስቃይ ውስጥ ለሚገኙ የዩክሬን፣ የቅድስት ሀገር እና የምያንማር ሕዝቦች መካከል ሰላም እንዲወርድ ምዕምናን የቅዱሳኑን አማላጅነት በጸሎት እንዲጠይቁ አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ዛሬ ታስቦ የዋለውን ዓለም አቀፍ የአደንዛዥ ዕጽ ቀን ምክንያት በማድረግ የዚህ አደገኛ ዕጽ ሱሰኛ ለሆኑት አስፈላጊው እንክብካቤ እና ክትትል እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለም ዙሪያ ሁሉ ሰላም እንዲሆን ዘወትር ባላቸው ምኞት፥ ዛሬ ረፋዱ ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ካቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ አስተምህሮአቸው ክፍል ቀጥለው መጭው ቅዳሜ ሰኔ 22/2016 ዓ. ም. ቤተ ክርስቲያን በድምቀት በምታከብረው የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ዓመታዊ በዓል ዕለት ምዕመናኑ የቅዱሳኑን አማላጅነት እንዲለምኑ አደራ ብለዋል።

በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በጦርነት ምክንያት የሚሰቃዩ ሕዝቦች በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላም እንዲያገኙ በዩክሬን፣ በፍልስጤም እና በእስራኤል እንዲሁም በምያንማር ውስጥ ሰላም እንዲሆን ምዕመናን ጸሎት እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል።

ሁሉም ሰው የቅዱሳንን የሐዋርያትን አርአያ በመከተል ወንጌልን በየሥፍራው እየመሰከሩ ወንጌላውያን ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ጋብዘዋል። ለፖርቱጋል ቋንቋ ተናጋሪ ምዕመና ሰላምታ ሲያቀርቡ ባስተላለፉት መልዕክት፥ እምነታቸውን ማዳበር እንዲቀጥሉ እና የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር በማኅበረሰቦቻቸው መካከል በደስታ እንዲጋሩ አሳስበው፥ “ምኞታችሁ ከቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ሕይወት የመነጨ ይሁን” ብለዋል።

ወጣቶች በአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት እንዳይወድቁ እንርዳቸው
ቅዱስነታቸው ከፖላንድ ለመጡት ነጋዲያን ካቀረቡት ሰላምታ ቀጥለው አደንዛዥ ዕጽን አላግባብ መጠቀም እና ሕገ-ወጥ ዝውውሩን መከላከል የሚለውን የዕለቱ አስተምህሮ መሪ ሃሳብን በመጥቀስ፥ በቅርቡ የሚጀመረው የበጋ ወራት የዕረፍት ጊዜ ብዙ ወጣቶች የሚሳተፉበት ወቅት መሆኑን አስታውሰዋል። ስለሆነም ዛሬ የተከበረው ዓለም አቀፍ የአደንዛዥ ዕጽ ቀን ሁሉም ሰው ለህፃናት እና ለወጣቶች ደህንነት ልዩ ትኩረት የሚሰጥበት እንደሚሆን ተስፋ አድርገዋል። ር ዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ነጋዲያን ባስተላለፉት መልዕክት፥ የምሕረት ወንጌል መስካሪዎች እንደመሆናቸው መጠን በዚህም ሱስ ለተያዙት ሰዎች የሚደረግላቸው ዕርዳታ እስኪሰማቸው ድረስ ስቃያቸውን ማቃለል፣ መፈወስ እና መንከባከብ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጀርመንኛ ቋንቋ ተናጋሪ ነጋዲያን ባቀረቡት ማሳሰቢያ፥ “የአደንዛዥ ዕፅ አላግባብ መጠቀም በዘመናችን የብዙ ሰዎችን ውስጣዊ ስቃይ የሚያሳይ ነው” ብለው፥ ሁሉም ሰው ለጎረቤቱ የበለጠ ትኩረት እንድንሰጥ በመጋበዝ፥ “ዕርዳታችንም ሳይዘገይ ሊደርሳቸው ይገባል” በማለት አሳስበዋል። ለአረብኛ ቋንቋ ተናጋሪ ነጋዲያንም ባስተላለፉት መልዕክት "ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር የሚደረገው ትግል ለሰው ልጅ ክብር እና ሁሉም ሰው የተሻለ የወደፊት ተስፋ እንዲኖረው የሚደረግ ትግል ነው” በማለት አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው ጣሊያን ውስጥ ከልዩ ልዩ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች እና የቤተ ክርስቲያን ማዕከላት እና ቁምስናዎች ለመጡት ነጋዲያን ሰላምታቸውን አቅርበው፣ ከስፖርት መምህራን፣ ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለወጣት ማኅበራት ደማቅ አቀባበል ካደረጉላቸው በኋላ በመጨረሻም ዘወትር እንደሚያደርጉት ወጣቶችን፣ ሕሙማንን፣ አረጋውያንን እና አዲስ ተጋቢዎችን በማስታወስ ሰላምታቸውን ካቀረቡላቸው በኋላ የዕለቱ አስተምህሮአቸውን ደምድመዋል።


 

26 June 2024, 17:24