ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከዓለም ዙሪያ ከተውጣጡ አርቲስቶች ጋር ሲገናኙ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከዓለም ዙሪያ ከተውጣጡ አርቲስቶች ጋር ሲገናኙ  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለኮሜዲያን ‘የተሻለ ዓለምን እንድናልም እርዱን’ ማለታቸው ተገለጸ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከዓለም ዙሪያ ከተውጣጡ ከ100 በላይ ኮሜዲያኖች ጋር ተገናኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ሰዎችን እንዲያበረታቱ እና ሰዎች እውነታውን ከሁሉም ተቃርኖዎች ጋር እንዲያስተያዩ ባላቸው ሙያ እንዲያበረታቱ መክረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ አርብ ጠዋት ኮሜዲያኖቹን ተቀብለው እንደተናገሩት ኮሜዲያኖች በጣም ከሚወደዱ እና ከሚደነቁ የመዝናኛ ባለሙያዎች መሃል አንዱ እንደሆኑ ገልጸው፥ ምክንያቱም ደግሞ “ሰዎችን የማሳቅ ስጦታ ስላላቸው እና ስላዳበሩ ነው” ብለዋል።

በብዙ “ጨለምተኛ ዜና” በሞላበት፣ እንደ ሕዝብም ሆነ በግል ቀውሶች በተበራከቱበት ዓለም መካከል ኮሜዲያኖች “መረጋጋትን እና ፈገግታን” ማሰራጨት ችለዋል ያሉት ብጹእነታቸው፥ “በጣም ከተለያዩ ሰዎች፣ ከተለያዩ ትውልዶች እና ከተለያዩ ባህላዊ ሰዎች ጋር መግባባት እና መነጋገር ከሚችሉት ጥቂቶች ሰዎች መካከል ናቸው” ብለዋል።

ይህ እውነታ ነው፥ ምክንያቱም “ሳቅ ከአንዱ ወደ አንዱ ስለሚጋባ” ነው፥ እንዲሁም “ማህበራዊ ተግዳሮቶችን አስወግዶ ግንኙነቶችን መፍጠር ይችላል” ብለዋል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ። በማከልም ኮሜዲያኖች “ጨዋታዊ ቀልድ እና ሳቅ በሰው ሕይወት ውስጥ ዋና ዋና ነገሮች እንደሆኑ” ያስታውሱናል ብለዋል።

ውድ ስጦታ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለኮሜዲያኖቹ እንደተናገሩት “በልቦቻችን ውስጥ እና በሰዎች መካከል ሰላምን የሚያሰፍን፣ ችግሮችን ለማሸነፍ እና የዕለት ተዕለት ጭንቀትን ለማስወገድ የሚረዳ “ውድ ስጦታ” እንዳላቸው ተናግረዋል።

ቅዱስ አባታችን በመቀጠልም “ተአምር” ያሉትን የኮሜዲያንን ሌላ ተሰጥዖ ሲገልጹ፥ “ሰዎች በከባድ ጉዳዮችን ተይዘው ባሉበት ወቅት እንኳን ሰዎችን ፈገግ እንዲሉ ማድረግ ይችላሉ” በማለት ከገለጹ በኋላ፥ “የስልጣን መብዛትን ታወግዛላችሁ፣ ለተረሱት ድምጽ ትሰጣላችሁ፣ ተገቢ ያልሆኑ ባህሪያትን ትጠቁማላችሁ… ነገር ግን ይህን ስታደርጉ ያለምንም ማንቂያ እና ሽብር ነው፣ እንዲሁም ጭንቀት ወይም ፍርሃት ሳታሰራጩ ነው” ብለዋቸዋል።

አምላክን ደስ ማሰኘት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በሥነ ፍጥረት ውስጥ “መለኮታዊ ጥበብ የጥበብ ክህሎታችሁን ያጎናጸፋችሁ ሌላ ለማንም ሳይሆን በታሪክ የመጀመሪያ ተመልካች ለሆነው ለአምላክ ነው፥ እግዚአብሔርም በሠራው ሥራ ደስ ይለዋልና” በማለት የአምላክን ምሥጢራዊ ሥራ ጠቁመዋል።

“ይህን አስታውሱ” ያሉት ቅዱስ አባታችን፥ “በአንድ ተመልካች ከንፈር ላይ ደማቅ ፈገግታ ማምጣት ስትችል አምላክንም ፈገግ ታደርጋለህ” ብለዋል።

ማንንም ፈጽሞ አይቃወምም

በአስቂኝ ሁኔታ ማሰብ እና መናገር የሰውን ተፈጥሮ እንድንረዳ እና እንድንገነዘብ እንደሚረዳን አበክረው ከተናገሩ በኋላ፥ ቀልድ “አያስከፋም፣ አያዋርድም፣ ሰዎችን በስህተታቸው ‘አያሸማቅቃቸውም’” ብለዋል።

ከሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች በተለየ፣ ቀልድ ከማንም ጋር በፍጹም በተቃራኒ አይቆምም፥ ነገር ግን ሁል ጊዜ አካታች እና ንቁ ነው፣ በተጨማሪም ግልጽነትን፣ መተሳሰብን እና የሌላውን ስሜት መረዳትን ያነሳሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዲያውም “ከምንወዳቸው ጋር እንደምንጫወት እና እንደምንቀልድ ሁሉ በአምላክም ደስ መሰኘት እና መሳቅ እንችላለን። ነገር ግን ይህ መደረግ ያለበት የአማኞችን ሃይማኖታዊ ስሜት በተለይም የድሆችን ሳያስከፋ ነው” ብለዋል።

የተሻለ ዓለም ማለም

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ንግግራቸውን ያጠናቅቁት “ሰዎችን በተለይም ህይወትን በተስፋ መመልከት በጣም የሚከብዳቸውን ማበረታታቱን ቀጥሉ፥ በፈገግታ ውስጥ ሆነን እውነታውን ከተቃርኖዎቹ ጋር ለማየት እና የተሻለ ዓለምን ለማየት እንድንችል እርዱን!” በማለ በሥፍራው የተገኙትን እና ጥበባቸውን በመባረክ ነው።
 

19 June 2024, 17:01