በር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የተመራው የካርዲናሎች መደበኛ ጉባኤ በር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የተመራው የካርዲናሎች መደበኛ ጉባኤ   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

የብጹዕ ካርሎ አኩቲስ እና የሌሎች አሥራ አራት ብፁዓን ቅድስና ጸደቀ

በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መሪነት የተካሄደው የካርዲናሎች መደበኛ ጉባኤ ብፁዕ ካርሎ አኩቲስን ጨምሮ 15 ብጹዓንን ቅድስናን አጸደቀ። ከፍተኛ የካርዲናሎች ጉባኤ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በመሆን ሰኞ ሰኔ 24/2016 ዓ. ም. ማለዳ በቫቲካን ውስጥ መደበኛ ጉባኤ አካሂዷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም የሚኖሩ ብጹዓን ካርዲናሎች የበርካታ ብፁዓን የቅድስና ማስረጃዎችን ከማጤናቸው በፊት ያደረሱትን የማለዳ ጸሎት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መርተዋል።

በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮች ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ በጉባኤው ወቅት የአሥራ አምስቱ ብጹዓን ሕይወት እና በስማቸው የታዩ ተዓምራትን በማስመልከት ማስረጃዎችን ካቀረቡ በኋላ ጉባኤው ድምጽ ሰጥቶ ቅድስናቸውን አጸድቆላቸዋል።

የሰማዕታት እና የመነኮሳት የእምነት ምሳሌነት
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አዲሶቹ ቅዱሳን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1860 ዓ. ም. በሶርያ ከተማ ደማስቆ ውስጥ በሰማዕትነት የተገደሉ እና “የደማስቆ ሰማዕታት” በመባል የሚታወቁ ናቸው።

እነርሱም አባ ማኑዌል ሩይዝ ሎፔዝ የተባሉ ፍራንችስኮስዊ ካኅን ከሰባት አጋሮቻቸው፣ አብደል ሞአቲ፣ ፍራንሲስ እና ራፋኤል ማሳብኪ የተባሉ ፍራንቺሳዊ ወንድሞች እንዲሁም ሦስት የማሮናዊት ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን እንደ ነበሩ ይታወሳል። አሥራ አንዱም የተገደሉት በሶርያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1860 ዓ. ም. ሲሆን በእምነት ጥላቻ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች በሙስሊም ሚሊሻዎች በጭካኔ ተገድለዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ ለጉባኤው ያቀረቡት ማስረጃ እንደገለጸው፥ የማሳብኪ ወንድሞች እና ስምንቱ ፍራንሲስካውያን በደማስቆ በሚገኝ የፍራንችስካውያን ጸሎት ቤት ውስጥ በጸሎት ላይ እያሉ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሐምሌ 9/1860 ዓ. ም. ምሽት መገደላቸው ይታወሳል።

የካርዲናሎች ጉባኤ የሁለቱን ጣሊያን ብጹዓን፥ የአባ ጁሴፔ አላማኖ እና የእህት ኢሌና ጉዌራ ቅድስናን ያጸደቀ ሲሆን፥ ብጹዕ አባ አላማኖ የኮንሶላታ ሚስዮናውያን ማኅበርን በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የሠረቱ ናቸው። እህት ኢሌና ጉዌራ ሕይወቷን ሙሉ ልጃገረዶችን በትምህርት ለማነጽ የሰጠች እና በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የመንፈስ ቅዱስ የእህቶች ማኅበርን መሥርታለች።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የቅዱስ ቤተሰብ ታናናሽ እህቶች ማኅበርን የመሠረቱት ካናዳዊ ገዳማዊት እህት ማሪ-ሊዮኒ ፓራዲስ ቅድስናንም ጉባኤው አጽድቋል።

የአሥራ አራት ቅዱሳን ስም በቅዱሳን መዝገብ ውስጥ እሁድ ጥቅምት 20/2017 ዓ. ም. በይፋ እንደሚጻፍ ተገልጿል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የካዲናሎች ጉባኤ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1981 እና 1996 መካከል የተገኙ፥ በተለምዶ “ሚሊኒየልስ” በመባል የሚታወቁትን የብጹዓን ቅድስናን ለማጽደቅ ድምጽ ሰጥተዋል።

የብፁዕ ካርሎ አኩቲስ ቅድስና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. በሚከበረው የኢዮቤልዩ ዓመት ከሌሎች ብጹዓን ጋር እንደሚታወጅ ይጠበቃል።

አዳጊ ወጣት ካርሎ አኩቲስ ከጣሊያን ወላጆቹ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1991 ዓ. ም. በእንግሊዝ መዲና ለንደን ተወልዶ በሞያው የድረ-ገጽ ዲዛይነር የነበረ ሲሆን፥ በደም ካንሰር ሕመም በተወለደ በ 15 ዓመቱ ጣሊያን ውስጥ ሞንዛ አውራጃ ውስጥ ሕይወቱ ማለፉ ይታወሳል።

ካርሎ አኩቲስ የቅዱስ ቁርባን ተአምራት እና የቅድስት ማርያም ግልጸቶችን እራሱ በነደፈው ድረ-ገጽ ላይ በመመዝገብ ይታወቅ ነበር።

የብጹዓኑ የቅድስና ማስረጃው እንደገለሰው፣ ብፁዕ ካርሎ ድሆችን በፍቅር ተቀብሎ የሚንከባከብ፥ መጠለያ የሌላቸውን እና ስደተኞችን በግል ካጠራቀመው ሳምንታዊ አበል ይረዳቸው እንደ ነበር ተገልጿል።

 

02 July 2024, 13:16